ተወልደው ያደጉት በሐረር ከተማ ውስጥ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሐረር ሞዴልና መድኃኒዓለም በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ለአብራሪነት ተወዳድረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥረው ለጥቂት ወራቶች ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በንግድና ሥራ ፈጠራ መሰማራት አዋጭ ሆኖ ስለታያቸው ሥልጠናውን ያቋርጣሉ።
የተለያዩ ሥራዎችን እየተዘዋወሩ በመስራት አቅማቸውን መገንባት ያዙ። ከዚሁ ጎን ለጎንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በንግድ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከሆላንድ በፐብሊክ ኢንተርፕራይዝ ትምህርት ዘርፍ ሠርተዋል። ገና ተማሪ ሳሉም እየተመላለሱ በሚሠሩት የኢትዮጵያ ምግብ ጥናት ድርጅት ውስጥ የገበያ ጥናት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።
በተቋሙ ውስጥ ከስዊድኖች ጋር በመሆን ሕፃናት ተጨማሪ ምግብ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ጥናት አጥንተዋል። የተለያዩ ለጋሽ አገራትን በማስተባበርና በመንግሥት ድጋፍ 12 ቶን የተመጣጠነ ምግብ ማምረት የሚችለውን የፋፋ የምግብ ፋብሪካን በ1969 ዓ.ም እንዲመሠረት አድርገዋል። በፋብሪካው በዋና ሥራ አስኪያጅነት የቀጠሉት እኚሁ ሰው በወቅቱ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ በመታገል ሂደት ውስጥ ፋብሪካው የጎላ ሚና እንዲጫወት ብዙ ስለመሥራታቸው ይነገራል።
በተለይም በአገሪቱ በነበረው የምግብ እጥረት አነስተኛነት የፋፋ ምግብ ተፈላጊነት በመጨመሩ የማምረት አቅሙ ወደ 24 ቶን እንዲደርስ አድርገዋል። ፋብሪካው የተመጣጠነ ምግብ በማምረት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ቀዳሚ እንዲሆን ቀን ከሌሊት ሠርተዋል። ከውጭ የሚገቡትን የተመጣጠነ ምግቦችን በአገር ውስጥ ምርት የመተካት አቅም እንዲጎለብት የዛሬው የዘመን እንግዳችን አስተዋፅኦ የላቀ እንደነበር ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን የምግብ ላብራቶሪ በፋብሪካ ውስጥ እንዲገነባ አድርገዋል።
በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ፋብሪካው ለተፈናቀሉና በተመጣጠነ ምግብ ለተጎዱ ወገናዊ አለኝታነቱን እንዲያረጋግጥ አግዘዋል። የፋብሪካውን ካፒታል በማሳደግ በዓመት የማምረት አቅሙን ወደ 34 ሺ ቶን እንዲያመርት ያደረጉት አስተዋፅኦ ከውጭ እርዳታ እስኪመጣ ድረስ የሁለት ሚዮኖችን ሕይወት ለመታደግ አስችሏል። በዚህም ሥራቸው የአውሮፓ ፓርላማ ልዩ ሽልማት አበርክቶላቸዋል። ከተለያዩ አገራት ጋር በመተባበር ወተትም ሆነ በርካታ የተመጣጠኑ የምግብ ዓይነቶችን በሰፋት በማምረት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን አድርገዋል። ይህም የምግብ ኢንዱስትሪው እንዲያብብ ፈር ቀዳጅ እንደሆነም ይነሳል። ከዚሁ ሥራ ጎን ለጎን በአገሪቱ የወጭ ንግድ ላይ ችግር በማጋጠሙ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኮርፖሬሽን የኤክስፖርት ማኔጀር ሆነው በተደራቢነት ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል።
እኚሁ ሰው ለአገርም ሆነ ለዘርፉ እድገት ለ19 ዓመታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያበረክቱም በ1983 ዓ.ም በአገሪቱ ከተደረገው የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በዓመቱ ከፋብሪካው እንዲለቁ ተደርገዋል። እሳቸው ግን ከሥራ በመሰናበታቸው ተስፋ አልቆረጡም፤ የነበራቸውን ገንዘብ በማሰባሰብና ሌሎች ደጋፊ አካላትን በማስተባበር የመጀመሪያውን የግል ጤና ምግብ አምራቾች የተባለ ፋብሪካ ከፈቱ። ቀደም ሲል ለፋፋ ግብዓት የሚሆኑና ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን ከግብርና ምርምር ጋር በመሆን በአገር ውስጥ እንዲመረቱ አድርገዋል።
በተለይም የመጀመሪያውን የአኩሪ አተር ምርት በመንግሥት እርሻዎች በሙሉ በማባዛት ያልተበረዘ የኢትዮጵያ አኩሪ አተር እንዲኖር በማድረጋቸው በዘርፉ ስማቸውን ተክለዋል። በፋብሪካው የአኩሪ አተር ኬክና ለከብት መኖ የሚሆኑ
ምርቶችን በየቀኑ እስከ 750 ኩንታል ማምረቱን ቀጠለ። የመጀመሪያው የአኩሪ አተር ፋብሪካም የነበራቸው እኚሁ ሰው በድርቅ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ዜጎች በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ መበላት የሚችል በስሎ የተዘጋጀ ምግብ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር አምርተዋል።
በተጨማሪም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አሰብ በመወሰዱና አሰብ ላይ ይሠራ የነበረው ጨው ላይ አዮዲን የመቀላቀል ሂደት በመቋረጡ ከአፋር ጨው በማስመጣትና አዮዲን እየደባለቁ ለኅብረተሰቡ በማከፋፈል በወቅቱ እንደአገር ላጋጠመው ችግር ፈጥኖ ደራሽ መሆን ችለዋል።
እንግዳችን በአሁኑ ወቅት ከፊሉን የድርጅታቸውን ድርሻ ለልጆቻቸውና ለፈረንሳይ ኩባንያ ቢያስተላልፉም፤ ዓለም አቀፍ ምስክርነት ያለውን የምግብ ላብራቶሪ በማምረት ላይ ይገኛሉ። ድርጅታቸው በተለይም መንግሥት በሚያከናውናቸው የልማት መርሃግብሮች ሁሉ የበኩሉን ድጋፍ እንዲሰጥም ዕድሜ ሳይበግራቸው እየሠሩ ነው።
ከዛሬው የዘመን እንግዳችን የበለጠና ቤተሰቡ የምግብ ኢንዱስትሪዎች የቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም የብሌስ ላብራቶሪ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ በለጠ በየነ ጋር በሕይወት ተሞክሯቸውና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለምልልስ እነሆ ብለናል። አዲስ ዘመን፡- ወደዚህ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ የገቡበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር? አቶ በለጠ፡- እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ ሥራ እወዳለሁ።
ለቱሪስቶች እያስተረጎምኩኝ ገንዘብ ማግኘት የጀመርኩት ገና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነው። በተለይ የንግድ ሥራን ከልቤ እወደው ስለነበረና ለመለወጥም ከፍተኛ ህልም ስለነበረኝ የአየር መንገዱን ሥራ ትቼ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ንግድ ማጥናት ጀመርኩ።
ዩኒቨርሲቲ ገብቼ እጄን አጣጥፌ አልተማርኩም፤ ይልቁንም የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ራሴን እደጉም ነበር። ተማሪ ሆኜ ከሠራሁባቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ምግብ ጥናት ድርጅት አንዱ ነው። ትምህርቴን እንዳጠናቀኩ እዚያው ተቀጥሬ መሥራት ቀጠልኩ። እንዳልኩሽ ፈጣንና ሥራ ወዳድ ስለነበርኩኝ ወደ ኃላፊነት ለመምጣት ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም። በተለይም በምግብ ኢንዱስትሪው መስክ የላቀ እውቀት እንዲኖረኝና እውቀቴን ለአገር እድገት ጥቅም ላይ እንዳውል ድርጅቱ ትልቅ እገዛ አድርጎልኛል።
