በዓለም ዙሪያ 90 በሚሆኑ ሃገራት 120 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የቦውሊንግ ስፖርትን ያዘወትራሉ። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ተዘውታሪነቱ አነስተኛ ሊባል የሚችል ነው። ይሁንና ቦሊውንግ በሃገሪቷ እንደ እግር ኳስና አትሌቲከስ ስፖርቶች ሁሉ ረጅም ጊዜ ቆይታ አለው። በኢትዮጵያ ከ1952ዓ.ም ጀምሮ የቦውሊንግ ስፖርት ይዘወተር የነበረ ሲሆን፤ ኤርትራን ጨምሮ በአራት የተለያዩ የሃገሪቷ ውስጥ ማዘውተሪያዎችም ነበሩ። እነርሱም ሪቼ(እምቧይ መስክ)፣ ገነት ሆቴል፣ መኮንኖች ክበብ እና በቀድሞ የኤርትራ ግዛት መሆናቸውን በኢትዮጵያ ቦውሊንግ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ምኒሊክ ሃብቱ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የቦውሊንግ ፌዴሬሽን አባል እንዲሁም የአፍሪካ ቦውሊንግ ፌዴሬሽን መስራችና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናት። ለ37 ጊዜያትም ኢትዮጵያ በዚህ ስፖርት ዓለም ዋንጫ ስትካፈል፤ በአፍሪካ ቻምፒዮና ደግሞ በቡድን አሸንፋ የዋንጫ ተሸላሚ እንደነበረችም ፕሬዚዳንቱ ያስታውሳሉ። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን ስፖርቱ መቀዛቀዝ አሳይቷል። ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የስፖርቱ ውድነት ነው። ስፖርቱን ለማከናወን ቤት እና የመጫወቻ ማሽኑ የግድ መኖር ያለበት ሲሆን፤ ይህንንም ለማሟላት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል።
ከቀደሙት የማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል የቀረው ገነት ሆቴል ያለው ብቻ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ዓመታትን ያስቆጠረው በላፍቶ ሞል የሚገኘው ነው። ሪቼ(እምቧይ መስክ) እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ከሲድኒ ኦሊምፒክ መልስ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲገነባበት መደረጉን ተከትሎ ስፖርቱ በማዕከሉ ይጠቃለላል ቢባልም ግንባታው እስካሁን ዕውን ሊሆን አለመቻሉን ፕሬዚዳንቱ ይጠቁማሉ። በተመሳሳይ ቀድሞ የነበረው የክለቦች ቁጥር 20 ቢሆንም አሁን እየሰሩ ያሉት ግን ስምንቱ ብቻ ናቸው።
ስፖርቱ በሌላው ዓለም እጅግ ተዘውታሪ ሲሆን፤ ማህበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር እና በዕድሜ የሚገደብ ባለመሆኑ ተወዳጅ አድርጎታል። በክልሎች እንዲሁም በከፍተኛ የትምህርት ማዕከላት ስፖርቱ እንዲኖር አሶሴሽኑ ጥረት እያደረገ መሆኑን የሚናገሩት ፕሬዘዳንቱ፣ አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች ላይ አሶሴሽኖች እንዲቋቋሙ መደረጉን አስረድተዋል። የማዘውተሪያ ስፍራዎችንም በጥቂቱ ጀምረው እንዲገነቡ ከማድረግ ባለፈ፤ ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽንም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥረት እየተደረገም ይገኛል።
ከዚህ ባለፈ ስፖርቱን ለማጠናከር በታዳጊዎች ላይ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ በየዓመቱ እስከ 60 የሚደርሱ ታዳጊዎችን ለማሰልጠን አሶሴሽኑ እቅድ ይዟል። ከ9 ዓመት ጀምሮ ወደ ስፖርቱ መግባት የሚቻል በመሆኑ፤ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (የትጥቅና ሌሎች ድጋፎችን ይሰጣል) እና ከዓለም አቀፉ ቦውሊንግ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ስልጠናውን በላፍቶ ሞል (ቦረላማር ቪንቴጅ) እንዲሁም በገነት ሆቴል ተጀምሯል። እስከ መጋቢት 24 በሚዘልቀው ስልጠና ላይም በንድፈ ሃሳብ እንዲሁም በተግባር የታገዘ ስልጠና ይሰጣል። ታዳጊዎቹ ወደ ስፖርት ከገቡም በኋላ እንዳይበተኑ ክለቦች ላይ አስገዳጅ የሆነ ደንብ እንዲኖር ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ክለቦች አደረጃጀታቸውን እንዲያስተካክሉ እየተሰራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2014