አዲስ አበባ (ኢ.ዜ.አ) በወሎ ጠቅላይ ግዛት በዝናብ እጦት የተነሳ ድርቅ ባስከተለው ችግር ጉዳት የደረሰበትን ሕዝብ ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም የሚደረገው የርዳታ አሰጣጥና የሥራ ዘመቻ በሠፊው በመካሄድ ላይ መሆኑን ክቡር ደጃዝማች ለገሠ በዙ የወሎ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ በቅርቡ ወደ ጠቅላይ ግዛቱ ተልከው ለነበሩት ለአገር ውስጥና ለውጪ አገር የሬዲዮና የጋዜጣ ወኪሎች ገለጹ፡፡
ደጃዝማች በቅርቡ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ተገኝተው ድርቅ የደረሰባቸውን ቀበሌዎች በጐበኙበት ወቅት፤ መሬት ላጣው መሬት፣ የእርሻ በሬ ላጣው በሬ፣ መቋቋሚያ ለሚያስፈልገው ተገቢው ርዳታ እንዲሰጠው ባደረጉት አዋጅ መሠረት፤ የበልጉ ጊዜ ሳይተላለፍ ዓዋጁን በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ጨምረው ገልጠዋል፡፡
ከዚህም ሌላ በድርቅ ምክንያት ከነበረበት ቀበሌ ዕቃውን ሸጦ ቤቱን አፍርሶ፤ መሬቱን በገንዘብ ለውጦ የተሰደደውን ሕዝብ የሚያስፈልገው ርዳታ ጊዜያዊ አለመሆኑን፤ ምናልባትም በዚህ ዓመት የበልግም ሆነ የክረምቱ ዝናብ እንደወትሮው ሆኖ ባይገኝ፤ ችግሩን በይበልጥ ያባብሰዋል ተብሎ በመገመቱ፤ ሕዝቡ ተቋቁሞ ራሱን እስከ ቻለ ድረስ በአቅራቢያው ከተሠራለትና ወደፊት ከሚሠራለት የርዳታ መስጫ ጣቢያ እየቀረበ እህል እንዲታደለው ታቅዷል፡፡
እስካሁንም ቁጥር ፭፻፲፫ ሺህ ፭፻፵፬ የሆነ ሕዝብ እህል የበሰለ ምግብ፤ የሕክምና የልብስና ሌላም ይህን የመሳሰሉ ርዳታ ማግኘቱን ከክቡር እንደራሴው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በጠቅላይ ግዛቱ ላይ በደረሰው የእህል እጥረት ምክንያት፤ ተጐድቷል የተባለው ሕዝብ በጠቅላላ በቁጥር ፱፻ሺህ ስለሆነ፤ በየወሩ ፺፬ ሺህ ፭፻ ኵንታል እህል የሚያስፈልግ መሆኑ ተገምቷል፡፡
በተጨማሪም መሥራት የሚችለውን ሁሉም ‹‹ምግብ ለሥራ›› በተባለ ፕሮግራም አማካይነት መጋቢ መንገዶችን በመሥራት፤ የዛፍ ችግኞችን በመትከልና በሌሎችም ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች እንዲሳተፉ በመደረግ ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በአውሳ በአምባሰል በየጁ በደሴና በቆቦ አውራጃዎች የመንገዱ ሥራ ተጀምሮ ለብዙ ሰዎች ሥራ የፈጠረ መሆኑን ክቡር እንደራሴው ገልጠዋል፡፡
ጥር ፴ ቀን ፲፱፻፷፮
የወሎ ገበሬዎችን ለመርዳት የእርሻ ወኪሎች ኮርስ ተጀመረ
በወሎ ጠቅላይ ግዛት የሚገኙ ገበሬዎችን በማዳበሪያና በብድር አሰጣጥ፤ በጠቅላላው በእርሻ ዘዴ አገልግሎት ለመርዳት የሚያስችል ፷ የገበያ አገልግሎትና ረዳት የእርሻ ወኪሎች ተካፋይ የሆኑበት ኮርስ ተጀመረ፡፡
ኮርሱ በመካሔድ ላይ የሚገኘው በጭላሎና በባኮ የእርሻ ማሠልጠኛ ት/ቤቶች ሲሆን፤ ከተካፋዮቹ መካከል ፴ዎቹ ረዳት ሲሆኑ ፴ዎቹ ደግሞ የገበያ ክፍል ሠራተኞች ናቸው፡፡
