ትዕግስት ጸንቶ የሚቆይ በጎነት ነው። ደስ የማይሉ ሁኔታዎችን በዝምታ መቋቋም ትልቅ ትዕግስትን ይጠይቃል። የሚያበሳጭ ከባድ ችግር ሲያጋጥም በእርጋታ መጠበቅ መቻል ታጋሽ መሆንን ያንፀባርቃል።
የሰው ደም የሚያፈስን ‹‹ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው›› ብሎ በመታገስ፣ ሥራው ቀኑን ጠብቆ እንደሚከፍለው አውቆና አምኖ ማለፍ መቻል በእውነትም የማይናጋ የፀና የታጋሽነት መሠረት ይፈልጋል።
የሚያምነው ወዳጁን የከዳ፤ የገዛ እናቱን የወጋ እና ለጠላት አሳልፎ የሰጠ ከሰው ተራ የወረደን፣ ሰብዕናው የተነጠለውን ኃይል እንደሰው በመቁጠር የመለወጫ ዕድል መስጠት መቻል፤ በእርግጥም ውቅያኖስ የሚያደርቅ ትዕግስትን ገንዘብ ማድረግን ያስገድዳል። ለነገሩ ፍቅር ያስራል፤ ዕውቀት ያኮራል ጥበብ ያስከብራል ይባል አይደል። ዕውቀት ያለው ፍቅር እና ጥበብን ገንዘቡ ያደረገ ታጋሽ ለመሆን አያዳግተውም። ለእዚሁ ሳይሆን አይቀርም፤ የገዛ እናታቸውን ጡት የነከሱ አውሬዎች ሳይቀሩ ዕድል ተሰጥቷቸዋል።
ለዚያውም አንድ ጊዜ አይደለም፤ ጥፋታቸው በላይ በላይ እየተጨመረ እንደተራራ ቢቆለልም ተደጋጋሚ ዕድል ሲሰጣቸው ቆይቷል። በፍቅር ዓለምን ሁሉ ለዘላለም መግዛት ይቻላል። ዓለምን ለመግዛት አሸናፊው መሣሪያ ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ ነው። ፍቅርን ገንዘብ ያደረገ ደግሞ ከሰው ተራ የማይመደበውን በጥላቻ ካልተነጠልኩኝ ብሎ ትዕቢቱን እያሳየ በየቀኑ የሚረክሰውን መሐይም እንደሰው ቆጥሮ ታግሶ ማለፍን ያስችላል። እናም አሁንም በትዕግስት ለማሳለፍ ጥረት እየተደረገ ነው። ምክንያቱም ሰላም ለማግኘት የማይከፈል ዋጋ የለም።
ዕውቀት ያለው ትዕግስቱ ወደር የለውም፤ የትዕቢት፣ የትምክህትና የክፋት ውቅያኖስ እስኪደርቅ፤ እስከመጨረሻው ይታገሳል። የትዕቢት እና የትምክህት ውቅያኖስ እስኪደርቅ – አሁንም ድረስ የሠላም ጥሪው እንደቀጠለ ነው። ችግሩ ግን ‹‹የክፉ ሰው ፈስ አይን ያፈስ›› እንደሚባለው ክፋታቸው የብዙዎችን አይን እያጠፋ ቀጥሏል። የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት አሳልፈዋል፤ የብዙዎች የነገ ተስፋ እንዲጨልም፤ ብዙዎች ቆመው አካላቸው እየተላወሰ በሕይወት ብቻ አሉ እንዲባሉ ሥነልቦናቸው ላይመለስ ተንኮታኩቶ ሞታቸውን ለመጠበቅ እንዲገደዱ አድርገዋል።
ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን እንዲያጡ፤ ብዙ ሴቶች የሕይወት ጉዞ ረዳቶቻቸው የሆኑትን ባሎቻቸውን ዳግም እንዳያገኙ በሞት እንዲለዩዋቸው አድርገዋል። ይህ ተግባር አሁንም ድረስ አላበቃም። በትዕቢት የተወጠሩ ኃይሎች በከፈቱት ጦርነት ልጆች ወላጆቻቸውን በግፍ ተነጥቀዋል። አባቶች ለነገ ሃብት እርሾ የሚሆናቸውን ንብረት ተዘርፈዋል። አረጋውያን ጧሪ ልጆቻቸውን አጥተዋል። ነገር ግን አሁንም የግፍ ፅዋ ሞልቶ ያበቃ አይመስልም።
ዛሬም ድረስ ጦር መምዘዝ እና ሰዎችን ማሳደድ ቀጥሏል። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ጥፋት በኋላም አሁንም ለዘላለም ዓለምን ለመግዛት መሠረት የሆነውን ፍቅር ይዞ ትዕግስትን ገንዘቡ ያደረገ መንግሥት በድጋሚ ዕድል እየሠጠ ነው። የኢኮኖሚው ድቀት በራሱ ከጦርነቱ የባሰ ቀውስ ይፈጥራል በሚል አስተዋይነት፤ ከአውዳሚው ጦርነት ውስጥ በመውጣት በፍጥነት ፊትን ወደ ልማት ማዞር ተቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንዳለበት በማመን ትዕግስት ገንዘብ ተደርጋ አሁንም የሰላም እጅ ተዘርግቷል።
