የ ኑሮ ውድነት ሰዎች አብዝተው እየተማረሩበትና በእጅጉ እየተገረሙበት ሰርክ የሚያሰላስሉትና የሚያብሰለስሉት አብይ ጉዳያቸው ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዓመት ዓመት ከፍ እንጂ ዝቅ የማይለው የኑሮ ውድነት በተለይም በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ በጉልህ የሚታይና ሸማቹን እየፈተነ የሚገኝ ሲሆን በተለይም የኑሮ ውድነቱ በመንግሥት ሠራተኛው ላይ እያደረሰ ያለው ጫና በእጅጉ የበረታ ስለመሆኑ ይነገራል።
በዚሁ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችም ያረጋገጡልን ይህንኑ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሚገኝበት አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሕንጻ ውስጥ አራዳ ማርት የሚባል የገበያ ማዕከል ይገኛል።
በዚሁ የገበያ ማዕከል ውስጥ ታድያ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሲሸማምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ አበባ ይበልጣል የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እንዳልተቻለ ሲገልጹ፤ ‹‹ሁሉም ነገር ዕለት ዕለት እየጨመረ በመሆኑ በኑሮ ውድነቱ የማይማረር የለም በተለይም በአሁን ወቅት የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ከሰዎች የመግዛት አቅም ጋር በፍጹም ሊጣጣም የሚችል አይደለም›› በማለት ሲገልጹ፤ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ በሚሠራበት አቅራቢያ የሚገኙ የገበያ ቦታዎችን የመፈለግና በመኖሪያ አካባቢው ካለው ገበያ ጋር በማወዳደር የአንድና የሁለት ብር ለውጥ ካገኘ መግዛትን ይመርጣል የሚሉት ወይዘሮ አበባ፤ እርሳቸውም ቦታው ለመሥሪያ ቤታቸው ቅርብ በመሆኑና የተወሰነ ቅናሽ አለው የሚል መረጃ አግኝተው የመጡ መሆኑን ገልጸው እንደተባለውም መጠነኛ የሆነ ቅናሽ አይቻለሁ። ያም ቢሆን ግን የኑሮ ውድነቱ መግለጽ ከሚቻለው በላይ ነው ለዚህም ነው ሰዎች የእሁድ ገበያን ጨምሮ የተወሰነ ቅናሽ አለ በተባለበት ሁሉ ተዘዋውረው መሸመትን የሚመርጡት በማለት እርሳቸውም በገበያ ማዕከሉ መገኘታቸው ለዚሁ እንደሆነ ተናግረዋል።
‹‹በልቶ ማደር ግድ ነውና እንታገላለን›› የሚሉት ወይዘሮ አበባ፤ ዛሬ ላይ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን በተለይም ለሕጻናት አስፈላጊ የሆኑ እንደ ወተት፣ እንቁላል፣ ፍራፍሬ የመሳሰሉትን ገዝቶ ለመመገብ እጅጉን አዳጋችና የማይታሰብ እየሆነ መምጣቱን በማንሳት የአብዛኛው ሰው ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት በዚህ ጊዜ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ እንደ ጽዳትና የመልዕክት ሠራተኞች ደመወዛቸው ከ1200 እስከ 1500 ብር ሲሆን የቤት ኪራይ የሚከፍሉት 1500 ብር ድረስ በመሆኑ በወር የሚያገኙትን ለቤት ኪራይ ከፍለው በልቶ ለማደር እጅጉን እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
ከእነሱ ሻል ያለው የመንግሥት ሠራተኛም ቢሆን የገቢውን ከፍተኛ ድርሻ የሚያወጣው ለቤት ኪራይ እንደመሆኑ ቀሪው ኑሮውን ማሸነፍና በልቶ ለማደር የሚያስችለው አይደለም።
እያንዳንዱ ነገር በየጊዜ እየጨመረ በመሆኑ በአሁን ወቅት ደግሞ ይበልጥ ተባብሶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። አንድ ኪሎ ብርቱካን 90 ብር ገዝቶ የሚመገበው ምን ያህል ሰው ነው ተብሎ ቢታሰብ በጣም ትንሽ ቁጥር ነው። በመሆኑም የኑሮ ውድነቱ አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍል እየፈተነ ይገኛል። በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ያለው አብዛኛው ሰው በአሁን ወቅት ምሬት ውስጥ የገባ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ አበባ፤ ጊዜው እጅግ አስቸጋሪና ከባድ እንደሆነም ገልጸዋል።
ታድያ አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ከመድረሳችን ባለፈ መንግሥት መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚጠበቅበት መሆኑን ጠቁመው ይህ ካልሆነ ግን ቀጣዩ ጊዜም ይበልጥ አስፈሪና አሳሳቢ እንደሚሆን ከወዲሁ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ። መንግሥት ከውጭ በሚያስገባቸው የፍጆታ ዕቃዎች ላይ በተደጋጋሚ ማሻሻያ ያደረገ እንደሆነና ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መፍቀዱን ሲናገር ይሰማል ነገር ግን መሬት ላይ ያለው ዕውነታ መንግሥት እየሠራሁ ነው ከሚለው በተቃራኒ ሆኖ ይታያል ብለዋል።
