ለ19ኛ ጊዜ የሚካሄደው የሴቶች የ5 ኪ.ሜ ውድድር ምዝገባ ተጀመረ፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያን በተቀላቀለው ሳፋሪኮም ስፖንሰር አድራጊነት የሚካሄደው ይህ ውድድር ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ ሲካሄድ 10ሺህ ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በተከናወነው በውድድሩ ምዝገባ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ እንደተጠቆመው፤ ውድድሩ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፣ ምዝገባውም ከትናንት በስቲያ ተጀምሯል፡፡ የውድድር መመዝገቢያም 300 ብር ሲሆን፣ አሸናፊዋ አትሌትም የ25ሺህ ብር ተሸላሚ ትሆናለች፡፡ ከዚህ ቀደም ይህን ውድድር ካሸነፉ አትሌቶች መካከል ያለምዘርፍ የኋላው፣ ጸሀይ ገመቹ እና ጽጌ ገብረሰላማ ይገኙበታል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ‹‹ከሁለት ዓመት በፊት ኮሮና ወረርሽኝ ከመምጣቱ ቀደም ብሎ ውድድሩን ማካሄድ ተችሏል፡፡ አምናም ወረርሽኙ ቢኖርም፣ ውድድሩን ማዘጋጀት ችለናል፡፡ ውድድሩን አለማቋረጣችን እድለኛ ያሰኘናል›› ብላለች፡፡
የውድድሩ የክብር አምባሳደር ጀግናዋ አትሌት መሰረት ደፋር ዘንድሮ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ከ35 ደቂቃ በታች 5 ኪሎ ሜትሩን የሚያጠናቅቁበትን ቻሌንጅ ያስጀመረች ሲሆን፣ ውድድሩ ለሴቶች ያለውን ፋይዳም አስረድታለች፡፡
በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በተከናወነው በዚህ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና አርቲስት ቻቺ ታደሰን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታድመውበታል፡፡
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014