በኢትዮጵያ ተወዳጅ ከሆኑ የስፖርት አይነቶች መካከል የቦክስ ስፖርት አንዱ ነው። የቦክስ ስፖርት በኢትዮጵያ ተወዳጅ ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያ በታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ ላይ በተለያየ ጊዜ የተሳተፈችበት ስፖርት መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በዚህ ተወዳጅ ስፖርት ኢትዮጵያ እኤአ ከ2008 የቤጂንግ ኦሊምፒክ በኋላ መድረኩ የሚሳተፍ የቡጢ ተፋላሚ ማግኘት አልቻለችም።
ስፖርቱ በአገር ውስጥ የሚደረግበት እንቅስቃሴ እምብዛም ከመሆኑ በተጨማሪ ለተወዳዳሪዎች እንደ ልብ የውድድር እድል ማመቻቸት አለመቻሉም በተደጋጋሚ ይነሳል። ለዚህም የቦክስ ውድድርን ለማካሄድ የቤት ውስጥ የመወዳደሪያ መሰረተ ልማትና የፍልሚያ ሜዳ (ሪንግ) እጥረት መሰረታዊ ችግር ተደርጎ ይነሳል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለቦክስ ስፖርተኞች የውድድር እድል ለመፍጠር ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ሲሆን ለዚህም ከቤት ውጪ ባሉ የመወዳደሪያ ስፍራዎችን በማመቻቸትም ቢሆን ውድድሮች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።
በዚህ አመት በተለያዩ ክልሎችም የቦክስ ውድድሮችን ማየት እየተለመደ የመጣ ሲሆን በአዲስ አበባ ትንሿ ስታድየምም ውድድሮችን በየጊዜው ማካሄድ ተችሏል። ከነዚህም መካከል ከቀናት በፊት የተጠናቀቀው የክለቦች አንደኛ ዙር ውድድር ተጠቃሽ ነው።
የ2014 ዓ.ም የአንደኛው ዙር የክለቦች ቦክስ ቻምፒዮና በሆነው ውድድር የአዲስ አበባ ፖሊስ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኖ ማጠናቀቁ ታውቋል። ለተከታታይ አራት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ትንሿ ስታድየም በተካሄደው ቻምፒዮና በሴቶች በአንድ አይነት ኪሎ ግራም ውድድር የተደረገ ሲሆን በወንዶች በተለያዩ ስድስት ኪሎ ግራሞች ፉክክሮች ተደርገዋል።
በቻምፒዮናው የተለያዩ አምስት ክለቦች ተሳታፊ መሆናቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ኮሚኒኬሽን መረጃ ያመለክታል። ከውድድሩ የመጀመሪያ ቀን አንስቶ የተለያዩ የጥሎ ማለፍ ፍልሚያዎች የተካሄዱ ሲሆን በሴቶች ሃምሳ ሁለት ኪሎ ግራም በተካሄደው ብቸኛ ፍልሚያ ዮርዳኖስ ተራማጅ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከድሬዳዋ ከተማዋ ሀገሬ እማኙ ባደረጉት ውድድር ሀገሬ እማኙ አሸናፊ ሆኗለች፡፡
በወንድ ሃምሳ አንድ ኪሎ ግራም በተካሄደው ፍልሚ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተወዳዳሪ የሆነው የአብስራ ታደሰ በፌዴራል ፖሊሱ ተወዳዳሪ ዘካሪያስ ከድር ተሸንፏል።
በተመሳሳይ በሃምሳ ሰባት ኪሎ ግራም በተካሄደው ፉክክር የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተወዳዳሪው ሳምሶን ጌታቸው የፌዴራል ፖሊስ ተወዳዳሪውን ቢላል አስራርን ማሸነፍ ችሏል።
በሰባ አንድ ኪሎ ግራም በተካሄደው ፉክክር ደግሞ የፌዴራል ፖሊሱ ተወዳዳሪ አቤኔዘር ዳንኤል የድሬዳዋ ከተማ ተወዳዳሪውን እዮብ ነጋሽ ማሸነፉ ታውቋል።
በሰባ አምስት ኪሎ ግራም በተካሄደው ፍልሚያ ተመስገን ምትኩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ የፌዴራል ፖሊሱን ተወዳዳሪ ገዛኸኝ ሮባን ማሸነፍ ችሏል። በዳኛ ውሳኔ ወይም በዝረራ በተጠናቀቀው የሰማንያ ኪሎ ግራም ውድድር የአዲስ አበባ ፖሊስ ተወዳዳሪው ሰይፈ ከበደ የድሬዳዋ ከተማ ተወዳዳሪውን ቢኒያም ተስፋዬን ማሸነፍ ችሏል።
በዘጠና ሁለት ኪሎ ግራም የወንዶች የፍጻሜ ፍልሚያ የድሬዳዋ ከተማው ሊበን መሐመድን ከፌዴራል ፖሊሱ ሙሉቀን መልኬ ያገናኘ ሲሆን ሙሉቀን መልኬ ውድድሩን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችሏል።
ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው ይህ ውድድር አምስት ክለቦች የተሳተፉበት ሲሆን አስራ አንድ ሴቶችና ስልሳ ወንዶች በአጠቃላይ ሰባ አንድ የቦክስ ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ሆኖዋል፡፡
በአጠቃላይ የሜዳልያ ብዛትም አዲስ አበባ ፖሊስ አንደኛ በመሆን ሲያጠናቅቅ፣ የፌዴራል ፖሊስ ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን ፈጽሟል። ድሬዳዋ ከነማ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የዋንጫ ተሸላሚ መሆናቸውን የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2014