መታሰቢያነቱ ለማህተመ ጋንዲ የሆነው ሆስፒታል የዛሬ 63 ዓመት በ1953 ዓ.ም ነው የተቋቋመው። ወቅቱ የእናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል እንዲህ እንደዛሬው የተበራከተበት አልነበረም። በእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ሙያ የሰለጠኑትም ቢሆኑ ጥቂት ነበሩ። አብዛኞቹ ባለሙያዎች በልምድ ነበር የሚሰሩት። የተቋቋመበት ዓላማ የእናቶችና ሕፃናት ሞት መቀነስን ታሳቢ ያደረገም ነው።
በልምድ አዋላጆች በየቤቱ ልጆቻቸውን የሚወልዱ እናቶችን፤ የሚያዋልዱ አዋላጆች ስለሙያው ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የራሱን ድርሻ ለመወጣትም ነው። እንደውም አንዳንዶቹ የዚያን ዘመን ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ ራሳቸው ጭምር ልጆቻቸውን በልምድ አዋላጆች በቤታቸው ውስጥ እስከ መውለድ የሚደርሱበት አጋጣሚም ቀላል አልነበረም። ለእናቶች የሚሰጠው ክብርም ከፍተኛ ነበር።
‹‹በሕክምናው ዓለም ስናልፍ ብዙ የተማርናቸው የሙያ ስነ-ምግባሮች አሉ›› የሚሉት ዶክተር ወዳጄነህ፤ ለአብነትም ስለዚሁ ክብር ይመሰክራሉ። በሕክምናው ሙያ ከተማሪነት ጀምሮ ያካበቱትን ልምድ መሰረት አድርገው እንደሚናገሩት አዋላጆች ለሰው ልጅ በሙሉ ክብር እንዲሰጡ መምህራኖቻቸው ያስተምሯቸው ነበር። በተለይ ለወላድ እናቶች ትልቅ ክብር መስጠት እንደሚገባቸው ደጋግመው አስተምረዋቸዋል ብለዋል።
በሕክምና ሙያ ትምህርትም ሆነ በሥራ ዓለም በቆዩባቸው ጊዜያት ለእናቶች ይሰጥ የነበረው ክብር ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ። ለአብነት የትምህርት ቤት ቆይታቸውን አስመልክተው እንደገለፁት ማህፀንና ጽንስ በሚማሩበት ጊዜ መምህራኖቻቸው ወደ ሆስፒታል ለክትትል ለሚመጡ እናቶች ክብር እንዲሰጡ አድርገው ነው ያሰለጠኗቸው።
‹‹ታካሚዋ እናት የመጨረሻ ምስኪን ልትሆን ትችላለች። ምን አልባትም ጫማዋ የተበጠሰ፣ ነጠላ ጫማ ሊሆን ሁሉ ይችላል። ለምርመራ ስትሬቸሩ (አልጋው) ላይ ስትወጣና ስትወርድ ጎንበስ ብለን ጫማዋን ማውለቅና ማጥለቅ እንደሚገባን ያስተምሩን ነበር›› ይላሉ ያለፉበትን ተሞክሮ ሲገልጹ።
አክለውም ‹‹እግሯ ላይ እብጠት መኖርና አለመኖሩን ለማረጋገጥ ስንነካት በአክብሮት ነበር›› ይላሉ። ዶክተር ወዳጄነህ እንደሚሉት ከሕክምና ሙያ ሰውን ሳይንቁ በቅንነት፣ በትህትና፣ በታማኝነት ማገልገልንና ማክበርን ተምረዋል። ይሄ የሙያ አስተምህሮ አንዲት ነፍሰ ጡር እናት ልጅዋን በሰላማዊ መንገድ መገላገል እንድትችል በማድረጉ ረገድ ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት መኖሩንም ይገልፃሉ። ከታላላቆቹ ሐኪሞችና መምህራኖቻቸው የተማሩት በታካሚዎቻቸው መካከል ልዩነትና አድሎ እንዳያደርጉ ጠቅሟቸዋል።
በአጠቃላይ ሥነ-ስርዓትን፣ ለሙያ መሰጠትን፣ ራስን መጠበቅን ከነሱ ተምረዋል። ይሄ ሁሉ እናቶች በሰላም ልጆቻቸውን እንዲገላገሉ በማድረጉ በኩል ያለው አበርክቶ የጎላ ነው። ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል በዚህ በኩል በሕክምናው መስክ በተለይም ከእናቶችና ሕፃናት ሞት ጋር ተያይዞ ብዙ ሥራ የሰራ ሆስፒታል ነው። እንደ ዶክተር ወዳጄነህ እንደሚሉት፤ የእኛ አገር አንዱ የጤና ተግዳሮት እናቶች በወሊድ ጊዜ ከደም መፍሰስ ጋር ተያይዞ የሚገጥማቸው ነው።
ሌሎች ለአስከፊው የፌስቱላ ችግር እንዲሁም ለሞት የሚያበቋቸው የጤና ችግሮችም አሉ። ከነዚህ የጤና ችግር ጋር ተያይዞ ብዙ እናቶች እንደሚሞቱም ዶክተር ወዳጄነህ ይናገራሉ። ከዚህ አኳያ ጋንዲ ባለፉት 63 ዓመታት ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎትን በመስጠት ብዙ እናቶች በሰላምና በጤና እንዲወልዱ ያደረገ ባለውለታ ሆስፒታል ነው።
ልጆች ሲወለዱ በወሊድ ጊዜ በሚገጥሙ አደጋዎች ሊታመሙና የአካል ጉዳተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንዲሁም ብዙ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው ያወሳሉ። በመሆኑም ሆስፒታሉ ለእናቶች ብቻ ሳይሆን ልጆችም ጤነኛ ሆነው እንዲወለዱና እንዲያድጉ በማድረጉ ረገድም አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በመሆኑም ሊመሰገን ይገባዋል። ሆስፒታሉ አሁን ላይ አገልግሎቱን የበለጠ ለማዘመንና ለማጠናከር እየሰራ ያለው የማስፋፊያ ሥራም አስደስቷቸዋል።
ሲስተር እታለማሁ ገብረዮሐንስ በነርስነት ሙያ 40 ዓመታት አገልግለዋል። እንዳጫወቱን፤ ተመርቀው ሥራ በጀመሩበት ሻኪሶ ለስምንት ዓመታት፤ በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ደግሞ ለሁለት ዓመታት፤ ቀሪውን 30 ዓመት ደግሞ በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሰርተው ነው በጡረታ የተሸኙት። ያኔ አንቡላንስና የሰው ኃይል ጨምሮ የሕክምና መገልገያ ዕቃ እንደ አሁኑ የተሟላ አልነበረም። ታካሚውም ቢሆን ወደ ጤና ተቋም የመምጣት ልምዱ አልዳበረም። በተለይ ገጠር ውስጥ እናቶች በአብዛኛው በቤት ውስጥ ነበር ልጆቻቸውን የሚወልዱት።
በጥቂት የጤና ባለሙያ ብዙ አገልግሎት ነበር የሚሰጠው። በመሆኑም ጫናው በባለሙያው ላይ ያርፋል። እንዲህም ሆኖ በወሊድ ጊዜ የሚሞቱ እናቶች አልነበሩም። ሐኪሞቹ ቅኖች ናቸው። ምክንያቱም ለሙያና ታካሚዎቻቸውም እንዲሁም ለሆስፒታሉ ታማኝ ናቸው። ሩህሩህና ትሑት በመሆናቸው እናቶች ልጆቻቸውን የሚወልዱት የምጡ ሕመም ብዙም ሳይታወቃቸው ነው። በጤና ተቋም መውለድም ትልቅ ፋይዳ አለው የሚሉት ሲስተር እታለማሁ ሁሉንም ልጆቻቸውን የወለዱት በጤና ተቋም ነው። በመሆኑም እሳቸውም ልጆቻቸውም ጤናማ መሆን ችለዋል።