እናም እዚያ የተጀመረው የምግብ ኢንዱስትሪ ልማት በ1984 ዓ.ም ከሥራ ከተሰናበትኩኝ በኋላም በዚያው ሙያ በመቀጠሌ አሁን የሚታየውን ድርጅት ማቋቋም ቻልኩ። በእርግጥ ስጀመር በጥቂት ካፒታልና የሰው ኃይል ነበር። የአኩሪ አተር ከውጭ በማስመጣት የተመጣጠነ ምግብና ወተት በማምረት የተጀመረው ሥራ እየዋለ ሲያድር አዮዲን ያለው ጨው፤ የበሰሉ ምግቦች፤ ጤፍና ሌሎች እሴት የተጨመረባቸውን የግብርና ውጤቶች እያመረትን አቅማችንን ማሳደግ ችለናል። ይህንን ፋብሪካ ወደ ማስፋፋት የመጣሁት ዩኒሴፎች ባደረጉልኝ ስምምነት መሠረት ብድር በመውሰድና ከኦሮሚያ ክልል መሬት አግኝቼ በኢትዮጵያ ትልቁ በስሎ የተዘጋጀ የነፍስ አድን ምግብ አምራች እንዲሆን ማድረግ ችለናል። ለምርቶቻችን መሠረታዊ ጥሬ ዕቃው ኦቾሎኒ ነው።
በብዛት ከሐረርና ከመተከል እናገኝ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየቀነሰ ስለመጣ ከውጭ ለማስመጣት ተገደናል። በተመሳሳይ ለዘይትም የምንጠቀመውን አኩሪአተር የምናስመጣው ከውጭ ነው። ያም ሆነ በመንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ ይደረግልናል። ከቀረጥ ነፃ ስለሚደረግና እኛም የውጭ ምንዛሬ ስለምናመጣ የምናወጣውን ወጪ ያካክስልናል። ድርጅታችን በአሁኑ ወቅት ከአትክልት የሚሰራ ስጋ እየሠራ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች ምሳ መደጎሚያ የሚሆን የእንቁላል ዱቄት ፋብሪካ ሰርተናል። በተመሳሳይ ከአፍላ ቶክሲን ችግር ነፃ የሆነ የኦቾሎኒ ቅቤ በማምረት ለትልልቅ ሆቴሎችና ኩባያዎች እናድርሳለን። በተመሳሳይ ጤፍ ላይም ለረጅም ጊዜ ከገበሬዎች ጋር ጥናት በማድረግ ተፈጥሮአዊ ይዘቱን እንደጠበቀ በማምረት ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- የመጀመሪያውን የግል የምግብ ላብራቶሪ በመቋቋም ረገድ የእርሶ ድርጅት ፈርቀዳጅ ነው። በዚህ ረገድ ላብራቶሪው ለአገሪቱ ምን ዓይነት አስተዋፅኦ አበርክቷል ማለት ይቻላል?
አቶ በለጠ፡- እንግዲህ በአገራችን ባህል አንድ ነገር አለ፤ እንጀራ ተጋግሮ፤ ወጡ ተዘጋጅቶ ባለቤትየው ጋር ሲቀርብ በመጀመሪያ ወንድየው ለሚስት ያጎርሳል፤ የሚያጎርስበት ዋነኛ ምክንያት ሁለት ነው፤ አንድም ለባለቤቱ ያለውን አክብሮትና ፍቅር ለመግለፅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ንፁህ መሆኑን ሯሳ ቀምሳ እንድትረጋግጥለት ነው። ስለዚህ ማንኛውም ምግብ ደህንነቱ ካልተረጋገጠ ሸማቹ ሊመገበው አይችልም። አዘጋጁ ራሱ ወዶትና ጣፍጦት የሚበላው መሆን አለበት። በፋብሪካ ደረጃ የሚመረተው ምርት ባለቤቱ የሚበላው ምርት መሆን አለበት።
ንፁህ መሆኑ መረጋገጥ አለበት። ነገር ግን ሁሉም ፋብሪካ ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም የጥራት ጉድለት በየቦታው አለ። አብዛኞቹ አምራቾች እነሱ የማይበሉትን ምግብ እየሰጡን ነው። ስለዚህ ይህንን የሚያረጋግጥ ላብራቶሪ ያስፈልጋል። ደግሞም ወደ ውጭ የምንልካቸው ምርቶች ላብራቶሪ ተመርምረው ደህንነታቸው የተረጋገጠ ሊሆኑ ይገባል። ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ምስክርነት የሚሰጥ ተቋም መገንባት መቻላችን ለአገር ጥቅም ትልቅ አንድምታ አለው። አንድም ምርቶቻችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያግዛል፤ ሁለትም በዚህ ረገድ አገሪቱ ያለባትን ክፍተት በመሙላት ረገድ ሚናው የላቀ ነው የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ በላይ ደግሞ ህሊና ምግብ ፋብሪካ ዓለምአቀፍ እውቅና እንዲያገኝ የላብራቶሪው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በነገራችን ላይ ይህንን ላብራቶሪ ስንገነባ የሆላንድ መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎልናል።
በዚህ ላብራቶሪ መጠቀም ማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ ደህንነት ሕይወት መታደግ ማለት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የውጭ ንግዱን ለማስፋፋት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል። አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ በአገሪቱ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በመቀነስ ረገድ ሚናውን በሚገባ ተወጥቷል ማለት ይቻላል? ተደራሽነቱስ ምን ያህል ሰፍቷል? አቶ በለጠ፡- አስቀድሜ እንዳልኩሽ አሁን ልጄ የምትመራው ህሊና ምግብ ፋብሪካ ባለፉት 20 ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ምርት ሲያመርት ቆይቷል።
ከውጭ የሚመጣውን አብዛኛውን የተመጣጠነ ምግብ በመተካት ሂደት የጎላ ሚና እየተጫወተ ነው። እርግጥ ይህንን ደረጃውን የጠበቀ ምርት ማምረት የቻልነው የተመሰከረለት ላብራቶሪ በመገንባቱ ነው። የእነዚህ ፋብሪካዎች መኖር ዓይን ገለጭ ነው። በተለይ ጤና ምግብ ለተባበሩት መንግሥታት የምናቀርበው እኛ ብቻ ነን። ከዚያ በፊት ግን የምናስመጣው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ ከውጭ ነበር።
በወቅቱ እንዲያውም እስከ 150 ሺ ቶን ምግብ የሚመጣው ከውጭ ነበር። ከእኛ በኋላ ግን ሌሎች ሰባት ፋብሪካዎች ተመሳሳይ ተገንብተዋል። እኛ የጀመርነው ሥራ እውቀት ተራመደ ወይም ተስፋፋ ማለት ይቻላል። በአጠቃላይ ከውጭ ይገባ ከነበረው 75 በመቶ የሚሆነውን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ባይ ነኝ።
በተጨማሪ የአኩሪ አተር ዘይት፣ መኖ እንዲሁም እርሻ እንዲነቃቃ ምክንያት ሆኗል። ከሁሉ በላይ የተመጣጠነ ምግብ አስፈላጊነት እውቀቱ እንዲስፋፋ ማድረጉ ለእኔ ትልቅ እምርታ ነው። ምክንያቱም የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ ማድረግ መቻል በራሱ ብቁና ጤናማ ጭንቅላት ያለውን ትውልድ ለማፍራት ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ነው።
በአጠቃላይ አሁን ያለው የፀጥታ ችግር ከተሻሻለ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች አሉ። ከተደራሽነት አኳያ ያነሳሽልኝ ጥያቄ እኔ ለመመለስ ይከብደኛል፤ ምክንያቱም እኔ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 24 ሚሊዮን ነበር። ዛሬ 120 ሚሊዮን ደርሰናል። ይህም ማለት ወደ አምስት እጥፍ ብዛታችን ጨምሯል ማለት ነው።
ታዲያ በዚህ ልክ ኢንዱስትሪዎቻችን አድገዋል ብሎ ለማሰብም ሆነ ተደራሽነት አለው ለማለት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ፋብሪካዎቹ በሚፈለገው ደረጃ አልሰፉም። ከዚህ አንፃር የተሠራው ሥራ እምብዛም ነው። አሁንም ቢሆን ያለን እምቅ አቅም በጣም ሰፊ ነው። ብዙ መሬቶች ሳይታረሱ ፆም እያደሩ ነው። በአመት ሦስት ጊዜ ማምረት የሚያስችል የውሃ ሀብት አለን፤ ግን ጥቅም ላይ አላዋልነውም።
ስለዚህ እኔ እንደማምነው ለእንደዚህ ዓይነት ዘርፎች ትኩረት ሊደረግ ይገባል። በተለይም በእርሻ ላይ ለሚሰማሩ፤ እሴት ለሚጨምሩ ብዙ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። ለምሳሌ በመሬት አቅርቦት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፤ በታክስና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተለየ ማበረታቻ መኖር አለበት። የተመጣጠነ ምግብ ማምረት ማለት አስቦ የሚሠራ ሕዝብ ማምረት ማለት ነው።
ማመዛዘን እውቀት ያለው ሕዝብ መፍጠር ማለት ነው። በእውነት ካለንበት ችግር እንድንወጣ ከተፈለገ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ላይ መወሰን ይገባል። ምክንያቱም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ትልቁ ችግራችን ነው።
እንደሚታወቀው ደግሞ በአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ ዋና አጀንዳ ሆኖ የቀረበው የተመጣጠነ ምግብ ጉዳይ ነው። ስለዚህ እኛም ለዚህ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መስጠት አለብን። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ኢትዮጵያ የታደለች ነች። አብዛኞቻችንም ጥራጥሬ ስለምንበላ የጭንቅላት አቅማችን ጥሩ ነው። ግን ያንን ምርት ሁሉም ሕዝብ እንደልብ ሊያገኘው ይገባል፤ ለዚያ ደግሞ በብዛት መመረት መቻል አለበት።
ሕዝባችን በጨመረ ቁጥር የሚመረትበት ቦታ እያነሰ ይመጣል። አሁን ላይ አብዛኛው አርሶአደር እያመረተ ያለው ከአንድ ሄክታር በታች በሆነ መሬት ላይ ነው። ይሄ በቂ አይደለም። ስለዚህ አሁንም ያልታረሱ መሬቶቻችንን ማረስ መቻል አለብን። ይህንን ስናደርግ በቶሎ ከምግብ ተመፅዋችነት ልንላቀቅ እንችላለን። ምሁራንንም በሚገባ ማሳተፍና መተጋገዝ መቻል ይገባናል። አዲስ ዘመን፡- ከኢንዱስትሪ ሽግግር አኳያ በተለይ በምግብ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተከናወነ ያለው ሥራ ምን ይመስላል? አቶ በለጠ፡- ይህ ጉዳይ እርግጥነው በፊትም ቢሆን በጥቂቱ የተጀመረ ነገር ነበር።
ለምሳሌ እኛ በአነስተኛ ጥቃቅን ደረጃ እንዲሁም ገበሬዎችን እየተዘዋወርን እንዴት የተመጣጠነ ምግብ ማዘጋጀት እንደሚቻል እናሰለጥን ነበር። የፋፋ ምግብ ፋብሪካም በተለይ አኩሪ አተርን በኢንዱስትሪ አቀነባብሮ ጥራቱ የተጠበቀ የተመጣጠነ ምግብ በማምረት ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በርካታ ጥናቶች ተከናውነው ተግባራዊ እንዲሆኑ በፋፋም ሆነ በጤና ምግብ ብዙ ተሠርቷል። አሁን ያለው ድርጅታችንም ከገበሬዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው።
ጤፍና ስንዴንም በማቀነባበር በቅርቡ ወደ ውጭ ለመላክና ለአገራችን የውጭ ምንዛሬ ለማስገባት እየሠራን ነው። ከዚህ ባሻገር ላብራቶሪው በሚያደርገው ምርምር እገዛ ዕድሜው የረዘመ የጤፍ ዱቄት ለገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የግብርና ውጤቶች ቢኖሩም በኢንዱስትሪ እሴት በመጨመር ረገድ ሰፊ ክፍተት አለ። እሴት ቢጨመር ኖሮ አሁን ከምንሸጥበት ዋጋ ሦስትና አራት እጥፍ ሊገኝ ስለሚችል ያንን እንደሞዴል ለማሳየት የምናደርገው ጥረት ዘርፉን በጥቅሉ ሊያሳድገው የሚችል ነው።
