ጠዋት ነው፤ በተለምዶ ብሔራዊ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ቆሜ ወደ መሥሪያ ቤቴ የሚያደርሰኝን ሰርቪስ እየተጠባበኩ ነኝ። ከባድ ቆፈን አለ፤ ወቅቱ የጥቅምት አጋማሽ እንጂ የጥር መገባደጃ ፈፅሞ አይመስልም።
ሥራ ረፍዶበት ወደ መሥሪያ ቤቱ በእግሩ የሩጫ ያህል የሚራወጠው መንገደኛ ብርዱን ፈርቶ የሚሸሽ ይመስላል። አንድ ዕድሜው ወደ ሰባት ዓመት የሚገመት ታዳጊ ዩኒፎርም ለብሶ ብቻውን ቆሟል፤ ብቻውን ያልኩት ነጠል ብሎ መቆሙና አጠገቡ ሰው አለመኖሩን ለደቂቃዎች ስለታዘብኩ ነው።
ትራንስፖርት የሚጠብቅ መሰለኝ። አንድ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ መጥቶ ከፊት ለፊቴ ቆመ። ታዳጊው ወደ አውቶቡሱ በሩጫ ሲጠጋ ከሌላው ተሳፋሪ በተለየ አሽከርካሪው አይቶት ነበር መሰል የፊት በሩን ከፍቶለት ወደ ውስጥ ገባ። የሹፌሩ ታዳጊው ሮጦ ሲጠጋው ቶሎ ምላሽ መስጠትና የታዳጊው ሁናቴ የዘወትር ደንበኛና ተስተናጋጅ ይሆኑ ይሆን ያሰኛል። ደጋግሜ ስለ ልጁ አወጣሁ አወረድኩ። ልጁ ጠዋት ላይ ተነስቶ ያለ ረዳት/ ሸኚ/ በዚህ ሁኔታ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ፣ ባልጠነከረ ሰውነቱ ለዚያውም ከተማዋ በደንብ ከእንቅልፍዋ ባልነቃችበት ሰዓት እዚያ ቦታ ላይ ማልዶ መገኘቱ አስገረመኝ።
ነገው የተሻለ እንዲሆን ወደ ሚያስችለው የትምህርት ገበታ ለመሄድ ብርድና ቁሩን በለጋነት እድሜው ሲታገል ደነቀኝ። ታዳጊውን እያሰብኩ የምጠብቀው ሰርቪስ መጣና ጉዞ ወደ አራት ኪሎ ሆነ። ከሜክሲኮ እስከ አራት ኪሎ ያሉት የጎዳና መብራት ምሶሶዎች በአፍሪካ አገራት ባንዲራዎች ደምቋል። መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን የሚያስተላልፉት ዘገባ ታሰበኝ፡ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ይካሄዳል፤ መዲናችን አዲስ አበባ ይህን ጉባዔ ለማስተናገድ ሽር ጉድ ላይ ናት።
የእግረኛ መንገዶችንና የአረንጓዴ ስፍራዎችን ጨምሮ ጎዳናዎቿን ለማስዋብ የተከናወነው ሥራ የእዚህን ጉባኤ ዝግጅት ተጨማሪ ውበት አጎናጽፎታል። ለመንገዶቹ የተገጠሙት አዳዲስ መብራቶችም ምሽት ላይ ከተማዋን በውበት ላይ ውበት ደርበውለታል።
ስለ ተስፋይቱ ምድር አህጉረ አፍሪካ ማሰብ ስጀምር፤ ከዚያ ታዳጊ ብላቴና ጋር የበዛ ነገርዋ ተመሳሰለብኝ። ታዳጊው የወደፊቱን መፃኢ ተስፋ ሰንቆ የሚጓዝ መሆኑ ከአፍሪካ ታዳጊነትና የመጪው ዘመን ተስፋዋ ጋር ማነፃፀርና ማየት ውስጥ ገባሁ። ከዚህ ራሱን ለመቻል እየተጋ፣ ለመለወጥ እየተባ ካለ ልጅ ጋር ብዙ ነገርዋ ተመሳሰለብኝ።
አፍሪካ ገና እያደገች ያለች አህጉር ናት። ራሷን ችላ በሁለት እግሮቿ ለመቆም እየተውተረተረች ያለች የተስፋ ምድር። መሪዎቿ ምንም እንኳ ለአህጉሪቱ ብዙም ጠብ ያለ ነገር ባይታይም፣ በሚገባ መቆም የምትችልበትን መንገድ ሊቀይሱ ሲመክሩ ይሄው ስድስት አስርተ ዓመታት ሊሞሉ ተቃርበዋል።
ዘንድሮም ጉባኤያቸውን ሊያደርጉ በአዲስ አበባ እየገቡ ናቸው። አህጉሪቱ ፖለቲካዊ ትኩሳት በዚህም የሚከሰት የእርስ በርስ ግጭትና የማያባራ ጦርነት፣ ረሀብ እርዛትና የተንሰራፋ ድህነትና በሽታ መገለጫዋ ነው፤ አህጉሪቱን ከእዚህ ማጥ በማውጣት የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥርዓት የሰፈነባት፣ በኢኮኖሚዋ የዳበረችና የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ የተለወጠች፣ በስልጣኔዋ የላቀች አህጉር ትሆን ዘንድ የመሪዎቿ ሚና ከፍተኛ ነው። ይህቺ ለራስዋ መሆን ያልቻለች ነገር ግን፣በሕዝቦቿ አንድነትና ትጋት ለሌሎችም መትረፍ የምትችል አህጉር መፃኢ ጉዞዋን ማቅናት ይጠበቅባቸዋል።
