ከቢሮ እስከ ጦር ግንባር ድረስ በተግባር የተፈተነ የጋዜጠኝነት ልምድ አላቸው። ከጀማሪ ዜና ዘጋቢነት ተነስተው የሙያው ቁንጮ እስከሆነው፣ ዋና አዘጋጅነት ድረስ ደርሰዋል። በመጠሪያ ስማቸውና በብዕር ስማቸው በርካታ ጽሑፎችን ጽፈዋል። ዘግይተው በጀመሩት የድርሰት ስራም አንቱታን አትርፈዋል።
‹‹ጋዜጠኝነት የወተት ጥርሴን የነቀልኩበት ሙያ ነው›› የሚሉት አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ አጥናፍ ሰገድ ይልማ፤ ጋዜጠኛነት በዕውቀት የሚደገፍ፣ በእውነት የሚዘገብና ያለ አድልዎ የሚሠራ የተከበረ ሙያ እንደሆነ በፅኑ ያምናሉ። አንጋፋው ባለሙያ የሕይወት ሩጫቸውን ጨርሰው ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ለዛሬ የሕይወት ጉዟቸውን በአጭሩ እንቃኛለን። አጥናፍ ሰገድ የተወለደው በ1929 ዓ.ም በቀድሞው የአርሲ ጠቅላይ ግዛት ጢቾ ከተማ ነው።
በሕፃንነቱ የቄስ ትምህርትን ጨምሮ የወቅቱ የባላባት ልጆች የሚማሯቸውን ባሕላዊ የአስተዳደርና የኑሮ ሥርዓቶችን ተምሯል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በጢቾ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በንግድ ስራ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በፖለቲካ ሳይንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲፕሎማ ተመርቋል።
በ1950 ዓ.ም በመከላከያ ሚኒስቴር የጽሕፈት ኮርስ መምህር ሆኖ ተቀጠረ። ከአንድ ዓመት አገልግሎት በኋላ በኢትዮጵያ ሕዝብ አገር ፍቅር ማሕበር ስር ይታተሙ በነበሩት ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› ጋዜጣና ‹‹መነን›› መጽሔት ላይ ጀማሪ ጋዜጠኛ ሆኖ የጋዜጠኝነት ስራን ጀመረ።
ከዚያም ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› ጋዜጣ የእንግሊዝኛው ክፍል (Voice of Ethiopia) ረዳት አዘጋጅ እንዲሁም የአማርኛው ክፍል ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል። የጋዜጣውና የመጽሔቱ አሳታሚ ድርጅት በመንግሥት ትዕዛዝ ሲዘጋ የድርጅቱ ባልደረቦች ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተዛወሩ። አጥናፍሰገድም የ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ (በወቅቱ አጠራር City Desk Editor) ሆኖ ተመደበ።
በጊዜው የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ ነበር። በአብዮቱ ዋዜማ፣ በ1966 ዓ.ም፣ ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ። ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተዛውሮ በመጀመሪያ የክፍላተ አገራት ዜና ዋና አዘጋጅ፤ ቀጥሎም የአዲስ አበባ ዴስክ የዜና ክፍል ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሲሰራ ቆየ።
ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ በጋዜጦችና በዜና አገልግሎት ጨምሮ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ለ22 ዓመታት ያህል ሰርተዋል። ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ቀጥለው በሰሩበት የከተማ ልማት ሚኒስቴር፤ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነትና በከተሞች ልማትና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊነት ለአራት ዓመታት ያህል አገልግለዋል።
ጡረታ እስከወጡበት እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ የቦሌ ክፍለ ከተማ ሊቀ መንበር እንዲሁም የአውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ሰርተዋል። ጡረታ ከወጡ በኋላ ጋዜጠኞች የሆኑ ወዳጆቻቸው (ሙሉጌታ ሉሌ፣ ጎሹ ሞገሥና ሌሎችም) ‹‹ጦቢያ›› መጽሔትን አቋቁመው ስለነበር ተጋባዥ ጸሐፊ ሆነው መስራት ጀመሩ።
በ1996 ዓ.ም እርሳቸውና ባልደረቦቻቸው ‹‹ልሳነ ሕዝብ›› የተባለ ጋዜጣ አቋቁመው ከ‹‹ጦቢያ›› ጋር አብረው መስራታቸውን ቀጠሉ። እስከ ጦር ግንባር ድረስ ዘልቆ በመዘገብ (በወታደራዊው የደርግ መንግሥትና በሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ/ሻዕቢያ መካከል ጦርነት ሲካሄድ በጦር ግንባሮች ተገኝተው ዘግበዋል) በካበተውና ረጅም ዓመታትን ባስቆጠረው የጋዜጠኝነት ልምዳቸው በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲሻሻል የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በተለይም በጦቢያና በልሳነ ሕዝብ ጋዜጦችና መጽሔቶች አማካይነት፣ ከሙያ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን፣ ሕዝብ እውነተኛ የሥልጣን ምንጭና ባለቤት መሆኑንና ነፃው ፕሬስ የሕዝብ አንደበት፣ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እንደሚያገለግል በማሳወቅ ሙያዊ ተጋድሎ አድርገዋል።
ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ስለጋዜጠኝነት ጅማሬያቸውና ጉዟቸው እንዲሁም ገጠመኞቻቸው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል። ‹‹ … ጋዜጠኝነት ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ የወተት ጥርሴን የነቀልኩበት ሙያ ነው። ዛሬም ጋዜጠኛ ነኝ
እላለሁ። አሁንም አንዳንድ ጽሑፎችን ጋዜጦች ላይ እጽፋለሁ። ጋዜጠኝነትን ከጀመርኩ 60 ዓመት ሊሆነኝ ነው። በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ራሴን እንደተሳታፊ ሆኜ ያየሁበት ጊዜ በ1966 ዓ.ም ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኜ የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት ነቅፌና ሕዝባዊ አብዮቱን ደግፌ የተሳተፍኩበትና ያገለገልኩበትን ጊዜ ነው።
