አልቢትር ባምላክ ተሰማ ከአፍሪካ ዋንጫው መልስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቀባበል ተደርጎለታል። ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ዳኞች በትልልቅ መድረኮች የሚታዩበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ አልቢትሩ ተናግሯል።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች በዋና በዳኝነት ከተሳተፉ ባለሙያዎች መካከል ኢትዮጵያዊው አልቢትር ባምላክ ተሰማ አድናቆትን ማትረፉ የሚታወቅ ነው። ባምላክ በተደረገለት አቀባበል ስነስርዓት ላይ ለቀጣይ ከባድ የቤት ስራ እንደሆነው በማንሳት፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዳኞችም በትልልቅ መድረኮች የሚታዩበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት አመላክቷል። በተለይም የካፍ የምርጫ መስፈርት ሰፊ እና ዳኝነቱም በቴክኖሎጂ እየታገዘ የሚገኝ በመሆኑ ዳኞች ከዘመኑ ጋር እንዲራመዱ የቪኤአር ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ መጀመር እንደሚገባው መጠቆሙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረገጹ አስነብቧል።
ካሜሮን ባስተናገደችው የአህጉሩ ታላቅ የእግር ኳስ ውድድር ኢንስትራክተር ባምላክ በዳኝነት ሀገሩን ያኮራ አቋም አሳይቶ መመለሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደማቅ አቀባበል አድርጎለታል። በመርሃ ግብሩም ላይ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የዳኞች ኮሚቴ አባላትና ኢንስትራክተሮች ተገኝተዋል።
ባምላክ በአቀባበሉ ክብር እንደተሰማውም ገልጿል። በንግግሩም ‹‹የስኬቴ ዋናው ምስጢር በዙሪያዬ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ናቸው። በተለይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከታች ጀምሮ አሁን እስካለሁበት ደረጃ አግዞኛል። ጽህፈት ቤቱም የመለማመጃ ሜዳ ከመፍቀድ ጀምሮ ሞራል በመስጠት፣ የዳኞች ኮሚቴ እና አሰልጣኞቼም አይዞህ በማለት አበረታተውኛል›› ሲል ተናግሯል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2014