በስፖርት እንቅስቃሴ በስፋት ከሚታወቁ ክፍለ ከተሞች አንዱ አቃቂ ቃሊቲ ነው:: የአካባቢው ማኅበረሰብ ለስፖርት ያለው ቅርበትና ፍቅር ልዩ ነው:: በርካታ ስፖርተኞችም ከስፍራው ወጥተው ሀገርን እስከ መወከል ደርሰዋል:: እግር ኳስ በአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይም በወጣቶች በስፋት ከሚዘወተሩ ስፖርቶች ግንባር ቀደም ነው::
በአካባቢው በርካታ የጤና ቡድኖችና የታዳጊ ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ ያደርጋሉ:: በዚህም ለአካባቢው ስፖርት እድገትና መነቃቃት አስተዋፅዖ እያደረጉ ይገኛሉ:: ከነዚህ መካከል በእድሜ ደረጃዎች የሚካሄዱት ውድድሮች አካባቢው ቀድሞ የሚታወቅበትን ጠንካራ የእግር ኳስ መነቃቃት እየመለሰ እንደሚገኝ እያመላከተ ነው:: ይህም በአቃቂ ቃሊቲ የጤና ስፖርት ማኅበራት እግር ኳስ ውድድር ላይ ሊንፀባረቅ ችሏል:: ውድድሩ የታዳጊ ፕሮጀክቶች እግር ኳስን መደገፍ ዓላማ አድርጎ ዘንድሮ ለአራተኛ ዓመት ከሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ በቅርቡ ተጠናቋል::
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ አወዳዳሪነት የተካሄደው ይህ ‹‹ሰመር ካፕ›› የተሰኘ የጤና ስፖርት ማኅበራት ውድድር በሁለት የእድሜ እርከኖች 28 የጤና ቡድኖችን አሳትፏል::
እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ 20 ቡድኖችና እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ 8 ቡድኖች በውድድሩ ተሳታፊ ሆነዋል:: እነዚህ ቡድኖች በአምስት ወራቱ የዙር ውድድር በሰበሰቡት ነጥብ መሠረት አሸናፊው ታውቋል:: ከ30 ዓመት በላይ ውድድር የፍጻሜ ጨዋታ አቃቂ ወንድማማቾች ጤና ስፖርት ማኅበር ከሞኩና ጓደኞቹ ቡድንን በፍፃሜ 4 ለ 2 በሆነ መለያ ምት አሸንፎ ፉክክሩ ፍጻሜ አግኝቷል:: ከ40 ዓመት በላይ ውድድሩ ደግሞ ሞኩና ጓደኞቹ ጤና ስፖርት ማኅበር የዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል:: አቃቂ ወንድማማቾች ደግሞ ሁለተኛ እንዲሁም ሲዳ አዋሽ ወንድማማቾች ሦስተኛ በመሆን የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል::
የክፍለ ከተማው የስፖርት ለሁሉም ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ገዛኸኝ ምንድዬ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ሰመር ካፕ የጤና ስፖርት ማኅበራቱ ከውድድር ባሻገር በሥራቸው የተተኪና ታዳጊ ወጣት ስፖርተኞች ፕሮጀክት በማቋቋም ድጋፍ እያደረጉና እያሠለጠኑ መሆኑን ተናግረዋል:: ስፖርት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይም የስፖርት ማዘውተሪያን ከማስተካከል ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ስፖርት ማኅበራት ማደራጀት፣ እውቅናና ድጋፍ ባለሙያ አቶ ተካበ መካሻ፣ የውድድሩ ዓላማ ታዳጊ ወጣቶችን መደገፍ እንደሆነ ጠቅሰው፣ 28ቱም የጤና ስፖርት ማኅበራት የታዳጊ እግር ኳስ ፕሮጀክቶችን በሥራቸው እንደያዙ አስረድተዋል:: በዚህም መሠረት ከፍተኛ ወጪ በማድረግ የመጫወቻ ኳስ ግዢ ተፈጽሞ ለሁሉም ቡድኖች ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል:: ውድድሩ በስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ አማካኝነት የሚካሄድ ሲሆን፣ ዘንድሮ የተሳታፊ ቁጥር መጨመሩንና የአካባቢው ኅብረተሰብም ማነቃቃቱን አክለዋል::
ከመንግሥትና ኅብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር እንዲሁም ትልልቅ ተቋማት ኮሚቴውን መደገፋቸውን አስታውሰውም፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ውድድሩ ዓመቱን ሙሉ እንዲካሄድ ፍላጎት ማሳየቱን ጠቅሰዋል:: አቃቂ ላይ ከአርባ በላይ የጤና ስፖርት ማኅበራት የሚገኙ በመሆኑ በቀጣይ እነሱን ያሳተፈ ትልቅ ውድድር ለማካሄድ መታቀዱንም አብራርተዋል:: በከተማው ያለውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በትብብር ለማሠራት ቃል የገቡ ባለሃብቶች መኖራቸውም ተጠቅሷል::
የክፍለ ከተማው አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና፣ ውድድሩን ላዘጋጁ የስፖርት ማኅበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበው፣ ከተማዋን ምቹ ለማድረግ ከሚያከናወኑት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ጤናማና አምራች ማኅበረሰብ ለመፍጠር በስፖርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንና በቀጣይም ድጋፋ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፣ በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውን ገልጸው፤ የጤና ስፖርት ማኅበራቱ ጤንነታቸውን ለመጠበቅ ውድድር ከማካሄድ በላይ ታዳጊዎችን አቅፈው መያዛቸውን አድንቀዋል:: ተተኪና ወጣት ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚደረገ ጥረት የሚበረታታና ለማስቀጠልም ፌዴሬሽኑ ባለው አቅም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል። በውድድሩ ቡድኖቹ የማይመች ሜዳ ላይ እንደተጫወቱና፣ ይህንን ክፍለ ከተማውና የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት እንዲሰጡበትም አመላክተዋል:: የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቃቂ ለሚገኙ የጤና ቡድኖች ሙያዊና የመጫወቻ ኳሶችን ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል::
አዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ከተማውን እና ሌሎች ደጋፊ አካላትን በማስተባበር ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንደሚሠራ ገልጸዋል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም