«ለበጎ ሥራ ለወገንና ለአገር ለመድረስ የተቸገሩትን ለመርዳት ትልቅ አቅም አልያም ትልቅ ሀብት የግድ አስፈላጊ አይደለም። የበጎነት ሥራም በጊዜ ገደብ ተቀንብቦ የሚቀመጥ አይደለም። ቀናነቱ ካለ ማንም በፈለገው ጊዜ ሊያደርገው የሚችለው ነው። ብቻ ከሰው ልብ ውስጥ መገኘት ያለበት በአለን አቅም ስለሰዎች ለመኖር መወሰን ብቻ ነው።» ይለናል የዛሬ የሀገርኛ አምድ እንግዳችን ወጣት ካሌብ ታደሰ።
ካሌብ ተወልዶ ያደገው በመዲናችን አዲስ አበባ ሜክሲኮ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ የካንሰር ህሙማን ማዕከል አጠገብ ነው። የልጅነት ጊዜውን በተዥጎረጎሩ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳሳለፈም ይናገራል። በልጅነቱ እንደማንኛውም የአካባቢው ልጆች ደስ በሚል ሁኔታ በሥነምግባር ታንጾ ያሳለፈ ቢሆንም ወደ ወጣትነት ዕድሜ ሲገባ ግን ነገሮች እንደቀደመው መቀጠል አልቻሉም ነበር። እናም ካሌብ አብዛኛው የአዲስ አበባ ወጣት እንደሚገጥመው እሱም ጊዜውን በአልባሌ ቦታዎች ማሳለፍ ይጀምራል። በልጅነቱ እንኳን ሊያደርጋቸው ሰው ስላደረጋቸውም የሚከብዱትን አንዳንድ ሱስ አምጪ ነገሮችን እስከመጠቀም ደርሶ ብዙ ውጣ ውረዶችን ለማሳለፍ በቅቷል።
ቀን ቀናትን እየወለዱ ሲመጡ ግን ካሌብ መለወጥ እንዳለበት ለራሱ ይነግርና እንቅስቃሴ ይጀምራል። ያቋረጠውንም ትምህርት በመጀመር በኮምፒዩተር ጥገና፤ በፋሽን ዲዛይን፤ በኤሌክትሪሲቲና በፊኒሽንግ ሥራዎች ለመመረቅም ይበቃል። ለጊዜው ሥራ ባይጀምርበትም የመንጃ ፈቃድም ያወጣል። ከነበረበት ጥሩ ያልሆነ ባህሪ በመላቀቅ እንዲህ የባከነ ጊዜውን እያጣፋ መጠቀም መጀመሩን የተመለከቱ በውጭ አገር የሚኖሩ ቤተሰቦቹም አንዳንድ ነገሮችን ያደርጉለት ይጀምራሉ።
«አብዛኛው ሰው ለሚደርስበት ችግርም ሆነ ላለበት ሁኔታ ምክንያት የሚያደርገው ቤተሰቡን፤ የተወለደበትን ሰፈር አልያም አገሩን ነው።» የሚለው ካሌብ ደግሞ የለውጥ ትንቅንቁ መጀመር ያለበት ከራሳችን ከእኛው ከወጣቶች መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ራሳችንን ለመጥቀም ብቻ ሳይሆን በአካባቢያችን ላሉትም ለመድረስ ዝግጁ ማድረግ አለብን የሚል እሳቤ ነበረው። ሀሳቡ ለማንም ሰው ግልጽና ቀላል ቢሆንም ያለምንም ጥሪት፤ ያለማንም ደጋፊ ከግብ ለማድረስ ማሰብ ግን ራስ ሳይጠና ጉተና ዓይነት ትችት በካሌብ ላይ ያስነሳበታል። ይህም ሆኖ የቅርብ ጓደኞቹን በመሰብሰብ ቢያንስ ሻይ ቡና ከምንልበት ላይ ጥቂት ለማድረግ እንሞክር በማለት ያማክራቸዋል። ጓደኞቹም ከፊሉ በሀሳቡ ተስማምቶ ከፊሉም ከነጥርጣሬያቸው ሆነው በሁለት ሺ ስድስት አመተ ምህረት አብረውት ለመሥራት ስለተስማሙ እንቅስቃሴውን ይጀምራል።
በወቅቱ የመጀመሪያ የበጎ ሥራው መዳረሻ ያደረገው ደግሞ በአካባቢው ያሉ ተማሪዎችን መደገፍ ነበር። እንደ ደብተር፤ እርሳስና እስኪብርቶ ያሉ የትምህርት መሣሪያዎች በቀላሉ አለማግኘት ተማሪን ምን ያህል በሞራልም በውጤትም እንደሚደቁሰው ካሌብ በራሱ ተሞክሮ ጠንቅቆ ያውቀዋል። በመሆኑም የአቅሙን በማሰባሰብ አቅም ለሌላቸው ለአስራ አምስት ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት ያቀርብላቸዋል። ነገሩ እንዲህ በቀላሉ የሚከወን መሆኑን ያዩት ጓደኞቹና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ለቀጣዩ አመት ራሳቸውን ሲያዘጋጁ ቆይተው በአመቱ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን የሸፈነ የትምህርት መሣሪያዎች እንዲያቀርብ ይረዱታል። በወቅቱ በወረዳው ካሉና ይህ ችግር ከነበረባቸው ተማሪዎችም አብዛኛዎቹን ለመታደግም ይበቃሉ። ድጋፉ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ በፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የዘወትር ልብስና የትምህርት ቤት ዩኒፎርም አልባሳትን ለተወሰኑት ተማሪዎች ያካተተ ነበር።
የእነካሌብ ሰፈር ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ በአገሪቱ ዋና የሚባለው የካንሰር ህሙማን ማዕከል አጠገባቸው መሆኑ ነው። እዚያ ማዕከል ውስጥ ሕክምናቸውን የሚከታተሉ ሰዎች ደግሞ አብዛኛዎቹ ከአዲስ አበባ ውጪ የመጡና በክፍለ ሀገር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ናቸው። በአንጻሩ ደግሞ የካንሰር ህመም ደግሞ በባህሪው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ መድኃኒቶች የሚፈልግ ነው። ህክምናውም ረጅም ጊዜ የሚወስድ ስለሆነ ሀብት ያለውም ሰው ቢሆን ይህ ችግር ከገጠመው የድህነት መንደርን ለመቀላቀል ጊዜ አይወስድበትም። በዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ ህመምተኞችም ሆኑ አስታማሚ ቤተሰቦቻቸው በርካታ ድጋፎችን በሚሹ ችግር ውስጥ መሆናቸውን እነ ካሌብ የዓይን እማኝ ሆነው ያውቁ ነበር። ነግቶ በጠባም ሰፈራቸው ሲንቀሳቀሱ ስለሚያዩዋቸው ለምን ችግራቸውን አንጋራቸውም የሚል ሃሳብ ያፈልቃሉ። ወዲያውም በመስማማት ከየቤታቸው ልብስ በማሰባሰብ ለአስታማሚ ቤተሰቦች ማካፈል ይጀምራሉ። ታካሚዎቹ ሆስፒታሉ ምግብ የሚያቀርብላቸው በመሆኑ በምግብ በኩል ችግር አልነበረባቸውም።
ነገር ግን በሽማግሌና በአሮጊት አቅማቸው የሚያስታምሙ ቤተሰቦች አንዳንድ ጊዜ የእለት ጉርሳቸውንም የሚያጡበት ሁኔታ አለ። ይህንን ያስተዋለው ካሌብም በአካባቢው ያሉ ምግብ ቤቶች በመለመን ለሁለትም ለሦስትም ሰው እንዳቅማቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ በመጠየቅ ማስመገቡን ይጀምራል። ለአመት በዓልና ለልዩ ልዩ ዝግጅቶችም በማዕከሉ በመገኘት ምግብ የመመገብ ሥርዓት ያካሂዳሉ።
