ትኩሳት ምንድን ነው?
ትኩሳት ሰውነት ከጎጂ ባክቴርያዎች እና ሌሎች ተውሳኮች ራሱን በሚከላከልበት ጊዜ የሚፈጠር የሰውነት ሙቀት መጨመር ነው። ጤነኛ የሆነ ህጻን የሰውነት ሙቀት ከ97 እስከ 100.4 ዲግሪ ፋራናይት (ከ36.1 እስከ 38 ዲግሪ ሴልሸስ) ነው።
የሰውነት ሙቀት እንዴት መለካት ይቻላል?
ትኩሳት በህጻናት ላይ ሲኖር መጀመሪያ መደረግ ያለበት ነገር የህጻኑን የሙቀት መጠን በቴርሞ ሜትር ለክቶ ማወቅ ነው። ልጅ ያለው ሰው ቴርሞ ሜትር በቤቱ ቢኖረው መልካም ነው። ዲጂታል ቴርሞሜትር በዋጋ ተመጣጣኝነትም ሆነ ለአጠቃቀም ቅለት ከሌሎቹ የቴርሞሜትር አይነቶች የተሻለ ነው።
የሰውነትን የሙቀት መጠን ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች መለካት ይቻላል። ከምላስ በታች፣ ከብብት፣ ከጆሮ፣ ከግምባር እና ከፊንጢጣ ትኩሳትን መለካት የተለመዱ መንገዶች ናቸው። ህጻኑ ከምላሱ ስር የቴርሞ ሜትሩን ጫፍ አፍኖ መያዝ የሚችል ከሆነ ከምላስ በታች ትኩሳትን መለካት የተሻለ መንገድ ነው። ካልሆነ ግን ከብብት ሙቀትን መለካት ይቻላል። ከጆሮ እና ከግምባር መለካት ትክክለኛ የሙቀት መጠን ላይሰጥ ይችላል።
ህጻኑ ከሦስት ወር በታች ከሆነ ከፊንጢጣ የሙቀት መጠንን መለካት በህክምና ባለሙያዎች የሚመከር መንገድ ነው። የልጅዎትን ሙቀት መጠን በዚህ መልኩ መለካት ከፈለጉ ህጻኑ እንዳይጎዳ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያድርጉ። በብብት የለኩትን የሙቀት መጠን ለማረጋገጥ ቢጠቀሙበት የተሻለ ነው።
ለትኩሳት የሚሰጡ መድኃኒቶች
ትኩሳት ለማብረድ ያለዶክተር ትዕዛዝ የሚሸጡ መድኃኒቶች አሲታሚኖፍን (acetaminophen/Tylenol/ Motrin) እና አይቦፕሮፍን (ibuprofen/Advil/) ናቸው።
1. አሲታሚኖፊን (Acetaminophen/Tylenol)
አሲታሚኖፊን ለልጆች የተሻለ የትኩሳት ማስታገሻ ነው። ይህ መድኃኒት በፈሳሽ መልክ በተለያዩ ጣዕሞች ተዘጋጅቶ ይመጣል። አንዴ አሲታሚኖፊን ከሰጡ በኋላ ህጻኑ ከተሻለው ደግሞ መስጠት አያስፈልግም። ካልተሻለው ግን ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ደግመው መስጠት ይችላሉ። በሃያ አራት ሰዓት ጊዜ ውስጥ ከአምስት ጊዜ በላይ መሰጠት የለበትም። ከተጠቀሰው በላይ አሲታምኖፊን ለህጻናት መስጠት የጉበት በሽታ ሊያመጣ ይችላል። ስለዚህ ልጅዎ ከሚመከረው በላይ ከላይ የተጠቀሰውን መድኃኒት የወሰደ ከመሰለዎ ወደ ሆስፒታል ይውሰዱት።
2. አይቦፕሮፊን (Ibuprofen/Advil/Motrin)
እንደ አሲታሚኖፊን ሁሉ ለልጆች የሚሰጠው አይቦፕሮፊን በፈሳሽ መልክ በተለያዩ ጣዕሞች ተዘጋጅቶ ይመጣል። ይህ መድኃኒት ከስድስት ወር እድሜ በታች ላሉ ህጻናት መስጠት የተከለከለ ነው። ከስድስት ወር እስከ ሁለት አመት እድሜ ላሉ ህጻናት ያለሀኪም ትዕዛዝ መስጠት አይመከርም። ልጅዎ ከሁለት አመት በላይ ከሆነ እና የኩላሊት ወይም የልብ በሽታ ከሌለበት አይቦፕሮፊን መስጠት ይቻላል።
እንደሌሎች ማስታገሻ መድሃኒቶች ሁሉ አንድ ጊዜ አይቦፕሮፍን ተሰጥቶት የህጻኑ ትኩሳት ከበረደ መድገም አያስፈልግም። ካልተሻለው ግን ከስድስት እስከ ስምንት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደገና መስጠት ይቻላል። ነገር ግን በሃያ አራት ሰዓት ጊዜ ውስጥ ከአራት ጊዜ በላይ መስጠት አይመከርም።
