35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ (35th Ordinary Session of the Assembly of the Heads of State and Government of the African Union) ቅዳሜ እና እሁድ (ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል። የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የተካው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (Organization for African Unity – OAU) ከ59 ዓመታት በፊት የተመሰረተው በአርቆ አሳቢ አፍሪካውያን ብርቱ ጥረት ነው።
በዛሬው ዳሰሳችን ለድርጅቱ መመስረት ጉልህ አስተዋፅኦ ካበረከቱ አፍሪካውያን መካከል የጥቂቶቹን አበርክቶ በአጭሩ እንቃኛለን። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ነፃነቷን አስከብራ የቆየችው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት ነበራቸው።
ንጉሰ ነገሥቱ ይህን ተደማጭነታቸውንና እንደ ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ያሉ የበሳል ባለስልጣኖቻቸውንና አማካሪዎቻቸውን ምክረ ሃሳብ ተጠቅመው ድርጅቱ እውን እንዲሆን አድርገዋል።
በወቅቱ የነበሩት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችም የንጉሰ ነገሥቱን ጥያቄ በቀናነት የሚቀበሉ ስለነበሩ የድርጅቱ ምስረታ ሊሳካ ችሏል። ድርጅቱን በመመስረት ሂደት ላይ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት የአህጉሪቱ ሀገራት በሁለት የተለያዩ ጎራዎች ተከፈሉ።
አንደኛው ቡድን ራሱን ‹‹የዘመናዊ ተራማጅ›› ብሎ የሚጠራው ‹‹የካዛብላንካ ቡድን›› ሲሆን የቡድኑ አባላት በፖለቲካና በኢኮኖሚ የተዋሃደች የአፍሪካ ፌደሬሽንን የመመስረት ዓላማና የግራ ዘመም ፖለቲካ አቀንቃኝ በሆኑ መሪዎች የተዋቀረ ነበር።
በዚህ ጎራ የተሰለፉት አገራት ጋና፣ አልጄሪያ፣ ጊኒ፣ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ማሊ እና ሊቢያ ሲሆኑ የቡድኑ መሪም የወቅቱ የጋናው ፕሬዝደንት ክዋሜ ንክሩማህ ነበሩ። ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ‹‹የሞንሮቪያ ቡድን›› ሲሆን የአፍሪካ አገራት ያለፖለቲካዊ ውህደት በኢኮኖሚያዊና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስሮች ተባብረው መዝለቅ እንዳለባቸው ያምናል። በዚህ ጎራ ከነበሩት ሀገራት ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ እና ላይቤሪያ ይጠቀሳሉ።
በመጨረሻም በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ታላቅ ጥረትና በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ ሁለቱም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ እንዲገናኙ በተደረገው ጥሪ መሠረት ግንቦት 14 ቀን 1955 ዓ.ም የ32 ነጻ ሀገራት ተወካዮች አዲስ አበባ ላይ ለስብሰባ ተቀመጡ። ከሦስት ቀናት ውይይት በኋላም፣ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ሀገራቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የስምምነት ውል (OAU Charter) ሲፈርሙ የድርጅቱ ምስረታ እውን ሆነ።
በዚህም የተነሳ በርካታ ወገኖች ለቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ‹‹የአፍሪካ አባት›› የሚል ስም ሰጥተዋቸዋል። በዕለቱ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ባደረጉት ንግግር ‹‹… ይህ ቀን ለአፍሪካውያን በሙሉ ታላቅና ታሪካዊ ቀን ነው።
