ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወጣቶች እጅ ኳስ ዋንጫ አራተኛ ሆና አጠናቀቀች

የአፍሪካ አህጉር ወጣት ወንዶች ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች እጅ ኳስ ዋንጫ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለተከታታይ አምስት ቀናት ተካሂዶ ከትናንት በስቲያ ተጠናቋል፡፡ በውድድሩ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ “ስፖርት ለአህጉራዊ ሰላም” በሚል ሃሳብ የተካሄደው የ2024 የዓለም አቀፍ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ዋንጫ አህጉራዊ ቻምፒዮና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ18 እና 20 ዓመት በታች የወንዶች እጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድኖችን አሳትፏል፡፡ ከ10 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ፣ 11 ብሔራዊ ቡድኖች በሁለቱ የእድሜ እርከኖች ጠንካራ ፉክክር ሲያደርጉ ኢትዮጵያ የደረጃ ተፋላሚ በሆነችበት ጨዋታ ከልምድ ማነስ፣ ቴክኒክ፣ ታክቲክና በአካል ብቃት የበለጠ ውጤት ሳታስመዘግብ አጠናቃለች፡፡

ኢትዮጵያ በውድድሩ ሶስት ጨዋታዎችን ጠንካራ ከሆኑ ሀገራት ጋር አድርጋ አንዱን በመርታት፣ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፋለች፡፡ የመጀመሪያ ጨዋታዋን የዛምቢያ አቻውን 41 ለ 14 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በድል መጀመር ችላ ነበር። በሁለተኛው ጨዋታ ጠንካራዋንና ቻምፒዮን የሆነችውን ናይጄሪያን ገጥማ 47 ለ31 በሆነ ውጤት ተሸንፋለች፡፡ በዚህም በደረጃ ጨዋታ የካሜሩን ብሔራዊ ቡድንን ገጥማ 45 ለ 37 በሆነ ውጤት ተረታ ሜዳሊያ ውስጥ ሳትገባ ውድድሩን ፈጽማለች፡፡

የኢትዮጵያ ቡድን በልምድ ማነስ፣ ቴክኒክና ታክቲክ እንዲሁም በአካል ብቃት በተጋጣሚዎቹ ቢበልጥም ትልቅ ልምድ ቀስሞ ውድድሩን ማጠናቀቁን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝና ተጫዋቾች ተናግረዋል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ተስፋዬ ሙለታ፣ በውድድሩ ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ጠንካራ ቡድኖች ጋር በመጫወታቸው የጠበቁትን ውጤት እንዳላገኙ ገልፀዋል፡፡ ቡድኑ ከረጅም እረፍት በኋላ ወደ ውድድር እንደተመለሰ የጠቀሱት አሰልጣኙ፣ ይህም በብዙ ነገሮች እንዲበለጥ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቡድኑን ተሰባስቦ በአካል ብቃት፣ ቴክኒክና ታክቲክ ላይ ዝግጅት ለማድረግ የነበረው ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ወደ ፉክክር መግባቱንም አስታውሰዋል፡፡

ናይጄሪያና ካሜሩን በእጅ ኳስ ስፖርት ትልቅ ደረጃ ላይ የሚገኙ እንደሆኑ የሚጠቅሱት አሰልጣኙ፣ በአካል ብቃት፣ በቴክኒክና ታክቲክ፣ ከፍተኛ ብቃት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ የማገገሚያ ጊዜ አለመኖርና በየቀኑ የመጫወት ልምድ ማጣት የኢትዮጵያ ቡድን ላይ ጫና ፈጥሯልም ብለዋል፡፡ በውድድሩ የተሻለ ውጤት ባይመዘገብም የስልጠና እና ምልመላ መንገዱ መፈተሽ እንደሚኖርበት ትልቅ ልምድ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በስፖርቱ የእድሜ ጉዳይ አሁንም ትልቅ ጥያቄ የሚያጭርና ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት የሚገባው ጉዳይ ሲሆን፣ ለዚህም የእጅ ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ አለመኖር ትልቅ ችግር እንደሆነም አክለዋል፡፡ በፕሮጀክቶች ላይ የሚሰራውም ስራ ተመጋጋቢና ታዳጊዎችን ማፍራት የሚያስችል መንገድን መከተል እንደሚኖርበት አመላክተዋል፡፡ የትምህርት ቤቶች እጅ ኳስ ውድድር ትኩረት ተሰጥቶበት መካሄድ እንደሚኖርበትም አስቀምጠዋል፡፡

ከወጣት ብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ስጦታው ፍቃዱ በበኩሉ፣ ኢትዮጵያ ውድድሩን በተሻለ ሁኔታ ለማስተናገድ ትልቅ ዝግጀት ማድረጓንና ለዚህም ወጣት ብሔራዊ ቡድኑ የምሥራቅ አፍሪካ ዋንጫን ማንሳቱ ምክንያት እንደሆነ አስታውሶ፣ ቡድኑ የተሻለ ዝግጅት በማድረግ ውድድሩን በድል እንደጀመረ ተናግሯል፡፡ በእጅ ኳስ ችሎታ የተሻለ ደረጃና ብቃት ላይ የሚገኙ ሀገራትን በመግጠማቸው አራተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸውንም ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ውድድር በመሳተፏ የተሻለ ልምዶችን መቅሰማቸውን አስረድቷል፡፡ ውድድሩ ኢትዮጵያ በመካሄዱ የእጅ ኳስ ስፖርትን በከፍተኛ ደረጃ ማነቃቃት መቻሉንና ውድድሮች ቤት ውስጥ እንዲካሄዱ፣ የዳኝነትና የስልጠና መንገዶች መፈተሽ እንደሚኖርባቸውም አስተያየቱን ሰጥተል፡፡

ከ18 ዓመት በታች በተካሄደው ከፍተኛ የዋንጫ ፉክክር ናይጄሪያ ጊኒን 38 ለ 26 በመርታት የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆና አጠናቃለች፡፡ ጊኒ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳሊያ ይዛ ስታጠናቅቅ፣ ካሜሩን ኢትዮጵያን በደረጃ ጨዋታ አሸንፋ ሶስተኛና የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች፡፡ ከ20 ዓመት በተካሄደው ውድድር ርዋንዳ ኮንጎን በመርታት ዋንጫ አንስታለች። ኮንጎ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቀቅ ሪዩኒየን ሶስተኛ ደረጃ ይዛ ውድድሩን ፈጽማለች፡፡

የናይጄሪያ ከ18 ዓመት በታችና የርዋንዳ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች አፍሪካን በዓለም እጅ ኳስ ዋንጫ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ታዳጊና ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች የተሳተፉበት፣ ይህ ውድድር 6 ከ 18 ዓመት በታች 5 ከ20 ዓመት በታች በአጠቃላይ 11 ብሔራዊ ቡድኖች ተወዳዳሪ ሆነዋል። ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ጊኒ፣ ካሜሩን፣ ዛምቢያ እና ናይጄሪያ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖቻቸው ሲወዳደሩ፤ ሪዩኒየን፣ ዚምባቡዌ፣ ርዋንዳ፣ ጊኒ እና ኮንጎ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን አወዳድረዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You