እኛም ያለንን እውቀት ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ስላለብን ከትርፉ በላይ የሚያሳስበን እውቀቱን ማሸጋገሩ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ካላት የአዝዕርት ውጤት ተጠቃሚ እንድትሆን የኢንዱስትሪ ሽግግሩ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አገራችን በአመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ማምረት የሚያስችል አየር ንብረትና ስነምህዳር ባለቤት ናት። ይህንን ምቹ የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ ከተጠቀምን ራሳችንን በምግብ እህል የማንችልበት ምክንያት አይኖርም። የሚገርምሽ በጓሮ አትክልት ብቻ ራሷን የመቻል አቅም አላት። ይህንን ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል ሁሉም የየበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባል። እውቀት ያለው በእውቀቱ፤ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፤ ጉልበት ያለውም በጉልበቱ ተባብሮ አገራችንን ማሳደግ አለብን ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት ትምህርት ተቋማት የምገባ ባህል እየተስፋፋ መምጣቱ ለመማር ማስተማሩ ውጤታማነት ያለው ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ በለጠ፡- እንግዲህ በተለይ በአዲስ አበባ ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።
በተለያዩ ምክንያቶች ደግሞ እያንዳንዱ ቤተሰብ ገቢ እየቀነሰ መጥቷል። አንድ ሰው ለምግብ ብቻ እስከ 30 እስከ 40 በመቶ ካለው ገቢ ለምግብ ያወጣል። ነገር ግን ካለው የኑሮ ውድነት የተነሳ ያንን ያህል ማውጣት ተስኖታል። በዚህ ችግር ደግሞ በዋናነት የሚጎዱት ሕፃናትና እናቶች ናቸው። በዚህም ምክንያት ተማሪዎች በቤት የሚበሉት ምግብ ባለመኖሩ ምክንያት በሚገባ ትምህርታቸውን ለመከታተል አልቻሉም፤ በተለያዩ በሽታች የሚጠቁትም በርካቶች ነበሩ።
ይህ ችግር በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቶ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ወይዘሮ ሮማን አማካኝነት የምግባ መርሃግብሩ ተጀምሯል። በመሆኑም መንግሥት ችግሩን በዚህ ደረጃ ተረድቶ ምገባ ማካሄዱ ጥሩ እርምጃ ነው ባይ ነኝ። ግን ደግሞ በብዛት የሚቀርበው ሽሮ ወጥ ነው። ሽሮ ደግሞ የሚጠበቀውን ኃይልና ንጥረ ነገር ይሰጣል ተብሎ አይታመንም።
ይህንን ጉዳይ ዩኒሴፍ ለረጅም ጊዜ ሲያስብበትና ሲያስጠና ከርሞ ከእኛ ጋርም በመነጋገር ሽሮ ላይ እንቁላል እንዲጨመርበትና ተማሪዎቹ ፕሮቲን የሚያገኙበት መንገድ ተቀይሷል። አሁን ላይ እንቁላል እየተወደደ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ እንቁላሉን በዱቄት መልክ በማዘጋጀት ከሽሮ ጋር ተማሪዎቹን መመገብ እንዲቻል ዝግጅት አጠናቀናል። ይህም ለትምህርት ቤቶች ጥሩ ዜና ይመስለኛል። ከዚህ በኋላ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ሊሳተፉበት ይችላሉ። በአጠቃላይ የምገባ መርሃ ግብሩ ጤናማ ኅብረተሰብ በመፍጠር ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። እኛም ደግሞ የዚህ አካል በመሆናችን እጅግ ያስደስተኛል።
አዲስ ዘመን፡- የአገሪቱን የምግብ ኢንዱስትሪ አሁን ካለበት በላቀ ደረጃ በማሳደግ ረገድ ድርጅታችሁ በቀጣይ ምን ለመሥራት አቅዷል?
አቶ በለጠ፡- ፈረንጆቹ ‹‹ታንጎን ለመደነስ ሁለት ሰው ያስፈልጋል›› እንደሚሉት እኛ ብቻ ስላቀድን የሚሳካ ነገር የለም። መንግሥትም ሊያግዘን ይገባል። እንዳልሽው ህሊና ምግብ አሁን የሚያመርተው ወደ 7ሺ 500 ቶን ገደማ ነው። ወደ 15 ሺ ቶን ለማድረስ እቅድ ይዘናል።
በመሠረቱ ሁሌም ቢሆን ካለን ገቢ ውስጥ 50 በመቶውን የምናወጣው ለዳግም ኢንቨስትመንት ነው። ይህም የሚሠራው በእኔ ቤተሰብና ከፈረንሳዮች ጋር በተደረገ ጥምረት ነው። አሁንም ከዚህ በላይ በጋራ ለማልማት ፍላጎት አለን። መንግሥት ደግሞ በእርግጥ በታክስ ረገድ ያግዘናል፤ ነገር ግን አሁን ላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለ። ሌሎችም ችግሮች በዘርፉ ላይ ትልቅ ተግዳሮት ሆነዋል። ስለዚህ መተጋገዙን የበለጠ ማጠናከርና ከሁለቱም አቅጣጫ ቢሆን ይመረጣል።
መንግሥት በአሠራር ሥርዓቱ በተለይም ጥሬ ዕቃ በአገር ውስጥ እንደልብ የሚገኝበት ሁኔታ ላይ ቢሠራ ዘርፉን ማሳደግ ይቻላል ብዬ አምናለሁ። በተለይም ግብርና ለኢኮኖሚው 50 በመቶ አመታዊ እድገት አስተዋፅኦ የሚያደርግ ዘርፍ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ 80 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮው በግብርና ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም ግብርናውንም ሆነ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ እኛ ብቻ ሳንሆን መንግሥትም የበኩሉን ሥራ መሥራት አለበት።
ሌሎችም እኛን አይተው ወደ ዘርፉ እንዲገቡ የሚያበረታታ ሁኔታ መፈጠር ይገባዋል። ደግሞም የምግብ ኢንዱስትሪ የማያቋርጥ የገቢ ምንጭ በመሆኑ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዘርፉን ለማሳደግ ለሚፈልጉ ሰዎች እንደቅርብ ጓደኛ አስቦ መንከባከብ ይኖርበታል። እናም ይሄ ኢንዱስትሪ ከውጭ ብዙ እህል እያሰገባ ነው። ለምሳሌ የእኛ ፋብሪካ የሚያመርተው ስንዴና ስኳር በከፍተኛ መጠን ከውጭ እያስገባ ነው፤ ይህም ምን ያህል ኢንዱስትሪውንም ሆነ አገሪቱን እንደሚጎዳ የሚያጠያይቅ አይደለም። እርግጥ እስካሁን ድረስ ብዙ ሥራ ተሠርቷል፤ ግን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት አልተቻለም። ስለዚህ በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ አካላትን እንደመንግሥት የልማት አጋር በማየት በሁሉም ነገር ቅድሚያ መሰጠት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ እስቲ እርሶ ትውልዷ የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት ተድርጋ ከምትወሰደው ሐረር ከተማ እንደመሆንዎ ይህንን እሴት በማስቀጠል በኩል መሠራት ይገባዋል የሚሉት ሃሳብ ካልዎት ዕድሉን ልስጥዎትና በዚሁ እናብቃ?
አቶ በለጠ፡- እንደሚታወቀው፤ አንቺም እንዳነሳሽው ሐረር የፍቅርና የመቻቻል አብነት የሆነች ውብ ከተማ ነች። ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ በሰላምና በእኩልነት የሚኖርባት ናት። በአንድ ጊቢ ውስጥ ከተለያዩ ብሔር ብሔርሰቦች የመጡ ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ማንም ስለማንም ብሔር ጠይቆ አያውቅም ነበር። ትምህርት ቤት ስንማርም የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር ነው። በመሠረቱ የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር ደስተኛ ያደርጋል።
እኔ አሁን ከአማርኛ እና ኦሮምኛ ውጪ ፈረንሳይኛ መናገር እችላለሁ። ይህም ብዙ እንድጠቀም አድርጎኛል። በልጅነቴ ፈረንሳይኛ በመቻሌ ቱሪስቶችን አስጎበኝ ነበር። ሐረር ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ ከአንድ በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ነው። ስለዚህ ቋንቋ ማወቅ ፍቅር ማወቅ ነው። ትዳር ስንይዝም የብሔራችን ጉዳይ አሳስቦን አያውቅም። እኔ አሁንም ቢሆን የትኛውንም ሰው ሰውነቱ እንጂ ማንነቱ ጉዳዬ አይደለም። አሁን ላይ የምናየው ልዩነት ለእኔ አይገባኝም። ስለዚህ ሐረር ማለት ትንሽዋ ኢትዮጵያ ናት።
አሜሪካ ከተለያዩ አገራት መጥተው የተጠለሉባት ታላቅ አገር ናት፤ ይህች አገር የዓለምን ትልቅ ኢኮኖሚ መገንባት የቻለችው የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተባብረው ስላቀኗት ነው። እኛም ከተባበርን እዚያ ላይ የማንደርስበት ምክንያት የለም። ስለዚህ ያንን ባህል በትውልዱ ማስቀጠል ይገባናል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ በለጠ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014