በእርግጥ ያ ጊዜ ‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ወርቃማው ዘመን› እለዋለሁ … ከየካቲት ወር 1966 ዓ.ም ጀምሮ ቀደም ሲል የነበረው ጥብቅ የሳንሱር ሥርዓት ቀረ … በተለይ ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ተፈላጊ ሆኖ ነበር … ጋዜጠኞች፣ በምንጽፈው ስህተት፣ ብዙ ጊዜ በተግሳጽ ነበር የምንታለፈው። ስህተቱ ከበድ ካለ፣ በገንዘብ ተቀጥተን ወደ ሌላ ክፍል እንዛወር ነበር እንጂ፣ ተከ’ሰንና ተፈርዶብን ወህኒ የተወረወርንበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም … ‹‹በ1956 ዓ.ም. እንደነበር ትዝ ይለኛል።
የሶማሊያ መንግሥት የ‹‹ታላቋ ሶማሊያ›› ግንባታ ቅዠቱን ለማሳካት፣ የኦጋዴንን አውራጃ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል፣ በመደበኛ ጦርነትና በሰርጎ ገብ ግጭት ሲሞክር ነበር። የሶማሊያ ሰርጎ ገብ ሽፍታን በጋዜጣው መጀመሪያ ገጽ ላይ በሚያሳይ አንድ የካርቱን ምስል ሥር ‹‹One of the Somali Expansionist/ ከሶማሊያ ገንጣይ ወንበዴዎች አንዱ›› በማለት የተጻፈውን መግለጫ፣ ግርማዊነታቸው በስታዲየም ተገኝተው፣ ለአንድ በስፖርት አሸናፊ ለሆነ ቡድን አምበል ዋንጫ ሲሸልሙ ከሚያሳየው ፎቶግራፍ መግለጫ ጋር በማሳከር ‹‹His Imperial Majesty Haile Sillasse I Awarding A Trophy to One of the Somali Expansionist/ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ለአንድ የሶማሊያ ገንጣይ ወንበዴ ዋንጫ ሲሸልሙ›› ተብሎ ታትሞ ወጣ።
በዚህ፣ ይሆናል ተብሎ በማይታሰብ ስህተት ምክንያት፣ የ‹ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ከደመወዝ 400 ብር፤ ረዳት አዘጋጆች ደግሞ አንድ አንድ መቶ ብር ተቀጥተናል … ›› ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ የጋዜጠኝነት ሙያቸውን ያዳበሩባቸውን ሥልጠናዎችን አግኝተዋል። በኬንያ፣ በሩማንያና በዩጎዝላቪያ በመስክ የሥራ ጉብኝት የታገዙ ሙያዊ ሥልጠናዎችን ወስደዋል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ከጋዜጠኝነት ሙያቸው በተጨማሪ በደራሲነታቸውም ይታወቃሉ። በአጠቃላይ ደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ ይልማ እስካሁን ድረስ ሰባት የልብ ወለድ፣ የታሪክና የግለ ታሪክ፣ መጽሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል።
መጽሐፎቻቸውም፡- 1. ‹‹የበደል ካሣ›› – በ1997 ዓ.ም 2. ‹‹የእንስሳት ዐመፅና ድርድር፣ ከሰው ሰውኛ ሥርዓት ጋር›› – በ2003 ዓ.ም 3. ‹‹አቤቶ ኢያሱ ፣ አነሣሥና አወዳደቅ›› – በ2006 ዓ.ም 4. ‹‹የሕይወቴ ምስጢር ፣ የተፈተነ ጋብቻ ኢዮቤልዩ›› – በ2008 ዓ.ም 5. ‹‹አገር የፈታ ሽፍታ›› – በ2009 ዓ.ም 6. ‹‹የፖለቲካ አሽሙር›› – በ2011 ዓ.ም 7. ‹‹የታሪክ ቅርስና ውርስ ፣ አበበ አረጋይ (ራስ)›› – በ2011 ዓ.ም ናቸው።
የመጀመሪያ የድርሰት ስራቸው ‹‹የበደል ካሳ›› የተሰኘ ታሪካዊ ልብወልድ ነው። ዶክተር ታደለ ገድሌ የጋዜጠኛና ደራሲ አጥናፍ ሰገድ ይልማን የሕይወት ጉዞ በቃኙበት ‹‹የዳማ ጌታ›› ጽሑፋቸው እንደጠቀሱት፤ ‹‹የበደል ካሣ›› የተሰኘው መጽሐፍ፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የተከሰተ ማሕበራዊ ችግርና ችግሩንም ለማስወገድ የገጠመውን ውጣ ውረድ የሚያሳይ ሲሆን አገሪቱን ይገዛ የነበረው የፊውዳል ሥርዓት በሕዝቡ ላይ ያደረሰውን በደል፣ የአስተሳሰብና የአመለካከት ተፅዕኖ እንዲሁም ሥርዓቱ ከተወገደ በኋላ የተገኘውን አንፃራዊ የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያወሳ ነው።
ጋዜጠኛና ደራሲ አጥናፍሰገድ ስለድርሰት ስራዎቻቸው ሲናገሩ ‹‹ … ወዳጆቼ ‹አንተ የድርሰት ችሎታ እንዳለህ አላወቅክም፤ ጥሩ ጸሐፊ ነህ› ይሉኝ ነበር።
በአቤቶ ኢያሱ እና በራስ አበበ አረጋይ ታሪክ ላይ ያተኮሩትን ጽሑፎቼን ወደ መጽሐፍ እንድቀይራቸው ወዳጆቼ ሲመክሩኝ እነሀዲስ ዓለማየሁን የመሰለ አንጋፋ ደራሲ ባለበት አገር ላይ የእኔ ደራሲነት ከምን የመጣ ነው? ሌሎች ባለሙያዎች አንቱ የተባሉበትን ሙያ እኔ ልደፍረው አይገባም ብዬ ራሴን ሰብስቤ ቆይቸ ነበር። በኋላ ላይ ግን በጋዜጠኝነቱ ካገኘሁት ክህሎት እንዲሁም በወዳጆቼ ማበረታቻ ምክንያት ጽሑፎቼ በመጽሐፍ መልክ ሊታተሙ ችለዋል።
መጽሐፎቹን ከጻፍኩ በኋላ ግን የድርሰት ችሎታ እንዳለኝ ተገንዝቤያለሁ …›› ይላሉ። ከ20 ዓመታት በላይ የቀሰሙት የጋዜጠኝነት እውቀትና ያበለጸጉት ክህሎት (በተለይም የምርመራ ጋዜጠኝነት) ለድርሰት ሥራቸው ጽኑ መሠረት እንደሆናቸው ይናገራሉ።
በርካታ ምንጮችን ተጠቅመውና አነጋግረው የጻፏቸው ‹‹አቤቶ ኢያሱ፣ አነሳስና አወዳደቅ›› እንዲሁም ‹‹የታሪክ ቅርስና ውርስ፣ አበበ አረጋይ (ራስ)›› የሚሉት ታሪካዊ የጥናት መጽሐፎቻቸው ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን አትርፈውላቸዋል።
በተለይ ‹‹አቤቶ ኢያሱ፣ አነሳስና አወዳደቅ›› የተሰኘው መጽሐፋቸው ለምርመራ ጋዜጠኝነት አርዓያነት ያለው ተግባር ጭምር በመሆኑ የወርቅ ሽልማት አስገኝቶላቸዋል። የመጽሐፉ የመጀመሪያው እትም በአንድ ሳምንት ውስጥ ተሰራጭቶ እንዳለቀና ሁለተኛው እትምም በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደተጠናቀቀ መረጃዎች ያመለክታሉ።
እንደ ዶክተር ታደለ ምስክርነት፤ ‹‹አገር የፈታ ሽፍታ›› የተሰኘው የታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፋቸው በእውነተኛ ድርጊት ላይ ተመርኩዞ የተሠራ ሲሆን በድንገተኛ ጠብ በተከሰተ ግድያ ምክንያት አባት ልጁን ከእሥራት ለማዳን የከፈለውን መሥዋዕትነት፤ ልጁ ደግሞ፣ ቢዘገይም በፍርድ ፊት እውነቱን በማውጣት አባቱን ከሞት ቅጣት ለማትረፍ ያሳየውን ቁርጠኛነት ያመለከተበት ሥራ ነው።
መጽሐፉ፣ ሰዋሰዋዊ ሥርዓትን በመጠበቅ፣ ሆሄያትንና ሥርዓተ ነቁጥን በአግባቡ በመጠቀም የበኩሉን ጥረት አድርጓል። 24 ምዕራፎችን ከፎቶግራፎችና ከልዩ ልዩ ሰነዶች ጋር አካቶ በ312 ገፆች በያዘውና ‹‹የሕይወቴ ምስጢር፣ የተፈተነ ጋብቻ ኢዮቤልዩ›› ብለው በሰየሙት ግለ ታሪካቸው ከውልደታቸው ጀምረው ትምህርታቸውን፣ የአስተማሪነታቸውንና የጋዜጠኝነታቸውን ጉዞ፣ ከባለቤታቸው ጋር የነበራቸውንና ያላቸውን የትዳር ሕይወታቸውን እንዲሁም በመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ የነበራቸውን ኃላፊነት ከአገሪቱ ታሪክና ፖለቲካ ምሕዋር ጋር አስተሳስረው አቅርበውበታል።