‹‹ልጅ የሚነሳም ሆነ የሚሰጥ እግዚአብሄር ነው። እንደጠበቅነው በሰላም ሳንገላገል ብንቀርም ሆስፒታሉንም ፈጣሪንም ማመስገን ይገባናል›› ያለችን በወሊድ ወቅት ልጇን ያጣችው ወይዘሮ እየሩሳሌም ነጋሽ ናት። ወይዘሮዋ እንዳከለችው ሐኪም አይሳሳትም አይባልም ይሳሳታል። ስህተቱን ከባድና አደገኛ የሚያደርገው የሰው ነፍስ መሆኑ ነው።
“እንደ እኔ ልጇ ሞቶባት በሆስፒታሉ ለምትቆይ እናት እንክብካቤያቸው ወሳኝ ነው። አንዳንድ ሰው ከሕክምና በላይ የሚያድነው ‹ከፍትፍቱ ፊቱ› እንዲሉ የሚቀበሉበትና እንክብካቤ የሚያደርጉበት መንገድ ነው። ከምታውቁት ዕውቀት በላይ ፍቅራችሁ፣ ርህራሄያችሁ፣ ትህትናችሁ፣ ሰዎችን ይፈውሳል። ያለባችሁ ኃላፊነት ብዙ ነውና በአግባቡ ተወጡ” ብላለች።
‹‹እናት የሁሉም መገኛ ናት። እናት ስትወልድ ነው ሰውም ሰው የሚሆነው። በመሆኑም እናት ሕይወትን የምትሰጥ ድንቅ ፍጡር ናት›› ያሉን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ታሪኩ ዴሬሳ ናቸው። ዶክተሩ አምጣ፣ ወልዳና ታጥባ በምትወጣበት ደረጃ ብቻዋን የምትገለገልበት ዘመናዊ የማዋለጃ ክፍል ተዘጋጅቶላታል ብለውናል።
‹‹ተግባሩ ብቻውን ውጤታማ አይሆንም። የኅብረተሰቡም ሆነ የግል ተቋማት ድጋፍ ያስፈልገዋል። ሙያተኞቹንም ማበረታታት ያሻል። እኛ ይሄን በጎ ተግባር ስንደግፍ ቆይተናል›› ያሉን ዘንድሮ 25ኛ ዓመቱን የሚያከብረው የወጋጋን ባንክ የማርኬቲንግና ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አፈወርቅ ገብረፃዲቅ ናቸው።
እንደሳቸው በመስኩ አገልግለው በጡረታ ለተሸኙ 15 ሴቶችና ለሌሎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ሺህ ብር ያለበት የቁጠባ ደብተር አበርክተዋል። ለጡረታ ሽኝቱ 140ሺህ ብር ሰጥቷል። ሴቶችና ህፃናትን ከመደገፍና ከማብቃት አንፃር የተለያዩ መርሐ ግብሮች ቀርጾ እየሰራ ነው። ጠቀም ያለ ወለድ የሚያስገኝ ‹ዋርካ› የተሰኘው የቁጠባ ሂሳብ ይጠቀሳል።
በቅርቡ ለሐምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል 500 ሺህ ብር እርዳታ አድርጓል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በሴቶች ጤና ዙርያ እየሰሩ ላሉ ድርጅቶች 33 ሚሊዮን ብር ለግሷል።
እኛም (አዲስ ዘመን) ድጋፉ እናቶች በሰላም እንዲገላገሉና ሕይወትን እንዲያስቀጥሉ በማድረጉ ረገድ ሚናው የጎላ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥል የሚል ማሳሰቢያ በመስጠት ወሬያችንን ቋጨን!!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014