ካሌብ ይህን ሥራ ከጀመረ በኋላ አመት በአላትን በራሱ ቤት አሳልፎ አያውቅም። ሁሌም ከእነሱ ጋር በመሆን ለሙስሊሙም ለክርስቲያኑም አቅሙ የፈቀደውን እያቀረበ አብሯቸው እያከበረ ይገኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንግሥት በአንድ ሺ ስድስት መቶ ብር እየገዙ የሚጠቀሙት መድኃኒት ካለቀ ህመምተኞቹ ወደ ግል መድኃኒት መደብሮች ሄደው ሲገዙ ከእጥፍ በላይ የሚጨምር በመሆኑ እጅግ ፈታኝ ይሆንባቸው ነበር። በመሆኑም ይህንንም ችግር መታደግ ስለሚገባ ካሌብና የበጎ ሥራ አበሮቹ እጅ ላጠራቸው የአቅማቸውን ማድረግ ይጀምራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ልዩ የካንሰር ህክምና ማዕከል እንደ ማዕከል የገጠመው ችግርም ነበር። ማዕከሉ ያለበት አካባቢ ያሉ የውሃ መፍሰሻ ቱቦዎች ተደፍኖ አካባቢው ለሌላ በሽታ መነሻ በሆኑ ምክንያቶች ተሞልቶ ነበር። እናም ካሌብ የአካባቢው ነዋሪም ሆነ እነዚህ ህመምተኞች ለተጨማሪ ችግር መዳረግ የለባቸውም በሚል አካባቢውን ማጽዳት ይጀምራል። ችግሩ ግን ቀላል አልነበረም ቆሻሻው ለአመታት የተከመረ በመሆኑ ብዙ ቢፈትናቸውም በበርካታ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እርዳታ አንድ መቶ ስልሳ ሦስት ማዳበሪያ ቆሻሻ ከአካባቢው በማስነሳት ሰፈሩን ጽዱ ማድረግ ችለዋል።
ካሌብ እነዚህን ማህበራዊ ኃላፊነቶች እየተወጣም በተጓዳኝ በአካባቢው የሚኖሩ ወጣቶች በአልባሌ ሁኔታ የሚያሳልፉትን ሰዓት መታደግ እንዳለበት ይወስናል። ለዚህ ደግሞ ቀዳሚ መዳረሻው ያደረገው በቁማር በጫትና በመጠጥ የሚጠፋውን ጊዜ በመጽሐፍ ማንበብ መቀነስን ነው። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ካሌብ ወጣቶቹን መጽሐፍ ማስነበብ የጀመረው በአንድ ወገን ከሱስና በአልባሌ እንቅስቃሴ የሚያጠፉትን ጊዜ መታደግ ይቻላል። ከሚያነቡት መጽሐፍ በመነሳት ራሳቸውንም አገራቸውንም ይቀይራሉ። ብሎም ለራሳቸው፤ ለቤተሰባቸው፤ ለማህበረሰባቸውና ለአገራቸው ያላቸው የተሳሳተ እሳቤ መስመር ይይዛል በሚል ነበር። እናም ታናሽ እህቱ ጥሩ አንባቢ ስለነበረችና ብዙ መጽሐፍ ስለሰበሰበች እነሱን በመጠቀም የመንገድ ዳር ቤተ መጻሕፍቱን ይጀምራል።
በሰፈር ውስጥም ምንም ዓይነት እንደ ልደት ምርቃትና ለቅሶ ቤትን ያሉ ዝግጅቶች ከተከናወኑ ካሌብ ስጦታ ብሎ የሚያበረክተው መጽሐፍና የሞባይል ካርድ ብቻ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ሰው ከመረጃ መራቅ የለበትም በሚል ነበር። በዚህ ዓይነት የጀመረው ወጣቶችን መጻሕፍት የማስጠቀም ሥራ በአካባቢው ነዋሪ በተለይም በወጣቶች ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘቱ ዛሬ በጎዳና ዳር ከሁለት ሺ በላይ መጻሕፍቶች ያሉበት ቤተ መጻሕፍት ባለቤት አድርጎታል። መጻሕፍቶቹ ለማንኛውም ተገልጋይ በውሰትም እዚያው ለማንበብም የሚሰጡት በነፃ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ አንባቢ ተውሶ ወስዶም ሆነ እዚያው ቁጭ ብሎ ካነበበው መጽሐፍ ያስደነቀውን የገረመውም ብቻ ይሄን አገኘሁ የሚለውን በአንዲት ገጽ ወረቀት እንዲያሰፍር ይጠየቃል።
የሚያሰፍረው ነገርም በውድድር ሽልማት የሚያሰጥ ነው። በተጨማሪ እቤት ድረስ መጽሐፍ ለሚፈልጉና በንግድ ሱቆች ለሚሠሩም እነ ካሌብ ባሉበት በነጻ ያደርሳሉ። በቅርቡም አንድ አንድ የስነ ጽሁፍ ባለሙያ በየወሩ በመጋበዝ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ለማዘጋጀት በሂደት ላይ ይገኛል። ለዚህም እስካሁን ስድስት ደራሲያን ፈቃደኛ ሆነው መጀመሩን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። የሥነ ጽሑፍ ማህበራትም የሚሳተፉበት ሁኔታ እየተመቻቸ ሲሆን መርካቶ ካለ ወዳጁ ጋር በመሆንም መቶ የሚደርሱ መጽሐፍ ወስዶ አንድ ተመሳሳይ ቤተ መጽሐፍት ሥራ አስጀምሯል።
ካሌብ ይህን ሥራ በጀመረ በአመቱ ዓለምን ለከፋ ችግር የዳረገው የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት ካሌብና ጓደኞቹ ለአካባቢው ኃላፊነት በመውሰድ ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ይጀምራሉ። አካባቢን ከማጽዳት ጀምሮ ሰፈርተኛውንም ሆነ ወደ መንደሩ የሚገባ የሚወጣውን ሰው ደከመን ሰለቸኝ ሳይሉ ሙሉ ቀን እጅ ሲያስታጥቡ ይውሉ ነበር። ውሎ እያደረ ሥራ እየተቀዛቀዘ ሲመጣና ሰዎች ለእለት ጉርስ የሚሆን ነገር እየቸገራቸው ሲመጡ ደግሞ እነሱን ወደ መደገፉ ይሸጋገራሉ። በወቅቱም ስልሳ ለሚደርሱ አረጋውያንና ችግርተኞች አስቤዛ ማቅረብ ችለዋል። የኮሮና ወረርሽኝን ለመታደግ የሰራው ሥራ ካሌብ ካገኛቸው በርካታ ሽልማቶች መካከል በልደታ ክፍለ ከተማ ሦስተኛ በመውጣት ያሸለመውም ነበር።
ከዚሁ ሁሉ ሥራ በተጓዳኝ እነ ካሌብ በሰፈራቸው አቶ እከሌ፤ ወይዘሪት እከሊት ታመሙ ደከሙ ሲባል በአቅማቸው ቀዳሚ ደራሽ ናቸው። ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ዛሬም ድረስ በየወሩ የሚደግፏቸውም አሉ። የአረጋውያን ድጋፉ በእነ ካሌብ እይታ የተለየ መስመር አለው። መጀመሪያ አረጋውያኑ ለአገር ለሕዝብ ውለታ የሠሩ ናቸው። በመሆኑም ልናከብራቸው ይገባል። ካስተዋልን ደግሞ አሁንም በርካታ እውቀትና ልምድ ሊያካፍሉን ይችላሉ። በመሆኑም እነዚህን አረጋውያን መደገፍና መንከባከብ የሰብአዊነት ግዴታችን ሊሆን ይገባል ይላል።
ምንም እንኳን ካሌብ የህክምና ባለሙያ ባይሆንም አብዛኛው በሽታ በወቅቱ ከተደረሰበት ሳይጠና በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል ግንዛቤ አለው። በመሆኑም ሌሎች ከፍተኛ ሞያና ትልልቅ የላብራቶሪ መሣሪያ ሳይፈልጉ የሚደረጉ ቀላል ምርመራዎችን ለመጀመር እየሠራ ይገኛል። በመንገድ ዳር ላይ ባቋቋማት ቤተመጻሕፍት ውስጥ በተደራቢነት የደም ግፊት መመርመሪያ ሚዛን በማዘጋጀት ኅብረተሰቡ በነፃ እንዲጠቀም መሣሪያውን ቃል የገባለት ሰው ያለ ሲሆን በቅርቡ ሁሉንም አጠናቆ ሥራውን እንደሚጀምር ይናገራል።
ካሌብ ወጣቶችን ከመውቀስ ካሉበት ሁኔታ እንዲወጡ ለመታደግ ደጋፊ ተባባሪ መሆን ይጠበቃል። ሀሜትና እንዲህ አድርግ ብሎ መምከር ብቻውን በቂ አይደለም። መንገዱን ማሳየት በአቅም መደገፍ ይጠበቃል። እኔ የማውቃቸው ብዙ ልጆች ዋስ በማጣት ብቻ ሥራ ፈት የሆኑ አሉ። እነዚህን ዱርዬ እያሉ ከማማት መስዋእትነት ከፍሎ ዋስ በመሆን ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቃል ይላል። ከፖሊስ ኮሚኒቲና ከወረዳ ጋር በመገናኘት በቢጂ አይ ኢትዮጵያ ከአስራ አምስት በላይ ልጆች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ማድረግ ችሏል። በቀጣይም ሌሎችን ለመታደግ ሥራ በማስቀጠር ብቻ ሳይሆን ስልጠና ለማስጠትም እንደሚሠራም ይናገራል። ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ካደረገው የመጽሐፍ ድጋፍ በተጓዳኝ በግል ትምህርት ቤት አራት ልጆች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙም አድርጓል።
ማስታረቅ ሰላም መፍጠር መደጋገፍና መተባበር ሠርቶ መኖር በማህበረሰቡ በተለይም በወጣቱ ውስጥ መስረጽ አለበት የሚለው ካሌብ ከባህላችን ጋር መጋፋት አለብን አልያስ እየኖረ ነው ያለውን የስህተት መንገድ ተቀብለን መቀጠል አለብን የሚለው ግራ ያጋባኛል። ይህን የሚያስብለኝ ደግሞ እንደ ባህል እየተስፋፋ ያለው ልመና ነው ይላል። ካለበቂ ምክንያት የሚደረግ ልመናን በጽኑ እቃወማለሁ የሚለው ካሌብ ይህን ያስባለውን በሚሠራበት አካበቢ የገጠመው ነገር እንደሚከተለው ይተርካል። ጠዋት ሥራ ወጥተው እስከ ስድስት ሰዓት ለምነው እስከ አምስት መቶና ስድስት መቶ ብር ይዘው ዝርዝሩን ለመድፈን የሚመጡ ሰዎችን በየቀኑ አገኛለሁ።
ሙሉ አካል ያላቸው ሠርተው መብላት የሚችሉ ናቸው። በአንጻሩ የመንግሥት ሠራተኛ ሆነው እኔን ብድር የሚጠይቁ ደመወዛቸው ከቤት ኪራይ ብዙም የማይተርፋቸውም ሰዎች አውቃለሁ። በመሆኑም ማን መረዳት አለበት፣ ምን መረዳት አለበት የሚለውን መለየት አለብን። ካልሆነ ሥራ ፈትነትንና ልመናን አንዳንዴም ወንጀልን የምናስፋፋው ራሳችን እንሆናለን ይላል። ካሌብ ሥራውን ከጀመረ አንስቶ በርካታ ሽልማቶችንም ያገኘ ሲሆን በቅርቡም ደራሲ ዶክተር እንዳለ ጌታ ከበደ ሦስት መቶ መጻሕፍቶችን አበርክተውለታል። «ሰው ክቡር ነው» በሚል ስያሜ ሕጋዊ ማህበር ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰም ሲሆን ፈቃዱን ካገኘ በኋላ ዘርፈ ብዙ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን እንደሚያከናውን ይናገራል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2014