
አፍዴራ፡- አሸባሪው ሕወሓት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በከፈተባቸው ዳግም ወረራ ቤት ንብረታቸውን ጥለው መፈናቀላቸውን በአፋር ክልል የዞን ሁለት መጋሌ ወረዳ እናቶች ተናገሩ።
ወ/ሮ አንድያ ሀመድ እና ወ/ሮ ከዲጃ ኢብራሂም የተባሉት አረጋውያን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪ ቡድን ባላሰቡትና ባልጠበቁት ወቅት በድንገት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በከፈተባቸው ዳግም ወረራ ንብረታቸውን ጥለው ለመፈናቀል ተገደዋል፡፡
ላለፉት ስልሳ ዓመታትም በጉርብትና አብረው መኖራቸውን የሚናገሩት እነዚህ አረጋውያን፤ እስከዚህ እድሜአቸው ድረስ ከቤታው ስለመፈናቀል አስበው እንደማያውቁ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት በትክክል እድሜአቸው ስንት እንደሆነ ባያውቁትም ሁለቱም ቅድመአያት መሆን መቻላቸውንና እያዳንዳቸውም ከሃምሳ በላይ የቤተሰብ አባላት እንዳፈሩም ይገልጻሉ፡፡
የመጋሌ ወረዳ የኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ዳሩ ቦርከታ በበኩላቸው፤ እነዚህ አዛውንቶች በአካባቢያቸው የሚታወቁት በተለይ ለታዳጊ ሴቶች አማካሪና መካሪ በመሆን ነው። ከዚህም በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ለነዚህ አረጋውያን ትልቅ ክብር ያለው በመሆኑ ምክራቸውን ይሰማል፤ ምርቃታቸውን ይፈልጋል።
ከዚህም ባሻገር በማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ ሰዎች ጠንክረው እንዲሰሩና የተሻለ ኑሮ እንዲኖራቸው በመምከር የሚታወቁ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ፤ በዚህ ምን እንደደረሰባቸው አናውቅም። ስለዚህ መንግሥት ቶሎ ብሎ ለወጣቶች ድጋፍ ቢያደርግ እነዚህን ሰው በላ ጠላቶች እናስወግዳቸዋለን ሲሉም ተስፋቸውን ተናግረዋል።
እንደ አረጋውያኑ ገለፃ፤ በአፋር ባህል አንድ ሰው በተለይ በዕድሜ ለሚበልጠው ሰው ክብር አለው። ግጭትም ቢሆን ሰው እና ሰው ቢጣላ በእኩል መሳሪያ ካልሆነ በስተቀር እድሉን አገኘሁ ብሎ ሰውን ማጥቃት ነውር ነው። ለምሳሌ መሳሪያ የታጠቀ እና ዱላ የያዘ ሁለት ሰዎች ቢጣሉ መሳሪያ የያዘው ሰው መሳርያ ይዣለሁ ብሎ ዱላ የያዘውን ሊመታው አይችልም። ከቻለ መሳሪያውን አስቀምጦ በዱላ ይፋለማል፤ ካልሆነ ግን ሸሽቶ ይሄዳል።
እነዚህ ግን በአሁኑ ወቅት አፋርን ያጠቁት በአጋጣሚ እጃቸው ላይ ባለው ከባድ መሳሪያ ነው። ይህ ደግሞ በኛ ባህል በጣም ነውር ነው። ሰው በከባድ መሳሪያ እንደዚህ ማድረግ ፈጣሪም አይወደውም፤ ነገር ግን እነሱ የአፋርን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት ነው እንዲህ የሚያደርጉት፤ አፋር ግን አሁንም ቢሆን ራሱን ለመከላከል ወደኋላ አይልም ብለዋል።
እነ ወይዘሮ አንድያ እንሚሉት እነዚህ አሸባሪዎች ሥነምግባራቸው እጅግ የተበላሸ ነው። ያገኙትን ሁሉ ንብረት ይዘርፋሉ፤ ሴቶችን ይደፍራሉ፤ አረጋውያንን ያዋርዳሉ፤ በአጠቃላይ እኛ እንዲህ አይነት ክፉ ስራ ከዚህ በፊት አይተን አናውቅም።

እኛ በአካባቢያችን ስንኖር በአብዛኛው እንስሳትን በማርባት ነው። አሁን ደግሞ እነዚህ ክፉ ሰዎች መጥተው እንስሳቶቻችንን ዘረፉብን። ከዚህም አልፎ ቤታችንን ሁሉ ጥለን ነው የወጣነው። አንዳችም ነገር ይዘን አልወጣንም። እኛ በዚህ በመጦሪያ እድሜአችን ተፈናቃይ ተብለን እርዳታ መጠበቃችን በጣም ያሳዝናል። ለዚህ የዳረጉንን እነዚህን ክፉ ጠላቶች ፈጣሪ የእጃቸውን ይስጣቸው ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
እኛ እነዚህ ጁንታዎች በድንገት በከባድ መሳሪያ ስለደበደቡን እንጂ የአፋር ወጣት ለነሱ አያንስም የሚሉት አረጋውያኑ፤ እንኳን ወጣቱ እኛ አረጋውያንም ብንሆን እነሱን ማስቆም እንችላለን። አሁን የከበደን ከባድ መሳሪያ በመያዛቸው ብቻ ነው ብለዋል።
ወርቁ ማሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም