አዛውንቱ በክረምት

ድንገት ለተመለከታቸው የ85 ዓመት የእድሜ ባለጠጋ አይመስሉም። ልክ እንደ ጎልማሳ ሰውነታቸው የጠነከረ ነው። ፊታቸውን ላስተዋለ ግን ውስጣቸው በእጅጉ እንደተጎዳና እንደታመመ ያሳብቅባቸዋል። ለዚህም ይመስላል ወደ ሕክምናው መጥተው በጎ ፈቃድ ከሚወስዱ ተጠቃሚዎች መካከል የተቀመጡት። እንዲሁ ሲታዩ የእግር ሕመም ያጋጠማቸው አይመስሉም። ጠጋ ብዬ ስጠይቃቸው ሕመሙ ውስጣዊ በመሆኑ በእጅጉ እንደባሰባቸውና አላንቀሳቅስ እንዳላቸው አጫወቱኝ።

አዛውንቱ ወልደሰንበት አስፋው ትናንትን ሲያስቡት ጀግናና ሠርተው የማይደክማቸው ነበሩ። ጤናቸውንም ቢሆን በአግባቡ ይጠብቃሉ። ከሱስ የጸዱ ወጣት ናቸውና ብዘዎች የሚወዷቸው ሠራተኛ ነበሩ። ይህ ትጋትና ብርታት ብዙ አትርፎላቸዋል። የወር ተቀጣሪ ቢሆኑም በቀን ገንዘብ የሚሰጧቸው በርካቶች እንደሆኑ ያስታውሳሉ። የዛኔ ‹‹አይዞህ በርታ›› የሚላቸው ብዙ ነው።

በወጣትነታቸው ከሥራቸው ጎን ለጎን በትምህርቱም ለመዝለቅ ሞክረዋል። በግዜው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት እርሳቸው ብቻ ነበሩ። ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ እንደፈለጉት አላዘለቃቸውም። እንዲያም ሆኖ በዘመናዊና በአብነት ትምህርቱ ትንሽም ቢሆን እውቀት ጨብጠዋል። ትምህርቱ በሕይወታቸው ብዙ ለውጦችን አምጥቷል። እሳቸው በአስኳላው እስከ ስድስተኛ መዝለቃቸውና በአብነቱ ትምህርት ዳዊትን መድገማቸው ልጆቻቸውን በትምህርት እንዲደግፉ አስችሏል። በሌላ በኩልም የተማሩበት ጊዜ በመንግሥት ደረጃ የተሻለ የሥራ ቅጥር ጭምር የሚያገኙበት በመሆኑ አማራጮችን በቀላሉ እንዲያገኙ ዕድል ሰጥቷል። እሳቸው የወጣትነት ጊዜያቸውን ከቅጥር ነፃ ሆነው እየተዘዋወሩ ለመሥራት ቢጠቀሙበትም።

ይህ ጊዜያቸው ለሰዎች ደብዳቤ በመጻፍ በቂ የሚሉትን ገንዘብ የሚያገኙበት ነበር። ቤተሰባቸውን በአግባቡ ጭምር የመሩበት ወቅት ሆኖም አልፏል። ውሎ አድሮ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሠርተው እንደበፊቱ የሚያድሩበት አልሆነላቸው። አጋጣሚው ኑሯቸውን ከእጅ ወደአፍ አደረገው። በኋላ ላይ ግን ቋሚ ሥራ የግድ እንደሚያስፈልጋቸው ተረዱ። እሳቸው እንዲህ ቢያስቡም ጊዜው ደግሞ የሚፈልጉትን ሊሰጣቸው አልወደደም። እናም ምርጫቸው ባይሆንም ኑሮ አስገድዷቸው የጥበቃ ሠራተኛ ሆኑ። የገቢ ምንጫቸውን ከፍ ለማድረግም በቋሚነት ከተቀጠሩበት ሌላ ሁለት ሦስት ቦታዎች ላይ ይህንኑ ሥራ ማከናወኑን ተያያዙት።

እድሜ እየገፋ ጉልበት መድከም ሲጀምር ግን የጀመሯቸው የሥራ አማራጮች ሊቀሩ ግድ ሆነ። በወቅቱ በአንድ ሆስፒታል የጀመሩትን የጥበቃ ሙያ በሁለት ሦስት ቦታ ማስፋት ቢሹም ሊሆንላቸው አልቻለም። ይህ ጊዜ ግን እንዳለፉት ዓመታት የሚጨናነቁበት አልነበረምና አምላካቸውን አብዝተው ያመሰግናሉ። ልጆቻቸውን የራሳቸው ጌታ እንዲሆኑ አስችለዋልና ለእሳቸውና ለባለቤታቸው ጡረታቸው ብቻ በቂ ነበር። ትንሽ ተፈተንኩበት የሚሉት ከሥራቸው ጋር በተያያዘ የገጠማቸው ችግር ነው።

