የ2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን 1ኛው ዙር ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ውድድሮች በሐዋሳ ሲካሄዱ ቆይተው ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም መጠናቀቃቸው ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ ከአንድ ወር ላላነሰ ጊዜ ክለቦች ዕረፍት ወስደው ለሁለተኛው ዙር ፍልሚያ በመዘጋጀት ላይ ይገኛሉ።
የ2ኛው ዙር ውድድር ከየካቲት 20 ቀን 2014 ጀምሮ ለአራት ቀናት በጎንደር ከተማ የሚካሄድ ሲሆን፣ ለዚህም ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብዱልፈታ ተማም ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል።
በሁለቱም ጾታ አምስት አምስት ክለቦች እየተሳተፉበት በሚገኘው የዘንድሮው የውድድር ዓመት የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አዳዲስ ክለቦች ፉክክሩን ተቀላቅለው ጠንካራ ተፎካካሪ መሆናቸውን በመጀመሪያው ዙር ውድድር እንዳሳዩ አቶ አብዱልፈታ ገልጸዋል።
በሐዋሳው የውድድሩ ቆይታ በወንዶች ሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት ማጠናቀቅ ችሏል። ሐዋሳ የመጀመሪያውን ዙር አራት ጨዋታዎች ሁሉንም በማሸነፍ በስምንት ነጥቦች መሪነቱን ይዟል፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች በአጠቃላይ 302 ቅርጫቶችን አስቆጥሮ 195 ቅርጫቶች ተቆጥረውበታል። ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀሉ አዲስ ክለቦች አንዱ የሆነው ሰበታ ከተማ የመጀመሪያውን
ዙር ውድድር በጠንካራ ተፎካካሪነት ማጠናቀቅ ችሏል። ሰበታ ከአራቱ ጨዋታዎች ሶስቱን በማሸነፍ በሰባት ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን በሁለተኝነት ይከተላል። በእነዚህ ጨዋታዎችም 241 ቅርጫቶችን አስቆጥሮ 219 ቅርጫቶች ተቆጥረውበታል። ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻለው ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ 224 ቅርጫቶችን አስቆጥሮ 235 ቅርጫቶች ተቆጥረውበት በስድስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የካ ክፍለ ከተማ አንድ ጨዋታ ብቻ በማሸነፍ አምስት ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። 239 ቅርጫቶችን አስቆጥሮም 247 ቅርጫቶች ተቆጥረውበታል።
የሁለተኛው ዙር ውድድር የሚካሄድበት ከተማ ክለብ የሆነው ጎንደር ከተማ በሐዋሳው የመጀመሪያ ዙር ውድድር አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። በዚህም በአራት ነጥቦች 179 ቅርጫቶችን አስቆጥሮና 299 ተቆጥሮበት የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ሁለተኛውን ዙር ፍልሚያ ያደርጋል።
ከወንዶቹ በተሻለ በአንጻራዊነት ተመጣጣኝ ፉክክር በተስተዋለበት የመጀመሪያው ዙር የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ወልቂጤ ከተማ በመሪነት ማጠናቀቅ ችሏል። ወልቂጤ ከአራቱ ውድድሮች ሶስቱን ሲያሸንፍ 249 ቅርጫቶችን አስቆጥሮ 155 ተቆጥሮበታል። በዚህም ሰባት ነጥቦችን ሰብስቦ የመጀመሪያውን ዙር በመምራት አጠናቋል።
በተመሳሳይ ሐዋሳ ከተማ ሶስት ጨዋታዎችን ያሸነፈ ቢሆንም ባስቆጠረው የቅርጫት ብዛት ከወልቂጤ በነጥብና በደረጃ አንሶ ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል።
ሐዋሳ በአጠቃላይ 176 ቅርጫቶችን አስቆጥሮ 117 ተቆጥሮበታል። ይህም ስድስት ነጥቦች እንዲሰበስብ አስችሎታል።
አማራ መንገድና ሕንጻ ስራ ያስቆጠረው የቅርጫት ብዛት ከሐዋሳ በአንድ ያነሰ ቢሆንም፣ የተቆጠረበት የቅርጫት ብዛት ካስቆጠረው በልጧል። 175 ቅርጫት አስቆጥሮ 218 ተቆጥሮበታል። ያሸነፈውም ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ነው። ይህም የሰበሰበው ስድስት ነጥብ ከሐዋሳ እኩል ቢሆንም ደረጃውን ሶስተኛ ላይ አስቀምጦታል።
በዚህ ውድድር እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አንድ ጨዋታ አሸንፏል። አካዳሚው በአምስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በአጠቃላይ በአንደኛው ዙር ውድድርም 167 ቅርጫቶችን አስቆጥሮ 195 ተቆጥሮበታል።
በሴቶቹ ፉክክር የመጨረሻውን አምስተኛ ደረጃ ይዞ የሚገኘው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። ያም ሆኖ በውድድሩ 106 ቅርጫቶች አስቆጥሮ 188 ተቆጥሮበታል። ሶስት ነጥቦችን ይዞም በሁለተኛው ዙር ውድድር ለመፋለም ወደ ጎንደር ያቀናል።
የዘንድሮው የውድድር አመት የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በአምስት ዙር የሚጠናቀቅ ይሆናል፤ የተለያዩ አምስት ከተሞችም አንድ አንድ ዙር ፉክክር ያስተናግዳሉ። የሁለተኛው ዙር ውድድር በጎንደር ከተማ ለአራት ቀናት ተካሂዶ ከተጠናቀቀ በኋላ ክለቦች እረፍት አድርገው በወልቂጤ፣ሰበታ፣አዲስ አበባ ከተሞች ውድድሮች እንደሚቀጥሉ ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2014