ባለፈው እሁድ የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ለ11ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የሬዲዮ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። በአገራችንም በእዚሁ ቀን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና ሌሎች የግልና የመንግሥት የሬዲዮ የመገናኛ ብዙኃን በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል ተከብሯል፡፡ በዓሉ በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለአንጋፋ ጋዜጠኞች እውቅናና የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡
በእንዲህ አይነት መድረክ ተገኝቶ ስለሬዲዮ መነጋገር መልካም ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ብዙዎችም ትዝታቸውን አጋርተዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን ስለዚህ መድረክ አይደለም፤ ስለአጠቃላይ የሬዲዮ ጉዳይ የታዘብኩትን መግለጽ ነውና ወደዚያው ልግባ፡፡
ይህን የሬዲዮ ቀን አስመልክቶ በርካታ የሬዲዮ ጣቢያዎች አውርተዋል፣ ጋዜጠኞች በማኅበራዊ ገጾቻቸው ጽፈዋል፡፡ ከሁሉም የታዘብኩት ግን ሬዲዮ አሁን ስላለበት እና በቀጣይ መሆን ስለሚገባው ሁኔታ አለማውራታቸውን ነው፤ ትዝታ ብቻ የተነሳው፡፡
ትዝታ ምን ያህል ስሜትን እንደሚቀሰቅስ ጠፍቶኝ አይደለም፤ እኔም ብዙ የሬዲዮ ትዝታ አለኝ፡፡ ትዝታው ይሁን፤ ከእሱ ጋር ተያይዞ ሬዲዮ አሁን ያለበትንና ወደፊት መሆን ስላለበት መታዘብም ይገባ ነበር፡፡ ወይስ ሬዲዮ እንደ ሙዚዬም ቅርስ ትዝታ ብቻ ሆኖ ይቅር?
ሬዲዮ ከመገናኛ ብዙኃን አይነቶች ሁሉ ቀላል (በዋጋም በአያያዝም፣ ተደራሽ እና ምቹ የሚባል የመገናኛ አይነት ነው፡፡ አሁን ደግሞ በየኪሳችን ያለ/ ነው፡፡ የአጠቃቀም ምቹነቱ፣ ድንበር አልባ ስርጭቱ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ተደራሽነቱ፣ ምስል ከሳችነቱ ባህሪዎቹ ናቸው፡፡ ንፅፅሩ ከጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ከቴሌቪዥን እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሥር ከሚጠቃለሉት የማኅበራዊ ትስስር መገናኛ ዘዴዎች ጋር ነው፡፡ ሁሉም የሬዲዮን ያህል አይሆኑም፡፡ ‹‹ለምን?›› የሚለውን ልብ እንበል!
ከአገራችን የገጠሩ ማኅበረሰብ አብዛኛው አሁንም ያልተማረ ብል ስህተት አይሆንም፡፡ ጋዜጦችና መጽሔቶችን አያነብም፣ ማንበብና መጻፍ ቢችል እንኳ ጋዜጣ የሚያነብበት ጊዜ ብዙም የለም፡፡ ሬዲዮ ግን የትኛውንም ሥራ እየሠሩ ለማድመጥ ይመቻል፡፡ አርሶ አደሩ የግብርና ሥራውን እየሠራ ያዳምጣል፡፡
አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ በቤቱ ውስጥ ቴሌቪዥን ሊኖረው ይችል ይሆናል፤ ለሥራ ቦታው ግን የሚጠቀመው ሬዲዮ ነው፤ በዚያ ላይ በሁሉም የአገራችን ክፍል መብራት የተሟላ አይደለም፡፡ ሬዲዮ ግን በባትሪ ድንጋይና በፀሐይ ኃይል (ሶላር) ይሠራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄው ታሳቢ ተደርጎ ይመስላል በሶላር የሚሰሩ የሬዲዮ አይነቶች መጥተዋል፡፡
ነጋዴውም እንደዚያው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬም ድረስ ሱቅ ውስጥ ቴሌቪዥን ሳይሆን ሬዲዮ ተከፍቶ የምንሰማው። በተሸከርካሪዎችም ውስጥ እንደዚያው ነው፡፡ በመሥሪያ ቤቶችም ቢሆን በጆሮ ማዳመጫ ሬዲዮ እያዳመጡ የሚሠሩ ብዙ ናቸው፡፡
የቴክኖሎጂ መገናኛ ዘዴዎች (ማኅበራዊ ገጾች) ከሞባይል ስልክ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ገጠር ድረስ እየዘለቁ ቢሆንም፣ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ያላቸው ተደራሽነት ብዙ ይቀረዋል። ጋዜጣ፣ መጽሔት እና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተማረ የሚባለው የከተሜው ማኅበረሰብ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን አዲስ አበባ ውስጥም ቢሆን፣ ሬዲዮ ብቻ የሚጠቀመው የማኅበረሰብ ክፍል ቀላል አይደለም፡፡ በታክሲዎችና በግል የቤት መኪናዎች ውስጥም ሬዲዮ በባህሪው ቀላልና ምቹ ነው፤ በተማረውም ባልተማረውም የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ይደመጣል፡፡
እነዚህን ከላይ የዘረዘርኳቸውን የሬዲዮ ባህሪያት መጥቀስ የፈለኩበት ምክንያት የሬዲዮን የአስፈላጊነት መጠን ለማሳየት ነው፡፡ አስፈላጊነቱን ይህን ያህል ካየን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከሬዲዮ ጣቢያዎች የታዘብኩትን ላካፍል፡፡
የሬዲዮ ጣቢያዎች በተለያየ አካባቢ የማሰራጫ አንቴና ቢኖራቸውም ዋና ስቱዲዮ የሚኖረው ከተማ ላይ ነው፡፡ ከጥቂት የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በስተቀር አብዛኞቹም አዲስ አበባና የክልል ከተሞች ውስጥ ነው ያሉት ፡፡
እነዚህ ከተማ ውስጥ ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች ገጠር ውስጥ ላለው ማኅበረሰብ የሚያደርሱት መረጃ ፈጣንና ለዚያ ማኅበረሰብ ብዙም አስፈላጊና ምቹ አይደለም፡፡ ይህን በሰፊው የታዘብኩት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ገና አፍላ በነበረበት በ2012 ዓ.ም መጋቢት፣ ሚያዚያና ግንቦት ወራት ውስጥ ነው፡፡ በእነዚህ ወራት ቤት መዋል የግድ ነበር፡፡ በእነዚያ ጊዜያት የሬዲዮ ጣቢያዎች የሬዲዮን ሳይንሳዊ ባህሪ እንዳልተጠቀሙበት ታዝቤያለሁ፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በማኅበራዊ ገጻቸው ትኩስ ትኩስ መረጃዎችን ይለቁ ነበር፡፡ እኔ አዲስ አበባ እንደመኖሬና የቴክኖሎጂውም ተጠቃሚ እንደመሆኔ ይህን መረጃ ወዲያውኑ አገኘው ነበር፡፡ መረጃውን ግን የሬዲዮ ጣቢያዎችን እያቀያየርኩ ብሞክርም አላዩም አልሰሙም። በሙዚቃ ላይ ሙዚቃ እየደራረቡ መቆየት ነው፤ከዚያ ወደ መደበኛ ፕሮግራሞች መሸጋገር ነው፡፡ ከብዙ ሰዓታት ቆይታ በኋላ (በመሐል ብዙ ነገር ተፈጥሮ) የጠዋቱን መረጃ ሲናገሩ ነበር የምሰማቸው፡፡
በሬዲዮ ሰበር ዜና መስማት ቀርቷል፡፡ የሚገርመው ግን ከቴሌቪዥን በተሻለ ሁኔታ ፈጣኑ ሬዲዮ ነበር፡፡ ቴሌቪዥን ብዙ ጣጣ አለበት፤ ሬዲዮ ግን ቀጥታ ስቴዲዮ ገብቶ ማውራት ነው፡፡ ዋናው ነገር የክስተቱን እውነትነት ማረጋገጥ ነው። ሲሆን የምናየው ግን ቴሌቪዥኑን መቅደም የነበረበት መገናኛ ብዙኃን ተቀድሞ መገኘቱን ነው፡፡ ቴሌቪዥንና ጋዜጣ የዘገቡትን ዜና እንኳ ቶሎ ሲዘገቡ አልተሰሙም፡፡ አሁንማ የትዝብቴን እውነትነት ለማረጋገጥ ብዬ ቴሌቪዥን ላይ ሰበር ዜና ሳይ ወዲያው የሬዲዮ ጣቢያዎችን እከፍታለሁ፤ ያንንም ያንንም እሞክራለሁ፤ አብዛኞቹ ምን እንደተፈጠረ ያልሰሙ ሆነው ነው የማገኛቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት (በዚያው በኮሮና አፍላነት ወቅት) በማኅበራዊ ገጼ ላይ ትዝብቴን ጽፌ የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ የሰጠኝን አስተያየት አስታውሳለሁ፡፡ በተለይም የግል የሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሲያወጡ ትኩረታቸው መዝናኛ ላይ ነው፤ በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ ፈቃድ የሚያገኙት እንቶ ፈንቶ ነገሮች ላይ የሚያተኩር ፕሮፖዛል ካቀረቡ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ምናልባትም ከጥቂቶች በስተቀር ፈጣን መረጃዎችንና ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን አይሰሩም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የንግድ ጣቢያዎች ስለሆኑ የአየር ሰዓቶቻቸው ለተባባሪ አካላት የተሸጡ ናቸው፡፡ የአየር ሰዓቱን የገዛው አካል (ግለሰብም ይሁን ተቋም) የራሱን ፕሮግራም ብቻ ያስተላልፍበታል እንጂ ዜና አይሰራም፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የሬዲዮ ተፈጥሯዊ(ሰው ሰራሽ ቢሆንም ሳይንሳዊ ባህሪውን ማለቴ ነው) ባህሪ በትክክል እንዳይሰራበት ሆኗል፡፡
ሌላው የታዘብኩት ነገር ደግሞ ማታ ማታ ዜናዎቻቸውን ስሰማ ነው፡፡ አብዛኞቹ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ተደራሻቸው የአዲስ አበባ ሕዝብ ነው፡፡ መስማት የሚፈልገው ለየት ያለ ዜና ነው፡፡ የሚገርመው ግን በተመሳሳይ ሰዓት ጣቢያ ብንቀያይር የምንሰማው ያንኑ አንዱን ዜና ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ተቋም በማኅበራዊ ገጹ የለቀቀውን መረጃ መዘርዘር ነው፡፡ አብዛኛቹ በቃለ መጠይቅ የሚሰራ /የፕሮጀክት/ ዜና የላቸውም፤ ሰርተው ከሆነም ጉዳይ መረጣ ላይ ጠንካራ አይሆኑም፡፡
ጠዋት የተለቀቀን ዜና ማታ እንደ አዲስ ያቀርቡታል፡፡ የግድ የዜና ሰዓታቸው ማታ ስለሆነ ብቻ የተሰለቸ ዜና ማቅረብ አልነበረባቸውም፤ እሴት መጨመር የሚባል ነገር የላቸውም፤ እሴት ያልተጨመረበት ሲነገር የዋለ መረጃ ለአዲስ አበባ ነዋሪ አይጠቅምም፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ መረጃዎቹን ከተለያዩ ምንጮች ሊያገኛቸው ይችላልና፡፡
ሬዲዮ ታስቦበትና ታቅዶ ሊሰራበት ይገባል፡፡ እቅድ ላይ ተመስርቶ ዜናዎችን መሥራት፣ መተንተን ያስፈልጋል፤ ሬዲዮ ጣቢያዎች እንደ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የራሳቸው የፕሮጀክት ዜናዎች ሊኖሯቸው ይገባል፡፡ ይህን የሚያደርጉት በጣም ጥቂት የሬዲዮ ጣቢያዎች ብቻ ናቸው፤ እነሱም በአብዛኛው ከቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር የተሳሰሩት ይመስሉኛል፤ እናም በሬዲዮ ላይ እየተሠራበት አይደለም፤ የሬዲዮ ጣቢያዎች እየበዙ መምጣት የሬዲዮ ባህሪን የተላበሱ የሬዲዮ ጣቢያዎችም እየጨመሩ እንዲመጡ ማድረግ መቻል ነበረበት። ይህ ሊስተካከል ይገባል፡፡ ፕሮጀክት ቀርጸው የራሳቸውን ሥራ የሚሰሩ ሬዲዮ ጣቢያዎች ተወዳጅ ሆነዋል፡፡ ሌሎችም እነሱም መከተል አለባቸው፡፡ ተደማጭነት ላይ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡
ስለዚህ የሬዲያ ጣቢያዎቻችን የሬዲዮን ባህሪ የሚመጥን ሥራ ይሥሩልን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2014