ከድህነት ወለል ተነስተው የስኬት ማማ ላይ ከተቀመጡ በኋላ ምቾትና የተንደላቀቀ ህይወት መነሻን በሚያስረሳባት አለም አልፎ አልፎ የድንቅ ስብእና ባለቤት የሆኑ ብርቅ ሰዎች የሚፈጠሩበት አጋጣሚ አለ። የዛሬ ሳምንት አገሩ ሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነሳ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ኮከብ ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ ለዚህ ሁነኛው ማሳያ ነው።
የማኔ ህይወት መነሻና የደረሰበት የስኬት ደረጃም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ታዳጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾችም ይሁን በትልልቅ ክለቦች ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ በመሆኑ በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ከብዙ በጥቂቱ እንመልከተዋለን።
‹‹የፈለኩትን ያህል መኪና ፣ ቤትና የተለያዩ ነገሮችን በቀላሉ መግዛት እችላለሁ ፤ ነገር ግን አንድ ዘመናዊ መኪና ከምገዛ በሀገሬ ሆስፒታል አጥተው ለተቸገሩት ብሰራ ደስታው ይበልጥብኛል ፤ አንድ ትልቅ ቤት መግዛት ቀላል ነው፤ ነገር ግን ትምህርት ቤት ስለሌላቸው መማር ላልቻሉት ትምህርት ቤትን እንደ መስራት አያደስትም።›› የሚለው ማኔ፣ ‹‹በልጅነቴ ሰፈራችን አካባቢ ሆስፒታል ቢኖር አባቴ አይሞትም ነበር›› ሲል ይገልጻል። ‹‹ያንን ስቃይ ጠንቅቄ ስለማውቀው ዛሬ ላይ ሆስፒታል ላጡት ሆስፒታል፤ ትምህርት ቤት ለሌላቸው ትምህርት ቤት መስራት ያስፈልገኛል ፤ የቅንጦት ህይወት አያስፈልግም››ይላል።
ማኔ ይህን ያለው በአንድ ወቅት ለምን የተሰበረ ስልክ እንደያዘ ተጠይቆ አስደናቂ ስብእናው የተገለጠበትን መልስ በሰጠበት ወቅት ነው። አሁን ላይ በአለም ላይ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ማኔ ተወልዶ ያደገው በምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ትንሽ መንደር ውስጥ ነው።
እኤአ በ1992 ቦምባሊ በሚባል መንደር ውስጥ ተወልዶ ያደገው ማኔ፣ ከአስር በላይ ከሆኑ የቤተሰቡ አባላት ጋር የልጅነት ህይወቱን በድህነት አሳልፏል። አባቱ የአካባቢው መስጊድ ኢማም ነበሩ። ትንሹ ማኔም በትምህርቱ እንዲበረታ እንጂ ወደ ኳስ እንዲሳብ ፍላጎት አልነበራቸውም።
ሆኖም የታዳጊው ማኔ የኳስ ፍቅር የአባትን ስሜት አሸነፈ። ወጣቱ ማኔም የጨርቅ ኳሱን ሰፈሩ ውስጥ እያንከባለለ የስፖርት ትጥቅ ሳያስፈልገው በባዶ እግሩ ለእግር ኳስ ህይወቱን ሰጠ። ከትምህርቱ ይልቅ እግር ኳስን የወደፊት ተስፋው አድርጎ አጥብቆ ያዘ።
የወጣቱ ማኔ ችሎታና በትጋት የሚሠራው ሥራ ቀስ በቀስ እያደገ ሄደ ። በ 15 ዓመቱም ወላጆቹ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ለእግር ኳስ እንዲሰጥ ቢስማሙም ርቆ እንዲሄድ አልፈቀዱም። ማኔ ግን ቤተሰቦቹ ሳያውቁ ጠፍቶ ወደ ዳካር በመሄድ በአንድ የእግር ኳስ አካዳሚ ውስጥ ራሱን ለማሳደግ ወስኖ ተጓዘ። የሴኔጋላዊው ኮከብ የስፖርት ሕይወት መሰረት የያዘበት አጋጣሚም ይህ ነው።