ሕዝቦቻችን ከእኛ የሚጠብቁትን ተግባር ለመፈፀምና ክፍለ ዓለማችን በዓለም አቀፍ ጉባዔ የሚገባትን ትክክለኛ ስፍራ እንድትይዝ ለማድረግ ተሰብስበናል።
በዛሬው ቀን መላው ዓለም አተኩሮ ይመለከተናል። አፍሪካውያን እርስ በእርሳቸው በመጣላት የተከፋፈሉ ናቸው የሚሉ አካላት አሉ፤ እውነትም አንዳንድ አለ፤ ቢሆንም ይህ መጥፎ አስተያየት ያላቸው ሁሉ የተሳሳተና ሃሳባቸው ሁሉ ከንቱ መሆኑን በስራችን እናሳያቸው! አፍሪካ ከትናንትናዋ አፍሪካ ወደ ነገዋ አፍሪካ በመሸጋገር ላይ ትገኛለች። አፍሪካ ከሞላ ጎደል ነፃ ሆናለች።
ነፃ ሆነን እንደገና ተወልደናል። ለእኛ ሲሉ ሕይወታቸውን የሰጡ አፍሪካውያን ስማቸው ሕያው ሆኖ ይኖራል፤ ሃውልትም ሊቆምላቸው ይገባል! ሕይወት ያለ ነፃነት ዋጋ የለውም! ትግሉ ያለቀ መስሎን ሳናመነታ ወደፊት እንግፋበት! ትግላችንን ለማጠንከር ጊዜው አሁን ነው! ለአፍሪካ ነፃነት የረዱትን ልንረሳቸው አይገባም! አንድነት ኃይል እንደሆነ መለያየት ደግሞ ደካማነት እንደሆነ እናውቃለን! በመካከላችን ሊኖሩ የሚችሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች ወደ ጎን ትተን ሁላችንንም ለሚያስተባብረን ለአፍሪካ አንድነት መድከም አለብን! እርስ በእርሳችን መነታረክ ትርፉ የሌላ ሲሳይ መሆን ነው! አፍሪካ የበለጠ እንድትነቃ ማድረግ አለብን!
የእያንዳንዱ አፍሪካዊ ታማኝነት ለጎሳውና ለመንግሥቱ ሳይሆን ለአንድ አፍሪካ ሊሆን ይገባል! በጎሳ መለያየት የአገርን አንድነት የሚያፈርስ ነው! በእጃችን የጨበጥነው የፖለቲካ ነፃነት በኢኮኖሚና በሶሻል እድገት ካልተደገፈ ከፍ ያለ አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል …›› ብለው ነበር። የአፍሪካን ነፃነትና አንድነት አጥብቀው ከሚሰብኩ መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት የጋናው መሪ ክዋሜ ንክሩማህ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ጉልህ አስተዋፅኦ ነበራቸው።
ንክሩማህ ራሱን ‹‹የዘመናዊ ተራማጅ›› ብሎ የሚጠራው እንዲሁም በፖለቲካና በኢኮኖሚ የተዋሃደች የአፍሪካ ፌደሬሽንን የመመስረት ዓላማ ይዞ የነበረው ‹‹የካዛብላንካ ቡድን›› መሪ ነበሩ።
ንክሩማህ የጋና የነፃነት ትግል መሪም ነበሩ። ከነፃነት በኋላም የጋና የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር (እ.አ.አ 1957- 60) እና ፕሬዝደንት (1960-66) ሆነው አገልግለዋል።
ፓን አፍሪካኒስቱ ንክሩማህ የአፍሪካ አንድነትና ትብብር ከመደበኛ አጋርነትና ማኅበር እሳቤ ከፍ ያለና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውህደትን ያካተተ ኅብረት ሊሆን እንደሚገባ በጽኑ ያምኑ ነበር። አፍሪካ በተሻለ የምጣኔ ሀብት ጎዳና እንድትራመድ ዜጎቿ ከመከፋፈል ይልቅ መተባበርና በጋራ መቆም እንዳለባቸው ይሰብኩ ነበር። በተለይም ዘረኝነትንና በጎሳ መከፋፈልን አጥብቀው ይቃመውና በሕግ መታገድ እንደሚገባቸውም ይናገሩ ነበር።
ይህን እሳቤያቸውን እውን ለማድረግም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት ንቁ ተሳታፊና አስተባባሪ ነበሩ። በዚህም ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራቾች መካከል አንዱ ሆነው በታሪክ ስማቸው ይጠቀሳል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የኢትዮጵያዊው አምባሳደር የክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ደጀን የእጅ ስራ (እሳቤ) ውጤት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አቶ ከተማ የድርጅቱ ምስረታ እውን እንዲሆን ትልቁን ተግባር ያከናወኑ በዲፕሎማሲ ጥበብ የመጠቁ ኢትዮጵያዊ ፓን አፍሪካኒስት ናቸው። የዚህን አርቆ አሳቢ፣ ደፋርና አገር ወዳድ ታሪክና አበርክቶ ዘርዝሮ መጨረስ ‹‹ዓባይን በማንኪያ›› ነውና ከድርጅቱ ምስረታ አንፃር ካከናወኑት ዘመን ተሻጋሪ ስራቸው መካከል ጥቂቱን ብቻ እንጠቃቅሳለን።