ዘይትን በአብነት ያነሱት ወይዘሮ አበባ አምስት ሊትር ዘይት በአሁን ወቅት 640 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሆነና
ነገር ግን መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከቀረጥ ነጻ አስገባኋቸው ከሚላቸው የፍጆታ ምርቶች አንዱ ዘይት ነው። ስለዚህ ችግሩ የት እንዳለ መንግሥት ማየትና መረዳት አለበት በተለይም መሬት ላይ ያለውን እውነታ በተጨባጭ መረዳትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ይገባዋል በማለት እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት መንግሥት መላ ሊፈልግለት እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።
በአገሪቱ ሲንከባለል የመጣው የመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች የዋጋ አለመረጋጋትና የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመምጣቱ ዋናው ምክንያት ምንድነው መፍትሔውስ ብለን ላነሳነው ጥያቄ በዋናነት ሁለት መንስኤዎች መለየታቸውን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ እቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ወይዘሮ መስከረም ባህሩ አስረድተዋል። በአገሪቱ የዋጋ መረጋጋት እንዳይኖር መንስኤ እየሆኑ ነው ተብለው በዋናነት የተለዩት ሁለት ናቸው። በአሁኑ ወቅት በተለይም ከውጭ በሚገቡ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች በየጊዜው ጭማሪ እየተደረገ ነው።
ነዳጅ፣ ዘይት፣ ስኳር የመሳሰሉ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መንግሥት የፈቀደላቸው ምርቶች የዓለም አቀፍ የዋጋ ጭማሪዎች በየጊዜው እያሳየ ነው።አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይህንን ነው የሚያመላክተው። ይህ በገበያ ዋጋ እንዳይረጋጋ የሚያሳድረው የራሱ ተፅዕኖ አለው። ሁለተኛው ደግሞ ሸቀጦቹ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ በተለይም የግብይት ሰንሰለቱ መርዘም፣ አንዳንድ ምርቶች ላይ የደላሎች ጣልቃ ገብነት መኖር የመሳሰሉ ጉዳዮች የሸቀጦች የመሸጫ ዋጋ ከፍ የማድረግ አቅም አላቸው።
ስለዚህ ዓለም አቀፍ የመግዣ ዋጋ መጨመርና በአገር ውስጥ ደግሞ የደላላ ጣልቃ ገብነት የስርጭት ሰንሰለቱን ስለሚያረዝመው ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ደግሞ ፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን የሚፈጥራቸው ጫናዎች አሉ። እነዚህ ተደማምረው ነው በየጊዜው የዋጋ ጭማሪዎችን እያስከተለ ያለው። በተለይም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዓለም አቀፍ ሁኔታ ምክንያት ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማሳደሩ ምርቶች በአገር ውስጥ በፋብሪካም ይሁን በአርሶ አደሩ የሚመረቱበት እና አቅርቦቱ ከፍ እንዲል የማድረግ ጥረት ይደረጋል።
ከስርጭት ጋር ተያይዞ የግብይት ሰንሰለት መርዘም የፈጠራቸው የዋጋ ጭማሪዎችም አሉ። የስርጭት ሰንሰለት መርዘምን ለማሳጠር፤ በተለይም በሕግ አግባብ እንዲሆን የማድረግ ሥራ እንደ መንግሥት እየሠራበት ይገኛል።
አምራቹ ወይም አስመጪው ቀጥታ ከሸማቹ ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ በአዲስ አበባ የተጀመሩትን የእሁድ ገበያዎችን በክልሎች ከተሞች የማስፋት ሥራዎች ይሠራሉ። በተለይም ባዛሮችና ሌሎችም መድረኮች የሚፈጠሩበት ሁኔታዎች አሉ። የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያዎችም በየአካባቢዎቹ እንዲቀርቡ እየተደረገ ሲሆን በተለይም በአትክልትና በንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን እንዲያቀርቡ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከዚያ በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በተለይም ከቀረጥና ታክስ ነጻ እየገቡ ያሉ ምርቶች በስርጭት ሰንሰለት መርዘም እንዳይከሰት የተለያዩ ጥናቶችን ከማድረግ ጀምሮ፣ አስመጪዎችን የማወያየት እንዲሁም አሰራሮችን የመዘርጋት ሥራዎች እየተሠራ ነው።
ስለዚህ በሕግ በተቀመጠው መሠረት ብቻ ስርጭት ሰንሰለት ጤናማ አድርጎ የመሄድ ሥራዎች እየተሠራ ይገኛል። እነዚህ ሥራዎች በሁሉም አካባቢዎች ከተተገበሩ በተወሰነ ደረጃ የሕገ ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነቶችን እየቀነስን የምንሄድበት አዝማሚያዎች ካሉ የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር የሚያስችል ስለመሆኑም አስረድተዋል። የገበያው ዋጋ አለመረጋጋት ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ እንደሆነ ቢያሳውቅም ችግሩ ሲባባስ እንጂ ሲሻሻል አይስተዋልም ይሁንና አንዳንድ ሸቀጦች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ የተወሰነው በቅርቡ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ውጤት አላስመዘገበም።
ስለዚህ በቀጣይ እስካሁን ከሚወሰደው እርምጃ በተለየ መንገድ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በመሥራት ውጤት ለማምጣት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ እ.ኤ.አ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ከቀን ወደ ቀን እጅጉን እየተባበሰ ነው።
ታዋቂው የጉተንበርግ ዩኒቨርሲቲ ባጠናው ጥናት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየታመሰ መሆኑን አመላክቷል። የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርቶች የሚያጠናክሩት ይሄንኑ ሐቅ ነው። በተለይ በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው አይነት የዋጋ ግሽበት እንዳጋጠማት የማዕከላዊ ስታተስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት ያሳያል። በ2014 ዓ.ም የመስከረም ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 34 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የኤጀንሲ ወርሐዊ ሪፖርት አመላክቷል። በዚሁ ወር የምግብ ነክ ዋጋ ግሽበት ደግሞ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 42 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ይህ የዋጋ ግሽበት የፈጠረው ድንጋጤ ሳንለቅ በጥቅምት ወርም 33 በመቶ የነበረው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት በኅዳር ወር ወደ 35 በመቶ ማደጉ ተሰምቷል። በሰዎች የቀን ተቀን ሕይወት ላይ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የምግብ ፍጆታ ላይ የታየው የዋጋ ግሽበት በጥቅምት ወር ከነበረው 28 በመቶ በኅዳር ወር ተባብሶ 41 በመቶ መድረሱም፤ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ እንዳደረገው እየተነገረ ነው። በተለይ በዳቦና እህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በያዝነው ወርም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የሩዝ፣የእንጀራ፤ የዳቦ፤ የጤፍ፤ የስንዴ፤ የማሽላ፤ የበቆሎ፣ የገብስ፣ የስንዴ ዱቄት፣ የፓስታና ማካሮኒ ዋጋ በፍጥነት ጨምሯል። ሥጋ፣ የምግብ ዘይት ፣ ወተት፤ አይብና ዕንቁላል፤ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም እና የመሳሰሉት ምግብ ነክ ነገሮች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ከመጠን በላይ በማደጉ እነሥጋ፣ የምግብ ዘይት ፣ ወተት፤ አይብና ዕንቁላል፤ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም እና መሰል ነገሮች እጅግ የተጋነነ ዋጋን በመያዛቸው እነዚህን ምግቦች ገዝቶ መጠቀም በተለይ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ እርከን ላይ ለሚገኙ ዜጎች የቅንጦት ምግቦች ከሆኑ ውለው አድረዋል። አሁን አሁን ደግሞ በመካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ይገኛል የሚባለውም የማኅበረሰብ ክፍል እነኝህ ምግቦች ቅጦንት እየሆኑበት መምጣት ጀምረዋል።
መንግሥት ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ሲንከባለል የመጣውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የተለያዩ መፍትሔዎችንና የማስተካካያ እርምጃዎችን ሲተገብር ይስተዋላል።
ነገር ግን ችግሩ ሥር የሰደደና የቆየ በመሆኑ በሚወሰዱ እርምጃዎችና በሚዘረጉ አዳዲስ አሠራሮች የኑሮ ውድነቱ ሲሻሻል አይስተዋልም። ይሁን እንጂ አሁንም ማኅበረሰቡ ችግሩን በዘላቂነት ተፈትቶ ማየትን ይናፍቃል፤ ይመኛልም።
ለኑሮ ውድነቱ ምክንያቶች ናቸው ተብለው በጥናት የተለዩትን አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት ኑሮውን ማረጋጋት አሁንም ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥር 25/2014