ማኔ ለ5 ዓመታት በዳካር ቆይቷል፤ ከ2005 እስከ 2010። እ.ኤ.አ በ 2010 በአፍሪካዊው የአጥቂ አማካይ የመፍጠር ችሎታ ፣ ፍጥነቱና ቅልጥፍናው የፈረንሳዊው ክለብ ሜትዝን መልማዮች ትኩረት ስቦ ሴኔጋልን ለቆ ባህር ተሻግሮ ለመሄድ አበቃው። ለሜትዝ የወጣት ቡድን መጫወት ጀምሮ ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋናው የአዋቂ ቡድን ተዛወረ። በፈረንሣይ እኤአ እስከ 2012 ድረስ በቆየበትም ወቅት እንዳሰበው በፍጥነት ለስኬት አልበቃም፤ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፈጠ።
እኤአ በ2012 – 2013 የውድድር ዘመን ማኔ ወደ ኦስትሪያው ክለብ ሬድቡል ሳልዝበርግ ተዛወረ። በዚያም ስኬታማ ጊዜን አሳልፎም በ2014 ተስፋ ሰጭው አማካይ ወደ እንግሊዝ ተዛወረ። በሳውዛምፕተን ተጫውቶም ወደ ስኬት ማማ የደረሰበትን ክለብ ሊቨርፑልን ተቀላቀለ። ከዚህ ታሪካዊ ክለብ ጋርም የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ የፕሪሚየርሊግ ዋንጫን በማንሳት ቁልፍ ተጫዋች ለመሆን ችሏል።
ማኔ ለዚህ ስኬት ሲበቃ ግን ነገሮች ሁሉ የተመቻቹ ሆነው አልነበረም። በተለይም በሊቨርፑል የመጀመሪያ አመታት ለእርሱ እጅግ ፈታኝና የሊቨርፑል ደጋፊዎች እንኳን ሳይቀሩ ያጉረመረሙበት ተጫዋች ቢሆንም፣ ትልቅ ህልምና ጉጉት ያለው ማኔ ቀን ከሌሊት እየሰራ በትልቁ ክለብ ራሱን ማሳየት ጀመረ። ከ2018 አንስቶም ነው ሊቨርፑል ያለ ማኔ ምንም እንዳልሆነ ማሳየት የጀመረዉ፤ ተጫዋቹ የማይደክም፣ ራስ ወዳድ ያልሆነ፣ ከራሱ ይልቅ ለክለቡ ተጫዋቾችና ለክለቡ የሚያስብ በመሆን አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ እንዲመኩበት ማድረግ ችሎ ወደ አለም ክለቦች አይን ውስጥ መግባት የቻለው።
ማኔ የስኬት ፍሬው ያመጣለትን ሃብትና ዝና እንደ በርካታ የአለማችን ተጫዋቾች አልተመጻደቀበትም። ወደ ድሃዋ የትውልድ መንደሩ ተመልሶ ከእናቱ አልፎ ለሙሉ ሴኔጋል መድረስ ቻለ። የእረፍት ጊዜውንም እንደ በርካቶቹ ኳስ ተጫዋቾች በተንደላቀቁ ውድ የባህር ዳርቻዎች ከማሳለፍ ይልቅ ወደ ትውልድ መንደሩ በመሄድ ያሳልፋል።
ከቤተሰቦቹ አልፎም ድሆችን መመገብ፣ ትምህርት ቤት ማሰራትና ሆስፒታል አጥቶ ለሞተው አባቱ መታሰቢያ እንዲሆን ትልቅ ሆስፒታል በሀገሩ አሰራ። የቅንጦት ህይወት እንደማይመቸው የሚናገረው ማኔ ጥቅም ለሌለው ነገር ብር ከሚያወጣ ለእርዳታ ማዋልን ይመርጣል።
ማኔ አሁን ላይ ከዛ ሁሉ ረሀብ፣ ድካም ፣ መገፋት፣ ችግር፣ ሀዘንና ዝቅተኝነት ወጥቶ በአገሩ ትልቅ ስቴድየም የገነባ ሰው ሆኗል። ትናንት ያለፈበትን መንገድ እያሰበ ብዙዎችን ረድቷል፤ ወደ ፊትም ለአፍሪካ በሙሉ የብርታት ማሳያ በመሆን ይጠቀሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014