በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ከታዩ ድንቅ ባለ ተሰጥኦ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች መካከል ራሺድ ያኪኒ አንዱ ስለመሆኑ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የምን ጊዜም ኮኮብ ግብ አስቆጣሪው አረንጓዴ ንስር በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የሕልፈተ ሕይወቱ ዜና ከተሰማ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከኳስ ውጪ ሌላ ሕይወት እንዳልነበረው የሚነገርለት ጭምቱ ኮከብ፣ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ የነበረው ሕይወትና የሞተበት መንገድ ልብ ይነካል፡፡ በ33ኛው አፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ እለት ላይ ሆነንም የዚህን ኮከብ አሳዛኝ ታሪክ በስፖርት ማህደር አምዳችን ለማስታወስ ወደድን፡፡
የያኪኒን ጉዳይ በተመለከተ የተለያየ ምርመራና ክትትል ሲያደርጉ የቆዩ የአገሩ ናይጄሪያና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በርካታ መረጃዎችን ሕይወቱ ካለፈ በኋላም ቢሆን አውጥተዋል፡፡ ያኪኒ ለሁለት አስርተ ዓመታት ያህል የኖረበትን የእግር ኳስ ሕይወት በአገሩ ሊግ የጀመረ ቢሆንም በቀጣይ ያመራው ወደ ኮትዲቯሩ ክለብ አፍሪካ ስፖርት ናሽናል ነው፡፡ ለሕይወቱ ማለፍ ምክንያት ተደርጐ የሚጠቀሰው ጉዳይም ከዚህ ይጀምራል፡፡
ያኪኒ በኮትዲቯሩ ክለብ በነበረው ቆይታ የሚያገኘውን ገንዘብ በራሱ ስም በባንክ የሚያስቀምጥ ሰው አልነበረም፡፡ ይልቁንም በትውልድ አገሩ በናይጄሪያ ቤቱን ለሚጠብቅለት የቅርብ ጓደኛው በመላክ እንዲያስቀምጥለት ያደርግ ነበር፡፡ ይህ ጓደኛውም የሚልክለትን ገንዘብ ተቀብሎ እቤቱ ውስጥ ሲያጠራቅምለት ይቆያል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ግን ይህ ጓደኛው የተጠራቀመው ገንዘብ ልቡን አሸፍቶት ከኮከቡ ጓደኛው ይልቅ ንዋይን መረጠ። ያኪኒ የኮትዲቯር ቆይታውን ደምድሞ ወደ አገሩ ሲመለስም ጓደኛው ከድቶት ቅንጡ መኪናና ቤት ገዝቶ የተንደላቀቀ ሕይወት ሲመራ ተመለከተው።
ከዚህ ጊዜ አንስቶም ያኪኒ ሰውን መራቅና ብቸኝነትን ከመምረጥ ባለፈ ማንንም ማመን አቆመ፡፡ የያኪኒ ሕይወት ግን በዚሁ አላበቃም። ሌላ ተስፋና ሌላ ሕይወት የጀመረበትን አጋጣሚ ከወደ አውሮፓ አገኘ፡፡
ፖርቹጋል፤ ግሪክና ሌሎች በርካታ አገራት ተዘዋውሮ በመጫወት በራሱ ላብ በክህደት ያጣውን ገንዘብ መልሶ አገኘው፡፡ ገንዘቡን ብቻም ሳይሆን ጫማውን ሰቅሎ ወደ አገሩ ሲመለስ አንድ የሚቀርበውና የሚያምነው፤ ቀድሞ በጓደኝነት የተሰበረ ልቡን የሚጠግንለት አዲስ ጓደኛ አገኘ፡፡
እንደ ማንኛውም ስፖርተኛ ያኪኒ ከስፖርት ሲገለል ወደ ቢዝነሱ ዓለም ገብቶ ቀሪ ሕይወቱን ለማሳለፍ ከአዲሱ ታማኝ ጓደኛው ጋር አንድ መላ ዘየዱ። ጓደኛው እውቀቱን ያኪኒም ሙሉ ጥሪቱን አሟጦ የጌጣጌጥ ንግድ ለመጀመር ዝግጅታቸውን ጨረሱ።
ያኪኒ ውድ የሆኑ ሃብቶቹን በመሸጥ ጭምር ቢዝነሱን ለመጀመር ለጓደኛው ገንዘቡን ባስረከበበት ወቅት ግን አንድ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ። በቅርብ ሲከታተሏቸው የነበሩ ዘራፊዎች ጓደኛውን እቤት ውስጥ ገድለው ጠቅላላ ገንዘቡን ይዘው ተሰወሩ።
አሁን ያኪኒ ልቡ ክፉኛ ተሰበረ፤ ያመነው ጓደኛው ከዳው፤ የታመነለት ደግሞ በዘራፊዎች ተገደለ፤ ይህም ቅስሙን ሰበረው። ብቸኝነቱን መርጦም ልጆቹን ጨምሮ ዘመድ አዝማዱን ርቆ ሕይወቱ በአርባ ስምንት ዓመቱ ባለፈበት ትንሽ ከተማ ኢባዳን መኖርን መረጠ።
ያኪኒ በዚህች ከተማ ሕይወቱን መምራት በጀመረበት ወቅት ይታይበት የነበረውን ያልተለመደ ባህሪ ተከትሎም ነበር የመገናኛ ብዙኃን እይታ ውስጥ የገባው። ያኪኒ በዚህ ወቅት እጅግ ብቸኛ ከመሆኑ ባሻገር የአዕምሮ እክል ገጥሞት እንደነበር መረጃዎች ወጥተዋል። ሲከታተሉት የነበሩ የናይጄሪያ መገናኛ ብዙኃን ያኪኒ የቅርብ ቤተሰቦቹን ጭምር እቤቱ ሲመጡ ያባርራቸው እንደነበር ዘግበዋል። ከዚህ በባሰም መንገድ ላይ ጭምር ሲፀዳዳና የቤቱን ቁሶች ግቢው ውስጥ ሲያቃጥል እንደታየም ተነግሯል።
ያኪኒ ከዚህ ካልተለመደ ባህሪው ባሻገር በአካባቢው ያሉ ሰዎችና ጎረቤቶቹ የአዕምሮ ችግር እንዳልነበረበት አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል። እንዲያውም ያኪኒ በአካባቢው ካሉ ድሃ ማኅበረሰቦች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደነበረውና ከገንዘብ አንስቶ እስከሚመገቡት ሩዝ ሲያከፋፍል እንደኖረ ይናገራሉ። ይህም የእውነት ያኪኒ የአዕምሮ ችግር ነበረበት ወይስ የደረሰበት ስነ ልቦናዊ ጉዳት ራሱን ከቅርቦቹ ሰዎች እንዲያገል አደረገው የሚል ውዝግብ እንዲነሳ አድርጓል።
ይህ በአንድ ወቅት በዓለማችን እግር ኳስ ታላቅ የነበረ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሕይወቱ ፍፃሜ በአሳዛኝ መልኩ ተቋጭቷል። የአረንጓዴ ንስሮቹ ታሪካዊ አጥቂ መጨረሻው ባያምርም በእግር ኳሱ የሠራቸው ታሪኮች ዘመን ተሻጋሪ ሆነው ይታወሳሉ። እኤአ 1963 ናይጄሪያ ካዱና ውስጥ የተወለደው ያኪኒ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በመጫወት ያን ያህል የጎላ ስም ባይኖረውም በናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያኖረው ታሪክ ግን አረንጓዴ ንስሮቹ እስካሁን ካፈሯቸው ታላላቅ ተጫዋቾችም የጎላ ነው።
ያኪኒ ለናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ በተጫወተባቸው ሃምሳ ስምንት ጨዋታዎች ሰላሳ ሰባት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ባለ ክብረወሰን ነው። በዓለም እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድም የሚታወስባቸው በርካታ ታሪኮች ያሉት ኮከብ ሆኖ ይታወሳል።
በተለይም አገሩ ናይጄሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ መድረክ ተሳትፋ ቡልጋሪያን ሦስት ለባዶ በረታችበት የመጀመሪያ ጨዋታ ያኪኒ ለናይጄሪያ በታሪክ የመጀመሪያዋን የዓለም ዋንጫ ግብ ማሳረፉ ይታወሳል። ይህችን ግብ ካስቆጠረ በኋላም የግቡን መረብ ይዞ እያለቀሰ ደስታውን የገለፀበት መንገድ እስካሁንም በታሪክ የ1994 ዓለም ዋንጫን እንዲታወስ አድርጓል።
እኤአ 1993 ላይ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተሰየመው ያኪኒ ለናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በሁለት የዓለም ዋንጫና በሦስት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ተሰልፎ መጫወት ችሏል። አረንጓዴ ንስሮቹ የ1994 አፍሪካ ዋንጫን ሲያነሱም ያኪኒ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ቁልፍ ሚና ነበረው። እኤአ በ1988 የሴኡል ኦሊምፒክም በናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ መካተቱ ይታወሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 29/2014