በራስ መቆም ክብርን ያላብሳል። ሉዓላዊነት ሳይሸራረፍ እንዲከበር፣ ይህን አድርጉ፣ ያን ተው ከሚሉ የውጪ ኃይሎች ያወጣል። አፍሪካ ወደ ብልፅግና በሚያስኬዳት ጎዳና ላይ በኅብረት መጓዟ እና ጠንካራ አመራር ያላት መሆኑ ይጠቅማታል። ከአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ያላትን አፍሪካ ማስተባበር ከተቻለ ተዓምር መሥራት አያዳግትም። ይህን የማድረጉ ሥራ ግን ብዙ ፈተናዎች ሊገጥሙት ይችላሉ። አለመበገር ዋናው ነገር።
ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት ታዳጊ፤ የልጅነት እንቅልፉን፣ብርድና ቁሩን እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ተቋቁሞ የነገውን ተስፋ የተሻለ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርገው ሁሉ ታዳጊዋ አህጉር አፍሪካም ችግሮችን ለመቋቋም፣ በተለይ ምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን በአፍሪካውያን ላይ ለማንሰራፋት እያደረሱ ላሉት ጫና ሳይንበረከኩ በርትተው መሥራት ይኖርባቸዋል።
አፍሪካ ነገን የተሻለ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕዝቧንና መሪዎቿን አስተባብራ መሥራት በሚያስፈልጋት ወቅት ላይ ትገኛለች። እንደ እኔ አፍሪካ ግቦቿን ለማሳካት የሆነ አብዮት ነገር ያስፈልጋታል። ለውጥ የሚያመጣ አብዮት፤ የህዳሴ አብዮት፤ የአንድነትና በጋራ የመቆም አብዮት ለአፍሪካ ያስፈልጋታል። በራሷ እንድትቆምና እንድትፀናና ተፅዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን መሪዎቿ ከጉባኤያቸው በኋላ የእውናዊ ለውጥ ጅማሮ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ተፅዕኖ ሳይፈጥሩ ዘመናትን የተሻገሩ አፍሪካዊ ተቋማት ዓላማቸውን ለማሳካት ስለ አፍሪካ አፍሪካዊነትን ተላብሰው መሥራት ይኖርባቸዋል።
የዘንድሮው የአህጉሪቱ መሪዎች ጉባዔ በአህጉሪቱ ላይ የተጋረጡ የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነትን በመሳሰሉ ችግሮች ላይ መምከር ይኖርባቸዋል። ምዕራባውያን አህጉሪቱን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ እንድትማቅቅ እያሴሩ ናቸው። ከማሴርም አልፈው በከሀዲዎች በኩል ጥቃት እየሰነዘሩ ናቸው፤ በማያገባቸው እየገቡ ሲፈተፍቱ ይታያሉ፤ በአህጉሪቱ አገሮች ለእነሱ የሚታዘዝ መንግሥት ለመተከል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ይህ ሁኔታ በአገራችን ላይ በግልጽ ታይቷል። ኢትዮጵያውያን ይህን ጫና አሻፈረኝ በማለት ለእነዚህ ኃይሎች ሴራ የማይንበረከኩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ተላላኪያቸውን አሸባሪውን ትህነግ በጦር ግንባር ድል በመምታት ቅስሙን ሰብረዋል። በበቃ /ኖ ሞር/ ዘመቻ ምዕራባውያን ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ በመላ ዓለም አስተጋብተዋል፤ ይህን ዘመቻቸውን የምዕራባውያኑን ሴራ የተገነዘቡ የዓለም ሕዝቦች በተለይ አፍሪካውያን ወንድሞቻቸውን ሁሉ ተቀላቅለውታል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔው አፍሪካዊ መሆን አለበት ብላ የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት በመቃወምና በመዋጋት ብዙ ርቀት ተጉዛለች። ለእዚህም እነ ግብጽ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጉዳይ ወደ አሜሪካ በወሰዱበት ወቅት ጉዳዩ አፍሪካዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው አስገንዝባ ሥራውም ተጀምሮ እንደነበር አስታውሳለሁ።
አሸባሪው ትህነግና ተባባሪዎቹ በተለያዩ ጉዳዮች ተመድ ድረስ ሄደው ኢትዮጵያን ሲከሱም ችግሩ አፍሪካዊ መፍትሔ ነው የሚያስፈልገው ባለችው መሠረት እየተሠራ ነው።
በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ድምጽ መሰማት የሚያስችለው ተግባር መከናወን አለበት በማለት እያሳሰበችም ትገኛለች። ጉባኤ አፍሪካውያን ኢትዮጵያ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሊጭኑባት የሞከሩ ምዕራባውያን፣ ከተላላኪያቸው አሸባሪው ትህነግ ጋር የከፉቱትን የተቀናጀ ጦርነት በድል በተወጣችበትና ምዕራባውያኑ የሀፍረት ማቅ በተከናነቡበት ማግስት መካሄዱም ትርጉሙ ብዙ ነው። ኢትዮጵያ ይህ ድል የእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች ቅስም የተሰበረበት እንደመሆኑ የአድዋ ድል ያህል ትቆጥረዋለች። ይህም የአፍሪካ አገሮች ብዙ ተሞክሮ ሊቀስሙ የሚችሉበት ነው።
አፍሪካ በተመድ ይበልጥ እንድትሰማ የሚያስችለው ይህ ሀሳብ እና የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሔ የሚሉት እንዲሁም ምዕራባውያን ከአፍሪካም ላይ እጃቸውን ያነሱ ዘንድ በመሪዎች በተናጠል ሲካሄድ የነበረው የሁለትዮሽና ባለብዙ ዘርፍ ውይይት በእዚህ የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤም መወያያ ሊሆን ይገባል።
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አፍሪካውያን በጋራ ድምጻቸውን እንዲያሰሙና አቋማቸውን አንድ እንዲያደርጉ ጉባኤውን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል። አፍሪካ በኢኮኖሚ ስትበለጽግ ድምጽዋ ይበልጥ መሰማት የሚጀምር ቢሆንም፣ አሁን ያላት ሕዝብ ብዛት በራሱ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት መሰማት ያለበት እንዲሰማ ማድረግ ላይ የመሥራትን አስፈላጊነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ ሲያስገነዝቡ እንደተናገሩት፤ አፍሪካውያን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ድምጸቸው ይሰማ ዘንድ ይህ ጉባኤ ይህን ጉዳይም አጀንዳው አርጎ ሊመክርበት ይገባል።
የአፍሪካውያን ችግሮች ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ ከምዕራባውያን ጫናና ጣልቃ ገብነት በተመድ ተገቢውን ቦታ ካለመያዝ የሚመነጩ ናቸው። እነዚህ በኢትዮጵያ ደረጃ ሲነሱ የነበሩና የበርካታ አፍሪካውያንም አጀንዳ መሆን የቻሉ አፍሪካዊ ጉዳዮች ተመክሮባቸው አፍሪካዊ ቢደረጉ አፍሪካውያንን እንደ አፍሪካ ማቆም ይቻላል፤ ይህ ሲሆን አብዛኞቹ የአፍሪካ ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 25/2014