አምባሳደር ከተማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ስራቸውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን ጋር እንድትቀራረብ ለማድረግ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ነው። ስለዚህ ጉዳይ አምባሳደር ከተማ በአንድ ወቅት ሲናገሩ … ‹‹ … እ.አ.አ 1961 ዓ.ም ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደገባሁ የመጀመሪያ አጀንዳዬ አድርጌ የያዝኩት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጋር የበለጠ የምትቀራረብበትንና የምትተባበርበትን መንገድ መፈለግ ነበር። ይህንን ጉዳይ ለጃንሆይ ነገርኳቸው። ‹ … ፋሺስት ኢጣሊያ በወረረን ጊዜ ወደ ዓለም መንግሥታት ማኅበር ሄደው የጮሁት ብቻዎን ነበር። ያ ጊዜ መደገም የለበትም። ከአረቦች ጋር ልንሆን አንችልም፤ ከአውሮፓውያንም ጋር መሆን አንችልም።
የእኛ ተፈጥሯዊ ምንጫችን አፍሪካ ስለሆነ ከአፍሪካውያን ጋር ነው መተባበር ያለብን። በዚህ ጉዳይ መግፋት አለብን። ይህን ጉዳይ ያምኑበታል ወይ?› ብዬ ስጠይቃቸው ‹ዋናው የእኔ ማመን አይደለም።
አንተ ታምንበታለህ?› ሲሉኝ ‹እኔማ አምኘበታለሁ› አልኳቸው። ‹እንግዲያውስ ካመንክበት ቀጥልበት› አሉኝ … ›› ነበር ያሉ። እንግዲህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን (የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረትን) የመመስረት እንቅስቃሴ የተጀመረው በዚህ ወቅት ነው። አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ ዋነኛ ወዳጆች አፍሪካውያን እንደሆኑ ጽኑ እምነት ነበራቸው። ይህን እምነታቸውን በተግባር ለመተርጎም አፍሪካውያንን በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስብ ኅብረት/ድርጅት ለማቋቋም ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ።
በወቅቱ ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገራት የካዛብላንካ (‹‹የአፍሪካ አገራት በፍጥነት ተዋህደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል››) እና የሞኖሮቪያ (‹‹አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል››) በሚባሉ ጎራዎች ተከፋፍለው ነበር። ይህ ክፍፍል የአፍሪካውያንን ኅብረት እንደሚጎዳው የተረዱት አምባሳደር ከተማ ይፍሩ፣ ኢትዮጵያ ሁለቱን ቡድኖች የማስማማትና አፍሪካውያንን በአንድ ኅብረት/ ድርጅት ስር የማሰባሰብ ስራ መስራት እንዳለባት ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አጥብቀው ተናገሩ።
ንጉሰ ነገሥቱም በአቶ ከተማ ምክረ ሃሳብ ተስማምተው እንቅስቃሴዎችን ጀመሩ። አምባሳደር ከተማ ስለዚህ ጉዳይ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፤ ‹‹ … እኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደ ነበርኩ በሁለቱም ስብሰባዎች ላይ እንድንካፈል ጥሪ ቀረበልን። የሞኖሮቪያ ቡድን ጥሪ ቀድሞ ስለደረሰን፣ የሞኖሮቪያ ቡድን አባል የነበሩት አገራት በቁጥር በርከት ያሉና በወቅቱ በአፍሪካ ከፍተኛ ተደማጭነት የነበራቸው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ስለነበሩ በእርሳቸው ሰብሳቢነት ሁሉም ወገኖች ተሰብስበው ወደ አንድ ሃሳብ እንዲመጡ በማሰብ በሞኖሮቪያ ቡድን ስብሰባ ላይ ተገኘን። ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም በስብሰባው ላይ ተገኙ። ቀጣዩ የሞኖሮቪያ ቡድን ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበን ተቀባይነትን አገኘን።
የካዛብላንካ ቡድን ጥሪ ሲደርሰን ‹በዚህ ዓመት መገኘት አንችልም፤ በሚቀጥለው ዓመት ግን እንገኛለን› የሚል ምላሽ ሰጠናቸው። የካዛብላንካ ቡድን አባላት ደግሞ በዚያው ሰሞን ስብሰባ ነበራቸው። የወቅቱ የጊኒ ፕሬዝደንት አህመድ ሴኮ ቱሬ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ተደረገና ለአፍሪካውያን መለያየት እንደማይበጅና በአንድነት መቆም እንደሚሻል ተወያየንና ‹ኢትዮጵያና ጊኒ ቀጣዩ ስብሰባ የመላው አፍሪካውያን ስብሰባ እንዲሆን ተስማምተዋል› የሚል የጋራ መግለጫ አወጣን። በዚህ መሰረት ቡድኖቹን የማግባባት ስራ እንድንሰራ ተስማማን።
ለመሪዎቹ ሁሉ ደብዳቤ ተፃፈ። በወቅቱ የእኔ ልዩ ፀሐፊ ከነበሩት ከአቶ አያሌው ማንደፍሮ ጋር በመሆን የንጉሰ ነገሥቱን ደብዳቤዎች ይዘን በየአገራቱ ዞርን። ‹መሪዎቹ ምላሽ ሳይሰጡን ከተሞቹን አንለቅም› ብለን ወስነን ነበር። መሪዎቹም በአጭር ቀናት ውስጥ አዎንታዊ የሆነ ምላሽ ሰጡን።
በመጨረሻም በግንቦት ወር 1955 ዓ.ም ጉባዔው ተካሄደና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ካበረከተቻቸው አስተዋፅኦዎች መካከል አንዱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም ያከናወነችው ተግባር ነው። ይህንን መካድ ታሪካችንን መካድ ነው።›› የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለማቋቋም አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ያበረከቱት አስተዋፅዖ በዋጋ የማይተመን፤ በቃላት የማይገለፅ ነው። የሞኖሮቪያ እና የካዛብላንካ ቡድኖች አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችንና መሪዎችን ማነጋገርና ማሳመን በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላ እጅግ ፈታኝ ስራ ነበር።
ምናልባትም ከአምባሳደር ከተማ በስተቀር ሌላ ሰው የሚያሳካው ተግባር አልነበረም። አምባሳደር ከተማ ግን ያን ከባድ ትዕግስት፣ ጥበብና ፅናት የሚፈልግ ተግባር በብቃት አልፈውታል። አምባሳደር ከተማ በየሃገራቱ ሲዞሩ ‹‹ምላሽ ሳትሰጡኝ ከሀገራችሁ ለቅቄ አልሄድም፤ ንጉሱም ወደ ሀገሬ አያስገቡኝም›› የሚሉ ማባበያዎችን ይጠቀሙ ነበር።
የቱኒዚያው ፕሬዝዳንት ‹‹የሁለቱ ቡድኖች የጋራ አቋም ሳይኖር እንዴት አንድ ላይ እንሰበሰባለን?›› የሚል የእምቢታ ምላሽ ሲሰጧቸው አምባሳደር ከተማ በምላሹ ‹‹አፄ ኃይለሥላሴ ያለ እርስዎ ይህ ስብሰባ አይካሄድም ብለዋል›› በማለት ነገሯቸው። በወቅቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የነበራቸው ተሰሚነትና ተፅዕኖ ከፍተኛ ስለ ነበርም የቱኒዚያው ፕሬዝደንት በአምባሳደር ከተማ ሃሳብ ተስማምተው አዲስ አበባ ተገኙ።
ከድርጅቱ ምስረታ ቀጥሎ የአፍሪካ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ፣ ‹‹የድርጅቱ ፀሐፊ ማን ይሁን?›› እንዲሁም ‹‹ዋና ጽሕፈት ቤቱ የት ይሁን?›› የሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎች ነበሩ። በአምባሳደር ከተማ አመራርነት ፖሊሲዎቹ ተዘጋጅተው ቀረቡ። በፖሊሲዎቹ ላይ አንዳንድ አለመስማማቶች ቢፈጠሩም ሰነዱ ተፈረመ። ከዚህ በተጨማሪም አምባሳደር ከተማ ‹‹ኢትዮጵያ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ ትሁን›› የሚል ሀሳብ አቀረቡ።
ጠንካራ ተቃውሞዎች ከብዙ አቅጣጫዎች ተደመጡ። ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አገራት ‹‹የሴኔጋሏ ዳካር ከተማ የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን ተስማምተናል›› አሉ።
