የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ተጨማሪ የባህል ስፖርቶችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ህግና ደንብ እንዲዘጋጅላቸው ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል። ፌዴሬሽኑ የሚያዘጋጀው አገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ቻምፒዮና እና የባህል ፌስቲቫል በተያዘው ሳምንት መጨረሻ በደብረብርሃን ከተማ አስተናጋጅነት እንደሚጀመርም አሳውቋል።
የማንነት መገለጫ የሆኑት የባህል ስፖርቶች ከሕብረተሰቡ የዕድገት ደረጃ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ሕግና ደንብ ተዘጋጅቶላቸው በዘመናዊ መልክ መካሄዳቸው ለተዘውታሪነትና ለስፖርቱ ዕድገት ጠቃሚ እንደሆነ ይታመናል።
የበርካታ ባህሎችና እሴቶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያም በየአካባቢው የሚዘወተሩና ወቅትን ጠብቀው የሚደረጉ ባህላዊ የስፖርት ውድድሮች በርካታ ናቸው። ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ ባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ህግና ደንብ ወጥቶላቸው ከወረዳ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ በዘመናዊ መንገድ የሚመሩት 11 የስፖርት ዓይነቶች ብቻ ናቸው።
እነርሱም፤ ትግል፣ ገና፣ ባለ 12 እና 18 ጉድጓድ ገበጣ፣ ፈረስ ጉግስ፣ ፈረስ ሸርጥ፣ ኮርቦ፣ በሻህ፣ ቡብ፣ ሁሩቤ እና ቀስት ናቸው። ይሁን እንጂ ከ293 በላይ የሚሆኑ የባህል ስፖርቶች እስካሁን ሕግና ደንብ ያልወጣላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይሁን ኃይሌ ይጠቁማሉ።
በዚህ ዓመትም የስፖርቶቹን ቁጥር ወደ 15 ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፤ ተጠንተው ሕግና ደንብ እንዲዘጋጅላቸው ለማድረግ ስፖርቶቹ ከሚዘወተርባቸው ክልሎች ጋር እየተሰራ ነው።
ከዚህ ባሻገር ከባህል ስፖርቶች ውድድር ጎን ለጎን በሚካሄዱ የባህል ፌስቲቫሎች ላይ ክልሎች ያልታወቁ ስፖርቶችን ለሌሎች የማሳየት የማስተዋወቅተግባራት ይከናወናሉ።
የዘመናዊ ስፖርት መሰረት የሆኑት የባህል ስፖርቶች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ባሉባቸው አገራት በስፋት ይገኛሉ። እነዚህ ስፖርቶች በተለይም በአርሶ እና አርብቶ አደሩ ማሕበረሰብ ዘንድ በስፋት ቢዘወተርም፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ግን ውድድሮች ይዘጋጃሉ።
ዘንድሮም ለ19ኛ ጊዜ የባህል ስፖርቶች ቻምፒዮና እንዲሁም ለ15ኛ ጊዜ የባህል ፌስቲቫል በአማራ ክልል አዘጋጅነት በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃን ከተማ ይደረጋል። ውድድሩ ‹‹ባህላዊ እሴቶቻችንን ማጎልበት ለጠንካራ አገራዊ አንድነታችን›› በሚል መሪ ቃልም ይታጀባል።
በ10 የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄደው ውድድሩ፤ የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን እንደሚከተልም ፌዴሬሽኑ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ከየካቲት 6-13/2014ዓም በሚቆየው ውድድርና ፌስቲቫል ላይም ከትግራይ ክልል በቀር አዲሱን የደቡብ ምዕራብ ክልል ጨምሮ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉበት መሆኑም ተገልጿል።
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የማሕበረሰብ ስፖርቶች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በቀለ፤ ስፖርቱ እያደገ መሆኑን ባለፉት ዓመታት የተካሄዱ የባህል ስፖርት ቻምፒዮናዎች እንዲሁም በየክልሉ የሚካሄዱ የውስጥ ውድድሮች አመላካች እንደነበሩ ጠቁመዋል።
ጃፓናውያን የባህል ስፖርታቸው የሆነውን ቴኳንዶን በመላው ዓለም ማስፋፋት እንደቻሉት ሁሉ በኢትዮጵያም አንድ የባህል ስፖርት ተመርጦ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ለማድረግ በሚኒስቴሩ ታቅዶ የሚሰራ መሆኑንም ጨምረው አመላክተዋል።
የባህል ስፖርቶችን በማሳደግና ማስተዋወቅ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ስፖርቱን ከማዘውተር ባለፈ በማቀራረብና በማስተዋወቅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ከውድድሩ ዓላማዎች መካከል አንዱ ነው።
በመሆኑም ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ የውስጥ ውድድሮችን በማካሄድ ወደ አገር አቀፍ ውድድር ይሸጋገራል። በዚህ ውድድር ላይም ከ900 በላይ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ተካፋይ እንደሚሆኑ ታውቋል።
አዘጋጁ የሰሜን ሸዋ ዞን በጦርነት ውስጥ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ያለበትን ሰላማዊ ሁኔታ ለማሳየት ውድድሩ እንደ መልካም ገጽታ ግንባታ እንደሚታይም በመግለጫው ተጠቁሟል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተዘጋጀና አገራዊ ጥሪን ተቀብለው ወደ አገራቸው የመጡ ዲያስፖራዎች የሽኝት መርሃ ግብር የካቲት 6/2014ዓም እንደሚካሄድም ታውቋል። በመስቀል አደባባይ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በሚኖረው ዝግጅት ስፖርታዊና ባህላዊ ክንዋኔዎች ይኖራሉ።
ይኸውም ማሕበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ እንዲሁም የባህል ስፖርቶች (የገና ጨዋታ፣ ገበጣ እና ፈረስ ግልቢያ) እንዲሁም የገመድ ጉተታ ውድድሮች ይኖራሉ።
ከዚህ ጎን ለጎን የቡና ጠጡ መርሃ ግብርም ይኖራል። ዲያስፖራው ስለ አገሪቷ ስፖርት ግንዛቤ እንዲጨብጥ፣ የባህል ስፖርቶችን እንዲያውቅ እንዲሁም አገሪቷ ሰላም መሆኗን ለተቀረው የዓለም ሕዝብ ለማንጸባረቅ ይቻላል። ለዚህም የሚሆነው አስፈላጊው ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2014