
በጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ለአራት ቀናት የቆየውን የ5 ዓመቱን ሞሮኳዊ ታዳጊ ለመታደግ እልህ አስጨራሽ ጥረት ቢደረግም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።
ራያን ይህችን ዓለም ተሰናብቷል። የታዳጊውን ሞት ይፋ ያደረገው የንጉሳዊ ቤተ መንግሥት መግለጫ፤ ታዳጊው ከጉድጓዱ ከወጣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መሞቱን ገልጿል።ራያንን ከጉድጓዱ ለማውጣት የተደረገው ጥረት አገሪቷን ያስጨነቀ ሲሆን፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጉድጓዱ ዙሪያ ተሰባስበው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በኦንላይን የታዳጊውን ሁኔታ በጉጉት ሲከታተሉ ነበር።
ታዳጊው የገባበት ጉድጓድ ጠባብና 32 ሜትር ጥልቀት ያለው ስለነበር የመሬት መንሸራተት አደጋ ስጋት የነፍስ አድን ሥራውን አዳጋች አድርጎታል።ይሁን እንጂ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስተመጨረሻ ቅዳሜ ምሽት ራያንን ከገባበት ጉድጓድ ማውጣት ችለዋል።
በወቅቱ ስለራያን ሁኔታ ምንም የተባለ ነገር አልነበረም። መጀመሪያ ላይ ይህ ዜና ሲሰማም ሁኔታውን ሲከታተል በነበረው ሕዝብ ዘንድ ደስታን ፈጥሮ ነበር። በማኅበራዊ ሚዲያ ራያንን ለመታደግ ‘ሴቭ ራያን’ የሚለውን ዘመቻ የተቀላቀሉና ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎችም ደስታቸውን ገልጸዋል። ይህ ፌሽታ ግን ከደቂቃዎች በኋላ አልዘለቀም። ታዳጊው ራያን ማለፉን የሚገልጽ መግለጫ ከቤተ መንግሥት ወጣ። የነበረው ደስታም ወደ ሐዘን ተቀየረ።
የታዳጊውን ራያን ኦራምን ሕይወት የቀጠፈውን ድንገተኛ አደጋ ተከትሎ ግርማዊ ንጉስ መሐመድ ስድስተኛ ለታዳጊው ቤተሰቦች ስልክ መደወላቸውን ከንጉሱ ቤተ መንግሥት የወጣው መግለጫ አመልክቷል።ንጉሱ በአደጋው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን መግለጻቸውን መግለጫው አክሏል።
የታዳጊውን ሕይወት የቀጠፈው አደጋ ማክሰኞ እለት ሲከሰት የራያን አባት የውሃ ጉድጓድ እየጠገኑ ነበር። ልጃቸው ጉድጓድ ውስጥ መግባቱን ለአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን የተናገሩት ግን በሚቀጥለው ቀን ነበር።”ለሰከንዶች ዓይኔን ከእርሱ ላይ ባነሳሁበት ቅጽበት ነው ልጄ ጉድጓዱ ውስጥ የገባው፤ ከዚያ በኋላ እንቅልፍ በዓይኔ አልዞረም ” ብለዋል የራያን አባት።
በሰሜናዊ ሞሮኮ በምትገኘውና ከቼፍቹዋን ከተማ 100 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ትንሿ ከተማ ታሞሮት በሞሮኮ የሲቪል ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የተመራው የነፍስ አድን ሥራ የተጀመረው ማክሰኞ ምሽት ላይ ነበር።ሐሙስ ዕለት ወደ ጉድጓድ በተላከ ካሜራ የተቀረጸው ምሥል ታዳጊው በሕይወት መኖሩንና ራሱን እንደሚያውቅ አሳይተው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ስላለበት ሁኔታ ምንም ዓይነት መረጃ አልተገኘም።
የነፍስ አድን ሠራተኞቹ ኦክስጅን ፣ ምግብና ውሃ ለማቀበል የሞከሩ ቢሆንም ታዳጊው መጠቀም ስለመቻል አለመቻሉም የታወቀ ነገር የለም።ድንጋያማ እና አሸዋማ አፈር ያለውን የውሃ ጉድጓድ ማስፋት የመደርመስ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል አደገኛ ነው ብለው ነበር የነፍስ አድን ሠራተኞቹ። በመሆኑም ታዳጊው ካለበት ጉድጓድ ጋር የሚያገናኝ ግዙፍ መተላለፊያ የቆፈሩ ሲሆን ባለሥልጣናትም የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ ታዳጊው እየተቃረቡ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።

ሠራተኞቹ ጉድጓዱ አለመደርመሱንና አፈር ታዳጊው ወደገባበት ጉድጓድ አለመግባቱን ማረጋገጥ እንዲችሉም የነፍስ ማዳኑ ሥራ በተደጋጋሚ ተቋርጧል። የነፍስ አድን ሠራተኞቹንም ሕይወት ለመጠበቅ ወደ ጉድጓዱ የሚያልፉበት አስተማማኝ መተላለፊያ ትላልቅ ቱቦዎች ተዘርግተው ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በአደጋ ሥፍራው በመገኘት ሃይማኖታዊ መዝሙሮችን በመዘመር፣ በመጸለይ እና ‘ አላሁ አክበር’ እያሉ ሥራውን ሲከታተሉ ሰንብተዋል።
አንዳንዶች ማደሪያቸውንም እዚያው አካባቢ አድርገው ነበር። ሃፊድ ኢል አዙዝ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ ለሞሮኮ እና ለመላው ዓለም ውድ ለሆነው ለዚህ ህጻን ያለውን አጋርነት ለማሳየት በሥፍራው መገኘቱን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።
ይህ ሁሉ ጥረት ግን ራያንን በሕይወት ማትረፍ አልቻለም። ክስተቱ እአአ በ2019 በስፔን የሁለት ዓመት ህጻን በማላጋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ሕይወቱን ያጣበትን አጋጣሚ የሚያስታውስ ነው ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 30/2014