አዛውንቱ ወልደሰንበት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ከ10 ዓመት በላይ አገልግለዋል። በሌሎች ሆስፒታሎችም ከዚህ ያልተናነሰ ዓመት ሠርተዋል። ረጅሙን የሥራ ጊዜያቸውን ያሳለፉት የጥበቃ ሙያ ላይ ነበር። ይህ ሥራቸው ለኑሯቸውና ለቤተሰቦቻቸው መሠረት ሆኖ ቢዘልቅም ጡረታ ከወጡ በኋላ ግን በእጅጉ እንዲፈተኑ አድርጓቸዋል። በዚህ ሥራ መቆየታቸው ከፍተኛ የጤና እክል አስከትሎባቸዋል። በአብዛኛው የጥበቃ ሥራቸው ምሽት ቢሆንም አንዳንዴም የቀን ጭምር ይሠራሉና በሁለቱም ፈረቃ ብርዱን የሚገፉት አልሆነላቸውም። በዚህም ለእግርና እጅ ሕመም ተዳርገዋል። በተለይ እንዲህ ክረምት ሲሆን ሕመሙ በቀላሉ የሚቋቋሙት አይሆንም።

የእግራቸው ሕመም 25 ዓመት ሙሉ ያሰቃያቸው ጡረታ ሳይወጡ ጀምሮ ነው። ያኔ ሆስፒታሉ ቅርባቸው ስለነበር በቀላሉ ታክመው መፍትሔ ያበጁለታል። ዛሬ ግን እንደዚያ ባለመሆኑ እጃቸውን ጨምሮ እያመማቸው ነው ። አሁንም ድረስ ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊያገኙለት አልቻሉም። የዘንድሮ ብርድ ውስጣቸው ገብቶ ያንሰፈስፋቸው ይዟል። የእግር ሕመማቸው እንደልባቸው ተዘዋውረው እንዳይሠሩ ገድቧቸዋል። የእጃቸው ሕመም ደግሞ ቤት እንኳን ተቀምጠው እንዲሠሩ አልፈቀደላቸውም። በተለይ አሁን ክረምት በከበደ ጊዜ በብዙ እየተፈተኑ ነው። እጃቸው በወጉ ብር እንኳን አይቆጥርም። በተለይም ቀኝ እጃቸው ምግብ ለመመገብ፤ ከዘራቸውን ጨብጦ ለመያዝ ጭምር ‹‹እንቢኝ›› ብሏቸዋል። ዘወትር ጠዋት እጃቸው ሱስ እንዳለበት ሰው ይንቀጠቀጣል። ምንም ይሁን ለመያዝ ሲሞክሩ ያርገፈግፋቸዋል።

አዛውንቱ ወልደሰንበት ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ አየር ጤና አካባቢ ነው። ከጡረታ በኋላ ችግራቸውን ለማስረዳትና መፍትሔ ለመሻት ያልሄዱበት ሆስፒታል የለም። እሳቸው እንደሚሉት የሕክምና ባለሙያዎቹ እንደቀድሞው በቶሎ አልተቀበሏቸውም። ችግራቸውን በጥልቀት አይተውም ለመፍትሔው አልተሯሯጡም። ይህን አጋጣሚ በክፋት አላዩትም። እንዲህ የሆነው በሥራ ክብደት መሆኑን ይረዳሉ። እንዲህ ሲሆን እያመማቸውም ቢሆን ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ። ይህንን በተደጋጋሚ ያዩና ድነው ማየትን የሚፈልጉ ባለሙያዎች ግን ይህቺን ቀን በጉጉት ጠበቋት፤መፍትሔ ያገኛሉ በሚልም ካሉበት ስፍራ ጠሯቸው።

ዕለቱ እንደ ሀገር የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ የሚጀመርበትና ለብዙዎች መፍትሔ ለመስጠት የታቀደበት ነው። እናም እሳቸውም አንዱ ሆነው ተገኝተዋል። ካለፈው አንጻር ብዙ የተመቻቹ ነገሮች እንዳሉም ተገንዝበዋል። እናም መፍትሔ አግኝተው ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱም ተስፋ ሰንቀዋል።

‹‹ማንኛውንም ታካሚ ለመታከም መልካም የሆነ አቀባበልን ይሻል። ‹‹ከፍትፍቱ ፈቱ›› የሚባለውን ብሂል ይከተለዋል። ምክንያቱም ከሕክምናው ይልቅ ፊታቸው የበራና የሚንከባከቡ ሰዎች ስናገኝ ሕመማችን ይታገሳል። በአግባቡ ሃሳባችንን፣ ሕመማችንን ገልጸንም በቂ ሕክምና እንድናገኝ እንሆናለን። ስለዚህም ዛሬ ያየሁት ይህንን በመሆኑ መፍትሔ አግኝቼ መመለስ ባልችል እንኳን ተደስቻለሁ።›› ያሉን አዛውንቱ ወልደሰንበት፤ ይህ ጊዜ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎችን ተስፋ እንደሚያለመልም አምናለሁ ብለውናል። እኛም ‹‹ያሰባችሁት ይሙላ፤ በሐኪሞችም በርካቶች የሚፈውሱበት ይሁን›› ስንል መልዕክት አስተላልፈናል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You