የተጠቀሱት ሞያተኞች ኮርሱን የሚከታተሉት ለሁለት ወራት መሆኑን የእርሻ ሚኒስቴር ማስታወቂያ ክፍል ገለጡ፡፡ የጥናቱ ጊዜ እንዳበቃ ፷ዎቹም ወጣቶች በወሎ ጠቅላይ ግዛት በየምድብ ሞያቸው ተሠማርተው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይህም ኮርስ በወሎ ጠቅላይ ግዛት በድርቅ ምክንያት ችግር የደረሰበት ገበሬ በእርሻው ሥራ ላይ ተቋቁሞ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት በተባሉት ሠራተኞች አማካይነት የግብርና ሥራውን ለማካሄድ እንደሚያስችለው ተረጋግጧል፡፡
(ጥር ፲ ቀን፲፱፻፷፮ ዓ.ም )
ዶክተሩ ዓባይን ሲያቋርጥ አዞ ጀልባውን ነጠቀው
ዶክተር ቮልትስ አንጆር የተባለ ስዊዛዊ፤ ዓባይን እየቀዘፈ ለማቋረጥ ሲሞክር፤፫፻ኪሎ ሜትር እንደሄደ፤ ጀልባውን አዞዎች ስለሰነጠቁት ጉዞውን አቋርጦ የተመለሰ መሆኑ ገልጧል፡፡
ዶክተሩ ጉዞውን ከሞጣ ተነስቶ ወደ ዓባይ ድልድይ ሲጓዝ ፪፻፶ ኪሎ ሜትር ላይ ፲፬ ወንዞች የሚገናኙበት በአዞ የተወረረ ቦታ ደረሰ፡፡ ከዚያም ሊተናኮሉት በሰልፍ የሚጠጉትን አዞዎች በሽጉጥ እየተከላከለ በጥድፊያ ወደ ውሃው ዳርቻ ለማምለጥ ሲሞክር አንዱ መቅዘፊያ ተሰበረበት፡፡
መቅዘፊያውንም ከአዲስ አበባ ተላልኮ አስመጥቶ ያቋረጠውን ጉዞ ለመቀጠል ፶ ኪሎ ሜትር እንደተጓዘ፤ እንደገና አዞዎች የጀርባውን ሚዛን መጠበቂያ የአየር ከረጢት ዘንጥለው መቅዘፊያውንም ከእጁ ነጥቀው አስቀሩበት፡፡ ዶ/ር አንዶርም በአንድ መቅዘፊያ እየተጠቀመ ከውሃው ዳር ሲጠጋ በሩቅ ዛፍ ላይ አፉን የከፈተ አዞ ተመልክቶ፤ ፎቶግራፍ ሊያነሳ ሲዘጋጅ ከዛፍ ላይ ወርዶ ከብዙ አዞዎች ጋር ሆኖ ጀልባውን ወረሩት፡፡
ጀልባውን ለማዳን አምስት ጊዜ ተኩሶ ያጎረሰውን ጥይት ጨረሰ፡፡ የቀረው ጥይት በጀልባው ውስጥ ስለሆነ፤ ለማውጣት እንዳይችል አደረጉት፡፡ ሌላውን ዕቃ ትቶ ለጊዜው የያዛትን ትንሽ ማርና ስኳር፤ ድንኳን፤ ካሜራና የለበሰውን ልብስ ብቻ ይዞ ከዳር ሆኖ ጀልባው በአዞዎች ተከቦ ሲዘነጣጠል በማየት የጉዞው መጨረሻ መሆኑን አረጋገጠ፡፡
ከዚያም በድንኳኑ ውስጥ አድሮ በማለዳ መንደር ወደ ሚገኝበት ቀበሌ ለመድረስ በጫካው ውስጥ ብዙ ሰዓት ከተጓዘ በኋላ፤ በሁለተኛው ቀን መንደርተኛው እስከ ጎሐ ጽዮን ሸኝተውት አውቶቡስ አሳፍረውት ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በቅቷል፡፡
ዶክተር አንዶር፤ ሦስት መቶውን ኪሎ ሜትር የተጓዘው በአሥር ቀኖች ውስጥ መሆኑን ገልጧል፡፡ በዚሁ ቀን ውስጥ በድንጋጤ ምክንያት ምግብ አልበላለት ስላለ፤ ሰባት ኪሎ ያህል የቀነሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ዶ/ር አንዶር የጉዞውን መመሪያ ላሰናደለት ለቱሪስት ድርጅትና ላዳኑት ለዓባይ አካባቢ መንደርተኞች ምስጋና አቅርቧል፡፡
(ጥር ፲፯ ቀን፲፱፻፷፮ ዓ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2014