ያለፈው ሁሉ አልፏል በማለት ኢትዮጵያ የተደቀነባትን ፈተና ተሻግራ የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት ለመጀመር ያለው አማራጭ፣ ነገሮችን በትዕግስት ማለፍ ነው ተብሎ አሁንም የክፋት ስሮች ለሆኑት አጥፊዎች ዕድል እየተሰጠ ይገኛል።
‹‹ውሃ ቢያንቅ በምን ይዋጣል፤ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጣል? ›› ብሎ በቃላት ሊገለፁ የማይችሉ ግፍ የፈፀሙ አውሬዎችን ወገን እንደሆኑ በማመን ተቆርጠው እንደማይጣሉ ቢገልፅላቸውም፤ በተግባር ከእስር እየተፈቱ ይቅር እየተባሉ እንዲታዩ ዕድል እንደሚሰጥ የመተማመኛ ቃል ቢገባላቸውም፤ እነርሱ ግን ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንደሚባለው በጄ ለማለት አልወደዱም።
‹‹ተማሪ ሲለግም አንድ መርፌን ሃምሳ ሆኖ ይሸከማል›› እንደሚባለው እነርሱም ለግመዋል እና የተሰጣቸውን ዕድል ለመጠቀም ምንም ዓይነት አዝማሚያ እየታየባቸው አይደለም። ቀን ፊት ለፊት ድርድር የሚል መዝሙር ዘምረው ሳያበቁ ትንሽ ሲጨላልም መልሰው የለመደባቸውን ትንኮሳ ይቀጥላሉ።
የቅራኔ መነሻ በመሆን፣ የሥልጣን ትንቅንቅ በመፍጠርና ግጭት በመቀስቀስ አንዳንዴም ከመቀስቀስ አልፈው እያራገቡ በማቀጣጠል፤ መንግሥት በሆኑባቸው ዓመታት ብቻ ሳይሆን ስልጣናቸውን ካጡም በኋላ ሲፈፅሙ የቆዩት ይህንኑ ተግባር፤ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያውያንን በብሔርና በሃይማኖት በማጋጨት በኩል ደባቸውን በተለያየ መልኩ ቀጥለውበታል። ወንድሙን የወደደ በብርሃን ይኖራል የሚባለው ነገር ፍፁም በብዙ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው እያደረጉ ነው። በልባቸው ውስጥ ያለው ክፋት እና ጥላቻ በመላው ኢትዮጵያውያን ውስጥ እንዲሰራጭ የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ጠማማ ሰው ክፋትን ከሁሉ ያደርሳል እንደሚባለው ክፋታቸውን በትውልድ ውስጥ እየዞሩ አልፈው ተርፈው ወደ ሌላው እያባዙ አሁንም ድረስ ሰው ለመግዛት በየቦታው ጥልቅ ጉድጓዶችን ከመቆፈር አልቦዘኑም። ጥላቻ እና ኃይልን ገንዘብ አድርጎ መንግሥት ሆኖ ለመግዛት የሚቻለው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው። ጊዜው ሲደርስ መግዛት ቀርቶ እንደማንኛውም ሰው መኖርም ቅንጦት ይሆናል። መጽሐፉ እንደሚለው አንድሰው በኃይሉ ጥቂት ጊዜ ይገዛል፤ ስለዚህ ኢትዮጵያን በሃይል ሲገዟት ቆይተዋል። ጊዜው ሲደርስ ደግሞ ሕዝቡ በኃይል እንደማይገዛ አሳይቷል። ‹‹ውረዱ አትመጥኑንም›› ብሏቸዋል።
እናም ኢትዮጵያውያን ‹‹ተንጋለው ቢተፉ ተመልሰው ባፉ›› እንደተባለው በጥላቻ እና በክፋት መንግሥት ሆነው የገዙበት ዘመን ቢያበቃም አመጣጣቸው ከበፊቱ የተለየ ባለመሆኑ ፈፅሞ ዕድሉን አይሰጧቸውም። ምክንያቱም መልሰው በዛው መልኩ ሲመጡ ውጤቱ ተመሳሳይ መሆኑ አያጠያይቅም፤ ይህንኑ ደግሞ ሕዝቡ ተረድቶታል። ነገሩማ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋይ ነው። በብሔር እና በሃይማኖት እየከፋፈሉ ለማፍረስ እንቅልፍ ቢያጡም ሊሳካላቸው አልቻለም። የውጪ ተላላኪ ሆነው ለዘመናት እየሠሩ አገር እና ሕዝብን ቢክዱም የመጨረሻ ግባቸውን ማሳካት አልቻሉም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋይ ነው። ካመነ አመነ ነው።
