ኢትዮጵያዊው የኦሊምፒክ የአስር ሺ ሜትር ቻምፒዮን አትሌት ሰለሞን ባረጋ የውድድር አመቱን በቤት ውስጥ የዓለም ክብረወሰኖች ለመጀመር መዘጋጀቱ ታውቋል።
ሰለሞን ከቶኪዮ 2020 የኦሊምፒክ ድሉ በኋላ በተያዘው የፈረንጆች ወር አጋማሽ የዓለም የአትሌቲክስ የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች የወርቅ ደረጃ በተሰጠው በፈረንሳይ ሌቪን የሦስት ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል እንደሚሮጥ የውድድሩ አዘጋጆች አሳውቀዋል።
የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በሦስት ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ሦስተኛው የዓለማችን ፈጣን አትሌት ሲሆን ይህን ድንቅ ብቃት ያሳየውም ባለፈው አመት 7:26:10 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ነበር።
የሃያ አንድ አመቱ ድንቅ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ባለፈው አመት በሌቪን ያደረገውን ውድድር ከሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጌትነት ዋለ ቀጥሎ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለ ነው፤ አሸናፊ ሆኖ የጨረሰው አትሌት ጌትነት ዋለ 7:24:98 የሆነ ሰዓት ማስመዝገቡ ይታወሳል።
ይህም ለረጅም አመታት በኬንያዊው አትሌት ዳንኤል ኮመን ተይዞ ከነበረው 7:24:90 ሰዓት በስምንት ማይክሮ ሰከንድ የዘገየ ነበር። ሰለሞን ባለፈው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ያሳየውን አስደናቂ ብቃት ተከትሎ ዘንድሮ ወደ ሌቪን ውድድር ሲመለስ ይህን ክብረወሰን ያሻሽላል ተብሎ ተጠብቋል።
ሰለሞን ባለፈው አመት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ድሉን ከማጣጣሙ አስቀድሞ በዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ቶረን ላይ አሸንፏል፡፡ በዚያ ውድድር የርቀቱን የራሱ ምርጥ ሰዓት 3:32:97 አስመዝግቧል። በተመሳሳይ ማድሪድ ላይም ማሸነፉ አይዘነጋም።
ሰለሞን በሌቪን የሚጠብቀውን ውድድር ካደረገ ከአምስት ቀናት በኋላ ወደ ቶረን አቅንቶ በኮፐርኒከስ ካፕ ሌላ የቤት ውስጥ ውድድር እንደሚያደርግ የዓለም አትሌቲክስ ድረ ገጽ መረጃ ጠቁሟል።
በዚህ ውድድርም ባለፈው አመት ሌቪን ላይ በሦስት ሺ ሜትር ሁለተኛውን የዓለም ፈጣን ሰዓት ቀዳሚ በመሆን ካጠናቀቀው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ኦሊምፒያን ጌትነት ዋለ ጋር ዳግም የሚፎካከሩ ይሆናል።
ባለፈው አመት ሌቪን ላይ ጌትነት ዋለንና ሰለሞን ባረጋን ተከትሎ በ7:27:98 ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ለሜቻ ግርማም ተሳታፊ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሌቪኑ ፉክክር አራተኛ ሆኖ በ7:29:24 ሰዓት ያጠናቀቀው አትሌት በሪሁ አረጋዊም፣ ከወር በኋላ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ጋር ተፎካካሪ ይሆናል። አትሌት በሪሁ አረጋዊ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በአስር ሺ ሜትር አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ የሚታወቅ ሲሆን ከወር በፊት በባርሴሎና የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የዓለም ክብረወሰን ማሻሻሉ ይታወቃል።
ከሌቪኑ ያለፈው አመት ውድድር በፊት በዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ሦስት ሺ ሜትርን ከ7:30 በታች ማጠናቀቅ የቻሉ አትሌቶች ስድስት ብቻ ነበሩ፤ አሁን ቁጥራቸው ወደ አስር ከፍ ብሏል።
ይህን የቁጥር ልዩነት የፈጠሩ አራት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዘንድሮ ከኦሊምፒክ በኋላ እርስበርስ የሚያደርጉት ፉክክርም ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል። ሦስቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሰለሞን ባረጋ፣ጌትነት ዋለና ለሜቻ ግርማ ባለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ አገራቸውን ወክለው መሳተፋቸው ይታወቃል።
ሰለሞን በኦሊምፒኩ በአስር ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ቢያጠልቅም፣ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል በነበረው አለመግባባት በአምስት ሺ ሜትር ሳይሳተፍ መቅረቱ በርካቶችን እንዳስቆጣ አይዘነጋም።
በተመሳሳይ አትሌት ለሜቻ ግርማ በሦስት ሺ ሜትር መሰናክል ሳይመረጥ ቀርቶ በመጨረሻ ሰዓት በኦሊምፒክ ኮሚቴ ውሳኔ ተሳትፎ በርቀቱ ብቸኛውን የብር ሜዳሊያ እንዳስመዘገበ ይታወቃል።
ሌላኛው የመሰናክል ፈርጥ ጌትነት ዋለም ልምድ በሌለው አምስት ሺ ሜትር ተወዳድሮ የመጨረሻውን ማጣሪያ ማለፍ ባይችልም በሦስት ሺ ሜትር መሰናክል አራተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል።
በዘንድሮው የሌቪን የቤት ውስጥ ውድድር በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ተሳታፊ እንደምትሆን የተጠቆመ ሲሆን፣ ጉዳፍ ባለፈው አመት በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ክብረወሰንን ማሻሻሏ አይዘነጋም።
በቶኪዮ ኦሊምፒክ በአምስት ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ጉዳፍ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሌቪን የአንድ ማይል ውድድር እንደምታደርግም ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 30/2014