የሴካፋ አሸናፊው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ የ180 ደቂቃዎች የጨዋታ ዕድሜ ብቻ ይቀሩታል፡፡ አፍሪካን ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይ ከሚወክሉ ሁለት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ለመሆን በሚያስችላት የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡
ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የአራተኛ ዙር የመልስ ጨዋታቸውን ያደረጉት የሉሲዎቹ ተተኪዎች ከሳምንት በፊት ከሜዳቸው ውጪ በታንዛኒያ አቻቸው የደረሰባቸውን የ1ለ0 ሽንፈት በሜዳቸው በመቀልበስ አምስተኛውን ዙር መቀላቀል ችለዋል፡፡ የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ስብስብ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነችው ረድኤት አስረሳኸኝ ደግሞ ኢትዮጵያ አሸናፊ የሆነችባቸውን ሁለት ግቦች በትናንቱ ጨዋታ አስቆጥራለች፡፡
በእዚህ የመልስ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አንስቶ አስደናቂ የግብ እድሎችን በመፍጠር ታንዛኒያዎችን አስጨንቋል፡፡ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎቹ በሚያስቆጭ መልኩ ጥቅም ላይ ባይውሉም በ31ኛው ደቂቃ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አግቢ ረድኤት አስረሳኸኝ የመጀመሪያውን ግብ ልታስቆጥር ችላለች፡ ፡ ከደቂቃዎች በኃላም ረድዔት ፍፁም ቅጣት ምት ብታገኝም አልተጠቀመችበትም፡፡ የታንዛኒያ ቡድን በበኩሉ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ለመጠጋት ሙከራ ቢያደርግም ግብ ሳያስቆጥር የመጀመሪያው ግማሽ የጨዋታ ሰዓት ተጠናቋል፡፡
ፈጣን እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽም በርካታ የግብ ሙከራዎችና ቅጣት ምቶች የታዩ ሲሆን፤ ረድኤት አስረሳኸኝ ከማዕዘን የተሻገረላትን ኳስ በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ ለማዋሃድ ችላለች፡፡ በዋናው የጨዋታ ሰዓት ላይ አራት ደቂቃዎች ቢጨመሩም በኢትዮጵያ ብልጫ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ በዚህም በጥሎ ማለፉ የማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአምስተኛውና የመጨረሻው ዙር ማለፉን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በመጨረሻው ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታም ከጋናና ዩጋንዳ አሸናፊ ጋር የምትገናኝ ይሆናል፡፡
ከሉሲዎቹ ተተኪዎች ጋር አስደናቂ የስኬት ጉዞ እያደረገ የሚገኘው አሰልጣኝ ፍሬው ከትናንቱ ድል በኋላ በሰጠው አስተያየት መደሰቱን ገልጾ፣ በቀጣይ ለሚገጥመው ቡድን የሚመጥን ዝግጅት በማድረግ የሉሲዎቹን ተተኪዎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ለማብቃት እንደሚጥር ተናግሯል፡፡ ይህን ለማሳካትም ቡድኑ ሊደገፍ እንደሚገባው ጠቁሟል፡፡
ቡድኑ የሁለተኛና ሶስተኛ ዙር ጨዋታዎቹን ሩዋንዳን እና ቦትስዋናን በሰፊ የግብ ልዩነት ጭምር በደርሶ መልስ ማሸነፍ መቻሉ ይታወሳል፡፡ አራተኛ ዙር ጨዋታውንም ኤርትራን በመርታት እንዲሁም ከብሩንዲ ጋር በጠባብ ልዩነት በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ከተቀላቀለው የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ሊደለደል ችሏል፡፡ በታንዛኒያው አማን ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታም ታንዛኒያ በቅጣት ምት ባስቆጠረችው ግብ ነጥብ አስመዝግባ ስትወጣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለ ልማዱ ግብ ሳያስቆጥር ጨዋታውን ማጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
በዓለም አቀፉ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለመራዘም ከተገደዱ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ከወራት በኋላ በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ የዓለም እግር ኳስን በበላይነት የሚመራው ፊፋ ተተኪ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚታዩበትና እንደ ወንዶቹ ያላደገውን የሴቶች እግር ኳስ ወደ ሌላ ደረጃ ያሸጋግራሉ በሚል እምነት ይህንን ውድድር ያዘጋጃል፡፡
16 ቡድኖች የሚፋለሙበትን ይህንን ውድድር የምታስተናግደው ኮስታሪካ ከፓናማ ጋር በጥምረት መሰናዶውን ብትጀምርም እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ብቻዋን ዝግጅቷን በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ውድድር ተሳታፊ ለመሆንም የአገራት ብሔራዊ ቡድኖች በየአህጉራቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ስር የማጣሪያ ውድድራቸውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንም በዓለም ዋንጫው አፍሪካን የሚወክሉ ቡድኖችን ለመምረጥ የሚያስችለውን የማጣሪያ ውድድር እያከናወነ ሲሆን፤ 56ቱ አባል አገራት 40ዎቹ የወጣት ሴት ቡድናቸውን በማጣሪያው እያሳተፉ ይገኛሉ፡፡ አምስት ዙሮች ባሉት በዚህ ማጣሪያ በደርሶ መልስ ጨዋታዎች አሸንፈው ለመጨረሻው ዙር ያለፉ ሁለት ቡድኖች አፍሪካን ወክለው በኮስታሪካው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2014 ዓ.ም