
አዲስ አበባ፦ የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የግብርና ዘርፎች እንዲሳተፉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጠየቁ።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በአንጎላ ሉዋንዳ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባዔ ጎን ለጎን የአፍሪካና የአሜሪካ የግብርና፣ የምግብ እና የቢዝነስ ዘርፍን ለማጠናከር ያለመ የፓናል ውይይት ላይ እንደገለጹት፤ አሜሪካ አሁን ላይ በአፍሪካ ያላትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግ ያላትን ፍላጎት አድንቀዋል። የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
አፍሪካ የአሜሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻ የሚሆን አቅም እንዳላት ጠቅሰው ፤ በአፍሪካ በኩል ሊለማ የሚችል መሬት፣ የሰው ሀብትና ትክክለኛ ፖሊሲ መኖሩን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በተለይም ጠንካራ የምግብ ሥርዓት መዘርጋት፣ አስተማማኝ የንግድ ትስስር መፍጠርና በምርቶች ላይ እሴት የሚጨምር ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ከዚህ አንጻር የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ለመሳተፍ የሚጋብዝ ከፍተኛ አቅም እንዳለ ጠቁመው ይህም በቅርቡ በተግባር ተፈትኖ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ ለእርሻ ሥራ መዋል የሚችል ሰፊ ለም መሬት ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን የግብርና ሥራ ሊያከናውን የሚችል የሰው ሃይል ያላት መሆኗንም ገልጸዋል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ በተለይም ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር በተለይም በስንዴ ምርት ላይ በጥቂት ዓመት ውስጥ ከፍተኛ እመርታ ተመዝግቧል ነው ያሉት።
የአሜሪካ የዘርፉ ተዋናዮች በኢትዮጵያ በተለይም በጥጥ፣ በአቮካዶ እና በስንዴ ምርት ላይ ቢሳተፉ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ከተጨባጭ አሃዛዊ መረጃ ጋር በማቅረብ አስረድተው፤የአሜሪካ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ለረጅም ዓመት የሚዘልቅ መሆን እንዳለበት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በፓናሉ ከፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በተጨማሪ የኮትዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር ሮቤርት ቡግሬ ማምቤ እና የኤስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ሚሶ ድላሚኒን ጨምሮ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ኩባንያዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም