የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደ ተቋም ወደ ፊት በመሄድ የሚያጠቃ ብሔራዊ ቡድን እንደሚፈልግ ለዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ መግለጻቸውን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ረዳቶቻቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሳምንት በፊት በተጠናቀቀው በ33ኛው የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ቆይታቸውን በተመለከተ ከትናንት በስቲያ በድሬዳዋ ለቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስራ ስድስቱ የክለብ አሰልጣኞች ገለጻ አድርገዋል።
አሰልጣኙ ገለጻውን ባደረጉበት መርሃግብር ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንደ ፕሬዚዳንት ከራስ ሜዳ በሰከንድ ውስጥ ኳስ ተቀባብሎ በተጋጣሚ ሜዳ የሚጫወት ቡድን እንደሚፈለግ ለአሰልጣኝ ውበቱ በግምገማ ወቅት መግለጻቸውን አስረድተዋል።
«ስለተጫዋች ምርጫ፣ ስለ ተጫዋቾች አሰላለፍ ሥራዬ ስላልሆነ ከአሰልጣኙ ጋር አውርቼ አላውቅም፣ ማውራትም አልፈልግም» ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ሊሠራ የሚገባውን ሁሉ ግብ አስቀምጦ ወደ ካሜሩን ቡድኑ እንደተጓዘ ማብራራታቸውን የሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል።
በቀጣይ ወር ውስጥ ብሔራዊ ቡድኑ ከሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ ጀምሮ ቡድኑ ፍሰት ያለው ጨዋታ እንደሚጫወት የጠቆሙት አቶ ኢሳያስ፣ በግምገማው ወቅት ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆና ተከላካዮቹ ያሬድ ባዬ እንዲሁም አስቻለው ታመነ ኳስን ወደ ራስ ግብ ክልል በመመለስ ሲጫወቱ ማየት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ ግን የቴክኒክ ጉዳይ በመሆኑ ለባለሙያ መተው እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ያምሆኖ ተከላካዮች በተጋጣሚ ሜዳ ላይ እንጂ በራስ ሜዳ አደገኛ ክልል ውስጥ የኢትዮጵያ
ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ኳስ ይዘው ሲጫወቱ በማየት መሳቀቅ እንደማይፈልጉ አስረግጠው ተናግረዋል። ለዚህም ቡድኑ መጫወት ባለበት አግባብ መጫወት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ፣ እቅዱ እግር ኳስ ስለሆነ በቡድኑ ውስጥ ወደ ፊት የሚጫወት ተጫዋች ያስፈልጋል። በዚህ ዙሪያ የፕሪሚየርሊጉ አሰልጣኞችም እንደሚስማሙ ያስባሉ።
ከካሜሩን ጋር በነበረው ሁለተኛው የምድብ ጨዋታ በመጀመሪያው አርባ አምስት የጨዋታ ጊዜ ቡድኑ እንዴት ጥሩ ተንቀሳቀሰ የሚለውን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ሊሠራበት እንደሚገባም አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል። የቡድኑን ጥንካሬ እንዴት ወደ ሊጋችን አውርደን እናምጣው የሚለው ጉዳይም የሁሉም የቤት ሥራ መሆኑን ለፕሪሚየርሊጉ አሰልጣኞች አስገንዝበዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከአፍሪካ ዋንጫው መልስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቡድኑ አንዱ ደካማ ጎን አድርገው የተናገሩት የሊጉን ደካማነት ነው፤ ይህ አስተያየት ደግሞ በሊግ ኩባንያው ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ተቀባይነት አለማግኘቱይታወቃል። ይህንን በተመለከተም አቶ ኢሳያስ «ድክመቱ የሁላችንም ነው» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል። በዚህም መስራት የሚገባውን ነገር ከድክመቶች ተነስቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሁሉንም ነገር ከብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መጠበቅ እንደማያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ኢሳያስ፣ ድክመቱ የሁሉም እንደመሆኑ በጋራ መስራቱ የተሻለ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ያደረጋቸው ጨዋታዎች እንደጠቀሙትና ጥሩ እንደተንቀሳቀሰ ያስታወሱት አቶ ኢሳያስ፣ እንደ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያው የአፍሪካ ዋንጫው ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ አለመቻሉንም አያይዘው አስታውቀዋል። ይህ እንደተገመገመም ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት ግን አሰልጣኝ ውበቱ ይሰናበት፣ ኢሳያስም ከኃላፊነት ይነሳ የሚሉ ዘገባዎችን መስራት ስህተት መሆኑን በማስረዳት ፌዴሬሽኑ የሚመራው በሥርዓት እንደሆነ አብራርተዋል።
«የሚያስፈልገውና ዋናው ነገር ውይይት የተደረገባቸውን ጉዳዮች ተጫዋቾችና ድክመቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ነው፣ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ከየትም አይመጣም፤ ከክለቦች እንጂ፤ ስለዚህ ክለቦች መቶ በመቶ ብቁ ተጫዋቾችን መላክ ባይችሉ እንኳን አሻሽሎ ማቅረብ ያስፈልጋል፣ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በዘጠኝ ቀን የማቀናጀት ሥራ እንጂ ብዙ ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይታሰብም» ያሉት አቶ ኢሳያስ፣ እንደ ፌዴሬሽን ከምድብ የማለፍ ግብ አስቀምጦ ማድረግ አለመቻሉ እንደሚያስቆጭ ተናግረዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2014