ናይጀሪያ በበኩሏ የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ የአገሬ አፈር ላይ መተከል አለበት ብላ አቋም ያዘች። ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመመስረት በብዙ ደክማ አመድ አፋሽ መሆኗ ንጉሰ ነገሥቱንና አምባሳደር ከተማን ቢያስደነግጣቸውም ‹‹ሙያ በልብ ነው›› ብለው ኢትዮጵያ እንድትመረጥ የማግባባቱን ስራ ጀመሩ። በወቅቱ ‹‹ኢትዮጵያን እንዳትመርጡ›› የሚሉ የቴሌግራም መልዕክቶች ጭምር ይሰራጩ ነበር።
በመጨረሻም ከብዙ ማግባባትና ክርክር በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንድትሆን አገራቱ (ከናይጀሪያ በስተቀር) ድምፃቸውን ሰጡ። በወቅቱ በድንበር ውዝግብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ የነበረችው ሶማሊያ እንኳ ድጋፏን ለኢትዮጵያ እንደሰጠችና የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ‹‹ኢትዮጵያን እንዳትመርጡ›› ተብለው ከሌሎች አገራት የተላኩትን የቴሌግራም መልዕክቶች ለአምባሳደር ከተማ ያሳዩዋቸው እንደነበር ይነገራል።
ይህ ሁሉ ፈተና በአምባሳደር ከተማ በሳል የአመራር ብቃት ታልፎ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በግንቦት ወር 1955 ዓ.ም ተመሰረተ። የድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤትም አዲስ አበባ ሆነ። አንጋፋ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገራት ዲፕሎማቶችም ስለአምባሳደር ከተማ አስደናቂ ተግባራት በተደጋጋሚ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህልም፡- ‹‹… ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና አቶ ከተማ ይፍሩ በሁለቱ ጎራ ተሰልፈው የነበሩ መሪዎችን በማግባባት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እውን እንዲሆን አድርገዋል …›› የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪ ‹‹ … አቶ ከተማ ይፍሩን ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ታሪክ መለየት አይቻልም።
በጣም ብዙ ደክመዋል። የአፍሪካ መሪዎች በጃንሆይ ሰብሳቢነት ሲሰባሰቡ ጀምሮ መሪዎችን በማነጋገርና በማግባባት ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው። የሞኖሮቪያና የካዛብላንካ ቡድኖች ተፈጥረው የሃሳብ ልዩነት በነበረበት ወቅት አምባሳደር ከተማ በየአገራቱ እየዞሩ ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት እንደሚሻልና የቡድኖቹን ሃሳቦች በውይይት መፍታት እንደሚቻል ያስረዱ ነበር።
በጣም ወደ ግራ ያዘነበሉ የአፍሪካ መሪዎችንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በማግባባት ያበረከቱት አስተዋፅዖ እጅግ ከፍተኛ ነበር።›› አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ የታሪክ ጸሐፊና ዲፕሎማት አምባሳደር ዘውዴ ረታ ‹‹… አምባሳደር ከተማ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ‹‹ብሔራዊ ጥቅምን ያስከበረና ገለልተኛ የሆነ›› እንዲሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል … ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል የአፍሪካ የነፃነት ታጋዮችን በመደገፍና ወደ ነፃነት የሚያደርሱ መንገዶችን በማመቻቸት እንደ አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ታላላቅ ተግባራትን ያከናወነ ሰው የለም …›› የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትርና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አያሌው ማንደፍሮ፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥር 25/2014