የዚህ መድኃኒት አመጣጠን ከአሲታሚኖፍን ጋር ተመሳሳይ ነው። ምን ያህል እንደሚሰጡት ለማወቅ የመድኃኒቱ ብልቃጥ ላይ የተለጠፈውን ወረቀት ወይም ካርቶኑ ላይ ያለውን ትዕዛዝ (dosing or direction) ይፈልጉ። የልጅዎትን ክብደት ካወቁ በክብደቱ መሰረት ይስጡት። በቅርብ ጊዜ ተመዝኖ የማያውቅ ከሆነ ግን በእድሜው መሰረት ምን ያህል ሚሊ ሊትር (mL) እንደሚሰጡት ይመልከቱ። የህክምና ባለሙያዎች የሚመክሩትና የተሻለው መንገድ የመድኃኒቱን መጠን በክብደት መሰረት መመጠን ስለሆነ የልጅዎን ጊዜያዊ ክብደት ማወቅ ጠቃሚ ነው።
ለህጻናት መድኃኒት ሲሰጡ ማድረግ ያለብዎት ጥንቃቄ
1. መድኃኒት ለመለካት ተገቢ መመጠኛ ይጠቀሙ
አንዳንድ ሰዎች ለህጻናት የሚሰጥ ፈሳሽ መድኃኒት ለመለካት የቤት ማንኪያ ይጠቀማሉ። ይህ ትክክል አይደለም። የቤት ማንኪያዎች የሚይዙት መጠን የተለያየ ስለሆነ ልጁ ከሚገባው በላይ ወይም ከሚገባው በታች መድኃኒት ሊሰጠው ይችላል። መድኃኒቱ መለካት ያለበት ከመድኃኒቱ ጋር ከሚመጣ ትንሽ ስኒ የሚያክል ፕላስቲክ ወይም ለፈሳሽ መድኃኒት መለኪያ ተብሎ በሚዘጋጅ ስሪንጅ ነው።
2. መድኃኒትን ከምግብ ጋር ቀላቅሎ ስለመስጠት
አንዳንድ ልጆች መድኃኒት እሺ ብለው አይወስዱም። ወላጆች ይህንን ችግር ለመፍታት መድኃኒቱን በምግብ ደባልቀው ሊሰጧቸው ይሞክራሉ። ይህንን ማድረግ የአይቦፕሮፊንንም ሆነ የአሲታሚኖፊንን መድኃኒትነት አይቀንስም። ነገር ግን ህጻኑ መድሃኒቱ የተደባለቀበትን ምግብ ጥቂት በልቶ ከተወው ከቀረው ምግብ ጋር የተወሰነ መድኃኒት ስለሚቀር የሚያስፈልገውን የመድኃኒት መጠን አያገኝም። መድኃኒቱን በምግብ ደባልቆ ከመስጠት በፊት ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ጥሩ ነው። ይህን ማድረግ ከፈለጉ፤ በትንሽ (ከአንድ ማንኪያ ባልበለጠ) ጁስ ወይም አፕልሶስ (applesauce) ውስጥ መደባለቅ ይቻላል።
3. የጉንፋን መድኃኒቶች ውስጣቸው የትኩሳት መድኃኒት ሊኖራቸው ይችላል
ለልጅዎ የትኩሳት መድኃኒት ሲሰጡት ሌላ መደረግ ያለብት ጥንቃቄ አለ። ይኸውም አንዳንድ የሳል እና የጉንፋን መድኃኒቶች ውስጥ አሲታሚኖፊን ወይም አድቪል ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ የልጆች የጉንፋን መድሃኒት (Triaminic Children’s) በውስጡ አሲታሚኖፊን አለው። ስለዚህ ለልጅዎ ተጨማሪ የትኩሳት መድኃኒት መስጠት የለብዎትም። ይህንን ማድረግ ልጁን ከሚገባው በላይ መድኃኒት በሰውነቱ እንዲኖር ያደርገዋል። መድኃኒት ሲበዛ ሰውነትን ይጎዳልና ጥንቃቄ ያድርጉ።
4. ለህጻናት እና ለትልቅ ሰው የሚሰጠው የትኩሳት መድኃኒት የተለያየ ነው
ለህጻናት እና ለትልቅ ሰው የሚሰጠው የትኩሳት መድኃኒት ተመሳሳይ አይደለም። ስማቸው አንድ አይነት ቢሆን እንኳን በተመሳሳይ ሚሊሊትር(mL) ውስጥ ያለው የመድኃኒት መጠን ስለሚለያይ፤ የትልቅ ሰው ማስታገሻ መድኃኒት ለህጻናት አይሰጥም።
5. አስፕሪን ለህጻናት እና ለታዳጊ ልጆች አይሰጥም
አስፕሪን (aspirin) ሌላ ትኩሳት የመቀነስ ችሎታ ያለው መድኃኒት ነው። ነገር ግን እድሜያቸው ከአስራ ስድስት አመት በታች ለሆኑ ልጆች መስጠት አጥብቆ የተከለከለ ነው። ትኩሳቱን የሚያመጣው እንደጉፋን ያለ የቫይረስ ህመም ሊሆን ይችላል። የቫይረስ ህመም ያለባቸው ህጻናት (እያገገሙ ያሉ ወይንም ደግሞ ያለህመም በውስጣቸው ቫይረስ ያለ ቢሆን እንኳን) አስፕሪን ሲወስዱ ሬይስ ሲንድሮም (Reye’s syndrome) የሚባል በሽታ ሊያመጣባቸው ይችላል። ስለዚህ ሃኪም ካላዘዘ በስተቀር፤ ከአስራ ስድስት አመት በታች ላሉ ህጻናት እና ታዳጊ ልጆች አስፕሪን መስጠት የተከለከለ ነው።
ምንጭ፡- Amharic Health Information
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014