ይህ መጽሐፋቸው በሕይወት ጉዟቸው ያሳለፉትን በጐውንና ክፉውን ገጠመኝ የገለፁበት ብቻ ሳይሆን በግለታሪክ አጻጻፍ፣ ባልተለመደ ሁኔታ የራሳቸውን ስሕተት ጭምር በድፍረት የገለፁበትና ለተከታዩ ትውልድ አስተማሪ በሚሆን መልኩ ያሳዩበት ነው። የደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ ሰባተኛ መጽሐፋቸውና የስመ ጥሩን አርበኛ ራስ አበበ አረጋይን ታሪክ ሰንዶ የያዘው ስራቸው (‹‹የታሪክ ውርስና ቅርስ ፣ አበበ አረጋይ (ራስ)) በ2011 ዓ.ም ታትሞ ለገበያ በቅቷል።
ይህ ስራቸው በሚያዝያ 2006 ዓ.ም እንደታተመው ‹‹አቤቶ ኢያሱ፣ አነሳስና አወዳደቅ›› መጽሐፋቸው ሁሉ ጥልቅ ምርመራ የተደረገበት ታሪካዊ መጽሐፍ ሲሆን ከባለታሪኩ ከራስ አበበ ባለቤት እማሆይ ቆንጂት አብነት፣ ከልጃቸው ከልጅ አየለወርቅ አበበና አብረዋቸው ከሰሩ ወዳጆቻቸው ጋር ከተደረጉ ጥልቅና ሰፋፊ ቃለምልልሶች እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች በተገኙ መረጃዎችና ማስረጃዎች የዳበረ መጽሐፍ ነው። ‹‹ … መጽሐፉ ቀደም ሲል በምርመራ ጋዜጠኝት ካከማቸኋቸውና ከሌሎች መረጃዎች ተሰብስቦና ተጣርቶ የተጻፈ ስራ ነው። የራስ አበበን ታሪክ ቀደም ሲል በ‹‹ልሳነ ሕዝብ›› መጽሔት ላይ በአምስት ተከታታይ ክፍሎች አቅርቤ ነበር።
ጽሑፎቹን ያነበቡ ሰዎች ‹ራስ አበበ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው። መረጃ ጨምረህ አስፋፍተህ ጻፈው› ብለው በመጽሐፍ መልክ እንድጽፈው ጠየቁኝ። እኔም ወዲያውኑ ነው ከ16 ዓመታት በፊት መረጃ ስብሰባ የጀመርኩት። ከባለቤታቸው ከእማሆይ ቆንጂት፣ ከልጃቸው ልጅ አየለወርቅና አብረዋቸው ከሰሩ ሰዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጌያለሁ … እማሆይ ቆንጂት የራስ አበበን መዋዕለ ዜና ጽሑፍ ሰጡኝ።
ከአርበኞች ማሕበርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከልም ተጨማሪ መረጃዎችን አገኘሁ … ከመረጃ ምንጮቼ ያገኘሁት ታሪክ ራስ አበበ አረጋይም ሆኑ ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ለኢትዮጵያ ምን ያህል መስዋዕትነት እንደከፈሉ ሲያስረዳኝ እንባዬ እየመጣ ያስለቅሰኝ ነበር … ይህ ባለ 400 ገጽ መጽሐፍ በጥንቃቄ የተሰራ ስራ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በሆኑ ወዳጆቼም ተገምግሞ ይሁንታ የተሰጠው ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያዊነት በጎጠኝነት ተመንዝሮ እርስ በእርሳችን በምንናቆርበት ወቅት ለኢትዮጵያ ነፃነትና አንድነት ዋጋ የከፈሉ እንደነራስ አበበ አረጋይ ያሉ አባቶችና እንደነእማሆይ ቆንጂት አብነት ያሉ እናቶች እንደነበሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማሳወቄ ታላቅ ክብርና ኩራት ይሰማኛል፤ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ለንባብ በማብቃቴ በጣም ደስ ይለኛል …›› በማለት መጽሐፉ በታተመበት ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። 70 ዓመት ሊሞላቸው ጥቂት ሲቀራቸው መጽሐፍ መጻፍ የጀመሩት ደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ‹‹ … ገና በልጅነቴ መጽሐፍ መጻፍ ብጀምር ስራዎቼን ጳውሎስ ኞኞን፣ ብርሃኑ ዘሪሁንን፣ በዓሉ ግርማንና ሌሎች አንጋፋ ደራሲያንን የማሳየትና የማስገምገም እድል ነበረኝ። ይህንን ባለማድረጌና ዘግይቼ በመጀመሬ በጣም ይቆጨኛል።
መሞከርና ለታላላቆች ማሳየት ጠንካራ ያደርጋል። እስካሁን ድረስ 20ና 30 መጽሐፍት መጻፍ ሲገባኝ የጻፍኩት ግን ሰባት ብቻ ነው … ›› በማለት ቀደም ብሎ መጻፍ የመጀመርና በየጊዜው አቅምን እያጎለበቱ በሂደት ጎበዝ ደራሲ የመሆን ተምሳሌት አድርገው የሚጠቅሷቸውን፤ ከ50 በላይ መጽሐፍትን ጽፈውና ተርጉመው ያለፉትን የአንጋፋውን ጋዜጠኛና ደራሲ ማሞ ውድነህን ተሞክሮ በመልካም አርዓያነት ያስታውሳሉ።
‹‹በእድሜ ዘመኔ ያየኋቸውና ያለፍኩባቸው ሥርዓቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ምንጭና ባለቤት ለማድረግ ሳይሆን ‹እኔ ልግዛ፤ የሞትንም እኛ፤ የገደልንም እኛ› እየተባለ ኀዘንና ለቅሶ የበዛበት ሕይወት እንድናሳልፍ እያደረጉ ናቸው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያመጡት ለውጥ የለም።
በእርግጥ እነ ዐቢይ ወደሥልጣን የመጡበት መንገድ ከዚህ በፊት ከነበረው በትንሹም ቢሆን ለየት ይላል … ‹የሞትንም እኛ የቀረንም እኛ› እየተባለ እስካሁን ድረስ መቀጠሉ አሳዛኝ ነው! ካለፈው ስህተታችንና ከከፈልነው መስዋዕትነት እንዴት አንማርም? መቼ ነው የምንማረው? እኛ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግር የማይፈታ እንቅስቃሴና አመፅ ማቆም የምንጀምረው መቼ ነው? ሌሎች አገራትም ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር አልፈዋል፤ ብዙዎቹ አገሮች ግን ከችግሩ ተላቀዋል።
የሦስት ሺ ዓመታት የነፃነት ታሪክ ያለን እኛ ግን በዚህ ረገድ የመጨረሻዎቹ ኋላቀሮች ሆነናል። መጋደላችን ይቁም! መንግሥት ኃላፊነቱን በአግባቡ በመጠበቅ የአስተዳደር መዋቅሩን በተሻለ ብቃት መምራት ይገባዋል።
ሕዝቡም ሃሳቡን የሚገልጽበት መዋቅር ያስፈልገዋል … ›› በማለት ስለኢትዮጵያና ሕዝቧ የታዘቡትን ቁጭታቸውንና መፍትሄ ነው ያሉትን ምክረ ሃሳባቸውን ተናግረዋል።
ልምዳቸውን ለማካፈል የማይሰስቱት፣ የወጣት ደራስያንን ሥራዎች በማበርታት የሚተባበሩትና በየመድረኩ የአንጋፋ ጋዜጠኞችንና ደራስያንን ታሪኮች በመዘከር የሚያብራሩት ጋዜጠኛና ደራሲ አጥናፍሰገድ፤ ለበርካታ ደራሲያን የአርትኦት ድጋፍ በማድረግ ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በጋዜጠኝነትና ድርሰት ሥራዎቻቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦም በ2008 ዓ.ም ‹‹የበጎ ሰው›› ሽልማትን ተቀብለዋል።
ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አልማዝ ስነ ጊዮርጊስ ጋር ፈተናዎችን ተቋቁመው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ካቆዩት ትዳራቸው አምስት ልጆችን አፍርተዋል፤ የልጅ ልጆችንም አይተዋል።
ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም አርፈው ሥርዓተ ቀብራቸው በአዲስ አበባ ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም እና ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014