ይህን ሰሞን አገራችን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና ሌሎች ተያያዥ ስብሰባዎች የሚካሄዱበት ነው። በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችንም በ1963 በተቀራራቢ ወራት የተከናወኑ የኅብረቱን ጉባኤ፣ የመሪዎች አቀባበልን የሚመለከቱ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።
ጃንሆይ የሞሮኮንና የጊኒን መልዕክተኞች አነጋገሩ አዲስ አበባ ፤
(ኢ-ዜ-አ-) ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትናንት ከዕኩለ ቀን በፊት፤ለ፲፮ኛው የአፍሪካ አንድት ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ ተካፋይ ለመሆን ከመጡት መካከል ፤የሞሮኮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ሚስተር ዩሴፍ ቤን አባስንና በሚኒስትር ማዕረግ የጊኒ መንግሥት ፕሬዚዳንት ዲሬክተር ሚስተር ካማራ ጃማታኝን በየተራ በኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚሁ የንግግር ሥነ ሥርዓት ላይ የሞሮኮ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሞሮኮው ንጉሥ ከዳግማዊ ሐሰን ዘንድ የተላከውን መልዕክት ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አቅርበዋል። ቀጥሎም የጊኒ መልዕክተኞች መሪ በበኩላቸው ከፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ዘንድ የተላከውን መልዕክት ለግርማዊነታቸው አቅርበዋል።
የሁለቱንም መንግሥታት መልዕክተኞች በየተራ ለእኩል ሰዓት ያህል ባነጋገሩበት ወቅት ፤ክቡር ጸሐፌ ትዕዛዝ ተፈራወርቅ ኪዳነወልድ የግቢ ሚኒስትር ተገኝተዋል። (የካቲት 21 ቀን 1963 ዓ.ም )
በዩጋንዳ ጉዳይ የአፍሪካ ሚኒስትሮች በሃሳብ ተለያዩ
በአፍሪካ አዳራሽ ሰሞኑን የተከፈተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አስራ ስድስተኛው መደበኛ የሚኒስትሮች ጉባኤ ትናንት ቀኑን ሙሉ በዩጋንዳ ጉዳይ ተነጋግሮ በመልዕክተኞቹ መካከል የሃሳብ መለያየት በመፈጠሩ፤ምንም ውሳኔ ሳያደርግ ቀርቷል። ጉባኤው በሀሳብ የተለያየው፤አዲሱን የዩጋንዳ መንግሥትና የቀድሞውን የዶክተር አቦቴን መንግሥት በመወከል ከመጡት ሁለት የተለያዩ መልዕክተኞች የትኞቹ በጉባኤው ላይ ተካፋይ መሆን ይችላሉ? በሚል ጉዳይ ነው። ከቀትር በኋላ የመልዕክተኞቹ መሪዎች ብቻ ዝግ ጉባኤ አድርገው የመጨረሻ ውሳኔ ሰኞ እንዲደረግ ተስማምተዋል።
መልዕክተኞቹ እስከ ሰኞ ድረስ ከመንግሥቶቻቸው መመሪያ ጠይቀው በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም እንዲያረጋግጡ ተጠይቀዋል። የሚኒስትሮቹ ጉባኤ ሰኞ እንደገና ሲሰበሰብ፤በዩጋንዳ ጉዳይ የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ፤የሚቀበላቸውን መልዕክተኞች መግለጥ ወይም ጉዳዩ በሚቀጥለው የመሪዎች ጉባኤ እንዲወሰን በቀጠሮ ማስተላለፍ እንደሚሆን ተገምቷል።
አዲሱን የዩጋንዳ መንግሥት በመወከል ለሚኒስትሮች ጉባኤ ከ30 የሚበልጡ መልዕክተኞች ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፤በዶክተር አቦቴ መንግሥት ስም ደግሞ አራት መልዕክተኞች ትናንት ጉባኤው ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ገብተዋል። አራቱን መልዕክተኞች በመምራት ትናንት አዲስ አበባ የገቡት የቀድሞው
የዩጋንዳ መንግሥት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳም አዴካ ናቸው። ሌሎች አምስት የመልዕክተኛ አባሎቻቸው ዛሬ ወይም ነገ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ገልጠዋል። ሁለቱ የዩጋንዳ መልዕክተኞች መሪዎች ትናንት ለየብቻቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፤የዩጋንዳን ሕዝብ የሚወክሉ ሕጋዊ መልዕክተኞች መሆናቸውን አመልክተዋል።
አዲሱ የዩጋንዳ መንግሥት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶክተር ዋኑሜ ኦቤዲ ትናንት በሰጡት መግለጫ ፤ዶክተር አቦቴን በመደገፍ አዲስ አበባ የመጡት መልዕክተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጋብዘዋቸው ከተመለሱ በኋላ ምንም ርምጃ የማይወሰድባቸው መሆኑን አረጋግጠዋል። (የካቲት 21 ቀን 1963ዓ.ም )
የአፍሪካ የሕዝብ ቆጠራ ጥናት ጓድ መምሪያ አወጣ
በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አማካይነት በአፍሪካ አዳራሽ ከጥር ፲ እስከ ጥር ፲፬ /፷፫ ዓ.ም ተሰብስቦ የነበረው ስለአፍሪካ የሕዝብ ቆጠራ አሠራር ለአፍሪካ አገሮች መምሪያ እንዲሰጥ የተመረጠው የኤክስፐርቶች ጓድ ፤በስብሰባው መጨረሻ ላይ ለሕዝብ ቆጠራ ፕሮግራም የሚሆን መሠረታዊ መምሪያ ማጽደቁን ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተገኘው ዜና ገልጧል። ጓዱ ከአምስት ቀን ስብሰባ በኋላ፤ ባወጣው መግለጫ ፤ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝብ ቆጠራን ሥራ በገንዘብ የሚረዱ ሌሎች አገሮችም መኖራቸውን ገልጧል።
እነዚህ አገሮች በዚህ ረገድ ለአፍሪካ የሚያደርጉት ርዳታ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በኩል እንዲሆንና ኮሚሽኑም መሪ ሆኖ እንዲሠራ የሚሹ መሆናቸውን ዜናው አስረድቷል። ስብሰባው ለሕዝብ ቆጠራ ፕሮግራም አስፈላጊውን መረጃ በማንኛውም ጊዜ መስጠት እንዲችል ሆኖ መሥራት እንዳበት አሳስቧል። ለዚህም እንዲረዳውና ፕሮግራሙንም በሥራ መዋሉን የሚቆጣጠር አንድ አማካሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ማሳሰቡን ዜናው ገልጧል።
በስብሰባው ላይ የአሜሪካ ፤የምዕራብ ጀርመንና የካናዳ መልዕክተኞች በአፍሪካ አገሮች በሕዝብ ቆጠራ የተሰማሩ ሁሉ መተባበር እንዳለባቸው ገልጠዋል።የሚያደርጉትም ርዳታ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በኩል እንዲሆን እንደሚሹ አስረድተዋል።
በስብሰባው መጨረሻ በሚስተር ሮበርት ጋርድነር በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ስም ሚስተር ሶም የኮሚሽኑ የሕዝብ ጥናት ክፍል ኃላፊ ለአፍሪካ መንግሥታት ትክክለኛ የሆነ የሕዝብ ቆጠራ መረጃ አሰባሰብ ዘዴና መምሪያ በመስጠት በኩል ያለው ችግር ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጸው፤ የኤክስፐርቱ ጓድ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ቆጠራ በኩል ለሰጠው መመሪያ አመስግነዋል።
ከሚስተር ሶም ንግግር በኋላ ሚስተር ሊንከን ዲ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝብ ቆጠራና የሶሺያል እስታትስቲክስ ክፍል ኃላፊና፣ሌሎች የሕዝብ ቆጠራና የእስታትስቲክስ ክፍል ኃላፊዎች ባደረጉት ንግግር ስብሰባው አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ጥሩ ውጤት ያስገኘ መሆኑን መግለጣቸውን ዜናው አስረድቷል።
(ጥር 16 ቀን 18 63 ዓም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 24/2014