አምኖ ልቡን ይሠጣል። ከተከዳ ደግሞ በደንብ ትምህርት ይወስዳል። የውጪ ተላላኪ የሆኑ የውስጥ ባንዳዎችን ለሰላም ሲል ይቅር ቢልም ለመገዛት አይመችላቸውም። ምክንያቱም ጠላት እንደዳቦ እስኪገምጥህ አትመቸው የሚለውን ዘይቤ በደንብ ያውቀዋል። አሁን ከገባቸው እና ከተረዱ ከዘመኑ ጋር ይራመዱ። ዘመኑን በማይመጥን በአጉል ትዕቢት ራስን ወጥሮ መነፋፋት ዝሆን አክላለሁ ብላ እንደተወጠረችው እንቁራሪት መፈንዳትን ያስከትላል። ዘመኑን ከማይመጥኑ ድርጊቶች መታቀብ ያስፈልጋል። አሁን ላይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያን ትዕግስት ምክንያቱ ከግጭት አዙሪት የማላቀቅ ፍላጎት ነው።
በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ለፍቅር ቅድሚያ እንሰጣለን። የነጠቀ፣ የዘረፈ እና የገደለ ሳይቀር በሽማግሌ ይቅር ይባላል። በቀል የለም። በቀል ብቻ አይደለም፤ በተጨማሪ መሞኘትም ከዛ በኋላ ይበቃለታል። ይቅርታ ቢደረግም በፍፁም ሊረሳ አይችልም። ቀደም ሲል ሰዎችን እያታለለ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም መስሎት በእልልታ ቡድኑን ተቀብሏል። የኃይል ዘመን ሊያበቃ ነው ብለው የቀደመውን ጉልበተኛ ለማስነሳት አጋሩ ሆነው ደግፈውታል።
በዛ ጊዜ ከሶስት አሥርተ ዓመታት በፊት ምንም እንኳ መንግሥት መሆን የሚፈልገው ኃይል ህልሙ ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን እንደተገነዘቡ የተለያዩ ሰዎች ቢናገሩም፤ ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም። ነገር ግን በጥላቻ እና በክፋት የተተበተበው ኃይል መንግሥት ሲሆን፤ ዓላማው ለዓመታት ሲሠራ የነበረው ኢትዮጵያን ማፍረስ ላይ መሆኑን ጊዜ አረጋገጠው። አሁን ላይ ሕዝቡ ተረድቷል። ከእዚህ በኋላ መንግሥት የመሆን ምንም ዓይነት ዕድል አይኖረውም። ምክንያቱም መንግሥት ሆኖ ታይቷል።
አሁን እየፈፀመ ካለው ጥፋት ባሻገር ሰላም ወዳድ መሆኑን አስመልክቶ ቢለፈልፍም መስማት ማየትን ስለማያሸንፍ በተግባር በሠራው ሥራ ተቀባይነቱን ማጣት ብቻ ሳይሆን ከማንም በላይ የአገር እና የሕዝብ ጠላት መሆኑ ተረጋግጧል። ከዚህ በኋላ ለጥፋት ቡድን የመንግሥትነት ዕድል እንደማይሰጠው አያጠያይቅም። ነገር ግን እርሱ አሁንም ድረስ ህልሙ ተመሳሳይ ነው።
ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እንደሚባለው። መንግሥት እና ሕዝብ ላሳየው ትዕግስት የእርሱ ምላሽ አሁንም ድረስ እመራችኋለሁ የሚል ንቀትን እያሳየ ነው። ምክንያቱም አሁንም የሕዝብን ጉሮሮ ለመያዝ እና ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲነሳ በማሰብ አፋር ላይ ትንኮሳ እያካሔደ ነው። ዓላማው መንግሥት ሆኖ በፈፀመው የመነጠል እና የመለያየት ስትራቴጂ ያልተበተነችውን ኢትዮጵያ በየትኛውም መንገድ ተጠቅሞ ከቻለ መንግሥት ሆኖ ግቡ ጋር መድረስ ነው።
ካልቻለም በየትኛውም መንገድ አገር ለማፈራረስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። አሁንም ሂሳብ እንደሚያወራርድ ገልጾ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዲጣላ መሠረት ለመጣል ወረራ አካሒዶ ሲገል፣ ሲደፍር እና ሲዘርፍ ከመከራረም አልፎ አሁንም አከርካሪው ተመቶ ቢመለስም ያለፈ የጥፋት ተግባሩን ከመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይል እያሳየ ነው። አሁንም ድረስ ወረራውን አላቆመም። እዚም እዚያም መተነኳኮሱን እንደሥራ ይዞታል።
በዚህ ዘመን ትዕግሥት፣ ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት ያስፈልጋል በማለት ሕዝብ እና መንግሥት እርሱ ከቆመበት የክፋት ጥግ ርቀው በተቃራኒ አቅጣጫ ቢገኙም ለመቅረብ በጎነትን እና ትዕግስትን ለመረዳት አልፈለገም። አሁንም ድረስ ላለፈው ከፍተኛ ጥፋት ሳይፀፀት ያው የቁልቁለት መሥመሩን ይዞ እየተንደረደረ ነው።
መንደርደር ደግሞ መጨረሻው ተረጋግቶ መቆም ሳይሆን መደፋትን ያስከትላል። ነገር ግን መደፋት እስኪከተል በሕዝቦች መካከል እሳት እየለኮሱ እያራገቡ ዜጎችን እንደማገዶ እያነደዱ አገር ከማፍረስ ይልቅ መረጋጋት ጊዜ ሰጥቶ ማሰብ እና የሕዝብ እና የመንግሥትን ትዕግሥት ልብ ብሎ ቦታ ሰጥቶ ዕድሉን መጠቀም ያስፈልጋል። መንግስት እና ሕዝብን መጥላት ብቻ ሳይሆን መናቅ እና በሁሉም ውስጥ ቂም እና በቀል ሥር ሰዶ እንዲቀጥል፤ አገርም በዓለም የኋላቀርነት መገለጫ ምሳሌ እንድትሆን የማድረግ ጉዞ ከአሁን በኋላ ሊገታ ይገባል።
ይህ ኃይል በምንም መልኩ መንግሥት ካለመሆን ባሻገር ለሰላም ሲባል እየተሰጠው ያለው ዕድሉ ተጠቅሞ ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ‹‹ጠላት እንደዳቦ እስኪገምጥህ ከፈቀድክለት ችግሩ ከእርሱ ሳይሆን ከራስህ ነው።›› እንደሚባለው ኢትዮጵያን በልቶ እስኪጨርሳት መጠበቅ የሚያበቃ ይሆናል። እርሱ መንገዱ ፍቅር ሳይሆን ኃይል በመሆኑ እንዲሁም ኃይል እና ጉልበት ለጊዜው ቢያንበረክክም ዘላቂ መሆን ስለማይችል ይብቃህ ተብሏል። አሁንም ውቅያኖሱ ካልደረቀ ትዕግስት የሚያበቃበት ጊዜ ይኖራል። መፍትሔው አንድ እና አንድ ይሆናል።
ታጋሽነት በሰላም ለመኖር ይረዳል ። በማለት እየታገሰ ያለውን መንግሥት እና ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ካልቻለ፤ በፍቅር የተሞላ ሕዝብ ምንም እንኳ ግፉ ቢያስከፋውም ቢያንስ የሌሎችን ሞት ለመቀነስ እያሰበ ያለውን የይቅርባይነት ሃሳብ መናቅ ከቀጠለ፤ ሕዝብ እየሞተ፤ የአገር ኢኮኖሚ እየደቀቀ ቡድኑ በበኩሉ እንደፈለገው እየፈነጨ የሚቆይበት ጊዜ መገታቱ አይቀርም።
ከልብ ሞልቶ ከተረፈ አፍ ይናገራል እንደሚባለው እነርሱ ‹‹ኢትዮጵያን እናፈርሳለን፤ ኢትዮጵያዊነትን ከምድረ ገፅ እናጠፋለን›› ብለው በልባቸው ተመኝተው ከአፋቸው ያወጡት ቃል ሳይተገበር እነርሱ ይፈርሳሉ። የዛን ጊዜ ውቅያኖስ እስከ ማድረቅ ፀጥ ያለው ትዕግስት ተገቢውን ሥፍራ ካልተሰጠው ውጤቱ ከባድ መሆኑ የማይቀር ነው።
ለሕዝቡ የዕለት እንጀራና ዘለቄታዊ ዕድገቱ ምንም ፋይዳ የሌላቸውን አጀንዳዎች እየፈበረኩ አገር ከሚያምሱ፣ በመጪው ትውልድ የሚያስከብራቸውን ተግባር ያከናውኑ። ለፀፀት ከሚዳርጉ አስከፊ ድርጊቶች በመራቅ በታሪክ የሚታወሱበት ቁም ነገር ይሥሩ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 26/2014