የምስራቅ አፍሪካ አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ውድድሩ ከጃንሜዳ ዓለም አቀፍ የአገር አቋራጭ ውድድር ጋር ተያይዞ ነገ እንደሚደረግም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የመጀመሪያውን የምስራቅ አፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር በማካሄድ የጎረቤት አገራትን ትስስር ማጠናከር እንዲሁም አገራትን በአትሌቲክስ ስፖርት ማስተሳሰርን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል። ዘጠኝ አገራት በዚህ ውድድር ተሳታፊ እንዲሆኑ በፌዴሬሽኑ በኩል ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን፤ አምስት አገራት ተሳታፊ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ኤርትራ አራት አትሌቶቿ በውድድሩ እንደሚካፈሉ ስታሳውቅ፤ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ታንዛኒያ ደግሞ ሁለት ሁለት በድምሩ 12 አትሌቶችን ያሳትፋሉ።
ሁለት ስያሜ በመያዝ በሚደረገው የዘንድሮው ውድድር በኢትዮጵያ ብቸኛው ዓለም አቀፍ የሆነው ውድድር የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ለ39ኛ ጊዜ ይካሄዳል። ለበርካታ አትሌቶች የውድድር እድል የሚሰጠውና አገርን ወክለው በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች የሚመረጡበት ይህ ውድድር፤ ዘንድሮም በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦች፣ የግል አትሌቶችና ቬትራን አትሌቶች መካከል ይደረጋል። አትሌቶች ከአገራቸው ሳይወጡ በዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ውድድር ተሳታፊ በመሆን ልምድ ከማግኘታቸው ባለፈ በማበረታቻ ሽልማት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድልንም የሚፈጥር እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህ ውድድር ላይ አምስት ክልሎች፣ ሁለት ከተማ አስተዳደሮች፣ 19 ክለቦች፣ 55 ቬትራን እና 111 የግል ተወዳዳሪዎች በጥቅሉ 724 አትሌቶች ተሳታፊዎች ይሆናሉ። ከእነዚህም መካከል ታዋቂና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ስኬታማ የሆኑ ስመጥር አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ታውቋል። በወንዶች ሙክታር እንድሪስ፣ ጀማል ይመር፣ አቤ ጋሻው፣ ንብረት መላክ፣ የኔው አላምረው እና በሪሁ አረጋዊ ጥቂቶቹ ናቸው። በሴቶች በኩልም ሱሌ ኡቱራ፣ አባበል የሻነህ፣ መልክናት ውዱ እና ቃልኪዳን ፈንቴን የመሳሰሉ አትሌቶች ክለቦቻቸውን ወክለው ይሮጣሉ።
ውድድሩ አምስት ምድቦች ያሉት ሲሆን፤ ከ20 ዓመት በታች ወጣት ምድብ በሴቶች 6ኪሎ ሜትር እና ወንዶች 8ኪሎ ሜትር፣ በአዋቂ ምድብ 10 ኪሎ ሜትር ወንድ እና ሴት እንዲሁም 8 ኪሎ ሜትር ድብልቅ ሪሌ ናቸው። በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የሜዳሊያ እንዲሁም በቡድን የዋንጫ ተሸላሚዎች ሲሆኑ፤ በየውድድር ዓይነቱ በግል ከ1 እስከ 6ኛ ለሚወጡ እንዲሁም በቡድን ከአንድ እስከ ሦስት ለሚወጡ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል። ለዚህም ፌዴሬሽኑ 840ሺህ ብር ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
ውድድሩ የሚካሄድበት ጃንሜዳ መሰናክሎችን ጨምሮ ለአገር አቋራጭ ውድድር ምቹ በሚሆን መልኩ መዘጋጀቱንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ዓለም አቀፍ ውድድር እንደመሆኑ መጠን የዓለም አትሌቲክስ ባስቀመጠው ደረጃ መሰረት ዕውቅና ባላቸው ዳኞች ይመራል። ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞም ተሳታፊ አትሌቶች መመርመራቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ እንዲያቀርቡ የሚገደዱ ሲሆን፤ ላልቻሉ ደግሞ አንድ ቀን አስቀድሞ መመርመር የሚችሉበት ሁኔታ በፌዴሬሽኑ ተመቻችቷል። ከጎረቤት አገራት የሚመጡ አትሌቶችም ከንክኪ ርቀውና ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ብቻ ተሳታፊ ይሆናሉ። ከዚህ ባሻገር ውድድሩ ዓለም አቀፍ በመሆኑ እንዲሁም መሰናክሎች ያሉት እንደመሆኑ ድንገተኛ አደጋዎች ቢያጋጥም የህክምና እርዳታ ለመስጠት ሁለት የህክምና ባለሙያዎች፣ ቀይ መስቀል እንዲሁም ወጌሻዎች በስፍራው ይኖራሉ። አደጋ ካጋጠመም አምቡላንስ እንዲሁም በጃንሜዳ አቅራቢያ የሚገኘው ምኒሊክ ሆስፒታልና እና ሌሎች የህክምና ተቋማት ዝግጅት ማድረጋቸውም ታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014