
ድሬዳዋ፡– በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 15 በመቶ አገልግሎት ላይ እንዳልዋለ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሰሞኑን ‹‹ስለኢትዮጵያ መሠረተ ልማት›› በሚል በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት በድሬዳዋ ከተማ በተካሔደው መድረክ ላይ በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች ማምረት ከምትችለው 150 ጌጋ ዋት ውስጥ 6 ነጥብ 4 ጌጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል እያመረተች ትገኛለች። ከዚህ ውስጥ ከባከነው 35 በመቶ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ 15 በመቶ አገልግሎት ላይ እየዋለ አይደለም።
የሕዳሴው ግድብ ሙሉ ለሙሉ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር የኢትዮጵያ አቅም ወደ 9 ጌጋ ዋት እንደሚያድግ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይሁንና ሕዳሴው ግድብ ተመረቀ ማለት እያንዳንዱ መንደር ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛል ማለት አለመሆኑን ከወዲሁ መገንዘብ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከሕዳሴው ግድብ ግንባታ የማይተናነስ ወጪ በማውጣት በሺህ ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የመሥመር ዝርጋታ እንደሚያስፈልግ ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሃይል ማስተላለፍያ እና ማሰራጫ ሥራዎች ላይ በብዛት መሰማራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የሃይል መሠረተ ልማቱ በደጃቸው የሚያልፉ ዜጎች እንዲያገኙ ብሔራዊ ስትራቴጂ ተቀርፆ እንደነበር አስታውሰው፤ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም መቀረፁን እና በቀጣይም እያንዳንዱ ግለሰብ ከአቅራቢያው የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያገኝ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
አሁን ያለውን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅምን ማሳደግ እንዲሁም ስብጥሩን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር አባል ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ ለጎረቤት ሀገራት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች መሆኑ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለጂቡቲ፣ ለሱዳን፣ ለኬንያ፣ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች መሆኑን አስታውሰው፤ አሁን ምንም ዓይነት እጥረት እንደሌለ ጠቁመዋል። ይህ ወደ ፊት እጥረት እንደማያጋጥም ማረጋገጫ አለመሆኑን አስታውሰው፤ የሃይል ምንጭ አማራጭ ስብጥር መኖር አለበት ብለዋል።
በቀጣይም የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ከደቡብ አፍሪካ የኃይል ትስስር ጋር ለማገናኘት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ተገናኝታለች። ኬንያ ከዛምቢያ ጋር ትገናኛለች፤ ዛምቢያን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለማገናኘት እየተሠራ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር መገናኘቷን በመጠቆም፤ ሱዳን ከግብፅ ጋር ትገናኛለች፤ ግብጽን ከጆርዳን ጋር በማገናኘት ከአውሮፓ ጋርም ለማስተሳሰር መታቀዱን አብራርተዋል።
ኃይል ለመሸጥ የኢነርጂ ብቃትን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን አቅርቦት እና ፍላጎት ላይ ሚዛን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ከምንም በላይ የኢነርጂ ብቃትን ለማሻሻል የግል ዘርፉ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም ላለፉት 30 ዓመታት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ፖሊሲ አለመኖሩን አስታውሰው፤ አሁን ግን ለኢንቨስተሩ ምቹ ፖሊሲ በመቀረፁ፤ በተለይ ሃይልን ለማስተላለፍም ሆነ ለማሠራጨት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም