
አዲስ አበባ፡– ለኢትዮጵያ ጥቅምና ህልውና ሥንሠራ አንዳንዶቻችን የሕይወት ዋጋ እንከፍላለን፤ አንዳንዶቻችን በኑሮ እንቸገራለን ሲሉ ጥቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተናገሩት፤ ከልመና ነጻ ለመውጣት መወሰን ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ አለባት ተብሎ በተጀመረው ንቅናቄ ቢበዛ ከሁለት ዓመት በኋላ ነጻ ትወጣለች። ለኢትዮጵያ ጥቅምና ህልውና ስንሠራ አንዳንዶቻችን የሕይወት ዋጋ እንከፍላለን፤ አንዳንዶቻችን በኑሮ እንቸገራለን፤ አንዳንዶቻችን ምግብ ባንቸገርም ብዙ ጫና ሊበዛብን ይችላል፤ ሁሉን ችለን እና ወስነን ኢትዮጵያን ማሻገር ይኖርብናል ብለዋል።
ከለውጡ በፊት የነበረን የጤና ፖሊሲ መከላከል ላይ የተመሠረተ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከለውጡ ወዲህ ግን ፖሊሲው ማከም ላይም ተመሳሳይ ትኩረት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
በኮሪዶር ልማት የተሠሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የህጻናት መዋያ ቦታዎች፣ በሽታን ለመከላከል የሚረዱ እንደሆኑም ጠቅሰዋል። የበሽታ መንስኤ የነበሩ ቦታዎችን ወደ ጤናማ ሥፍራነት ለመቀየርም ብዙ ተደክሟል ብለዋል። ስለሆነም ሁሉም የሚሠራው የልማት ሥራ ከጤና ጋር በቀጥታ ይገናኛል ሲሉ አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲና በጤና ግንባታ ያለውን ወጪ ሳያካትት
ከጥቂት ዓመታት በፊት ለጤና ሚኒስቴር ይፈስ የነበረው ሀብት 70 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ግን 130 ቢሊዮን ሀብት የሚፈስ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና ይህ ወጪም ቢሆን በቂ ነው እንደማይባል ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ6 ሺህ በላይ አዳዲስ ጤና ጣቢያ፣ ጤና ኬላና ሆስፒታሎች መገንባታቸውን፣ መታደሳቸውን እና መስፋፋታቸውን ተናግረዋል። መንግሥት ከዚህም በላይ የማድረግ ፍላጎት ቢኖረውም የአቅም ውሱንነት የገታው መሆኑንም አንስተዋል።
እንደሀገር በመንግሥት የሚተዳደሩ ከ22ሺህ በላይ የጤና ተቋማት እንዳሉ ጠቅሰው፤ እነዚህ በአንድ ጊዜ ይታደሱ ቢባል ብቻ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የጤና ሙያተኞች ቁጥር 219ሺህ መሆኑን አመልክተው፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በእጥፍ አድጎ ሙያተኛው 520ሺህ መድረሱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ እንድትወጣ መከራን ተጋፍጦ ማሻገር ከእኛ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል። የድህነታችን መገለጫ በጣም ብዙ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ካልወሰንን በቀር ከችግራችን መውጣት አንችልም ነው ያሉት። ቢያንስ ልጆቻችን ከዚህ አይነት መከራ እንዲወጡ የሁሉ ነገር መሠረት የሆነውን ድህነትን እንዴት አድርገን እንቀይረው? ካላልን በቀር፤ የተሟላ ምላሽ መስጠት ያስቸግራል ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሀኪሞች ለምን የደመወዝ ጥያቄ አነሱ ብሎ የሚያስብ ሰው አለ ተብሎ እንደማይታሰብ ጠቅሰው፤ ጥያቄው የጦርነት መልክ መያዙን ግን ተገቢ ነው የሚል እንደማይኖር ገልጸዋል። ጥያቄዎችን ከሙያ ግዴታ፣ ከሕግ እና ከማህበረሰባዊ መሪነት አንጻር መመልክት ይገባ እንደነበርም አንስተዋል።
በሀኪሞች እጅ ብዙ ሰዎች መዳናቸውን እና ብዙ ያለቀሱ ሰዎች እንባቸው መታበሱን ጠቅሰው፤ ሀኪሞች ጥያቄ ማቅረባቸው ትክክል ቢሆንም የሚጠይቁበት መንገድ ትክክል አለመሆን ግን ነገሮችን ያበላሻል ብለዋል። የጤና ሴክተር ሆኖ ችግርን ለመፍታት ጤናማ መንገድ አለመከተል ፤ ችግሩን የሚያባብስ እንደሚሆንም አስረድተዋል።
ሀኪም አገልግሎት ሰጪ ሆኖ ሳለ፤ አገልግሎት ሰጥቶ የማያውቅ ሰው ጥያቄውን ጠልፎ እንዲነዳ እድል መስጠት ትክልል እንዳልሆነም ተናግረዋል። ‹‹አንቅልፍ አጥተን ሰው ለማዳን እየሠራን ነው፤ ልጆቻችንን ጎድተን ነው የምንሠራው፤ ኑሯችን ይታሰብበት›› የሚለው የሙያተኞቹ ትክክለኛ ጥያቄ ፤ እንቅልፍ አጥቶ ማገልገል ምን እንደሆነ በማያውቅ ሰው ተጠልፎ ለሌላ ዓላማ መዋል እንደሌለበት አስረድተዋል።
ሶስት አይነት መልክ ያላቸው አካላት እንዳሉ ጠቅሰው፤ የመጀመሪያዎቹ ጤናማ ሙያተኞች (በቅንነት ደክመው ፤ ችግር ጓዳቸው ስለገባ ለምን አንታይም ብለው ጥያቄ የሚያነሱ፤ ሁለተኞቹ አገልግሎት እና ሀገር ግንባታ ምን እንደሆነ የማያውቁ፤ ሁሉን ነገር ከደመወዝ ጋር ብቻ የሚያያይዙ፣ ከእለት ጉርስ ያለፈ እሳቤ የሌላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። ሶስተኞቹ ሀኪም መሳይ ወይም ገዋን ለባሽ ፖለቲከኞች፣ ከህክምና ተቋም የዓመት እረፍት ወስደው፤ የፌስ ቡክ ስም ቀይረው ጉዳዩን የቀሰቀሱ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
ባክቴሪያ ወይም ቫይረስ ወደ ሰው መግቢያ መንገድ ካገኘ በኋላ ሰውነት ውስጥ ተለጥፎ ምግብን እየተሻማ አካልን እንደሚጎዳ ሁሉ ደመወዝን እንደስስ ብልት ተጠቅመው እና ተለጥፈው፤ የሙያተኛውን አገልግሎት ያጠለሹ ስለመኖራቸው ገልጸዋል።
በአንጻሩም እናት የሆኑ፣ ቅን የሆኑ ፣ ከበሽተኛ ጋር የሚያለቅሱ፤ ብዙ የሚሰቃዩና ውለታ የሚገባቸው ሃኪሞች ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል።
በምክንያት ላይ ተመስርቶ አቅም በፈቀደው መሠረት የደመወዝ እና የጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን ለመመልከት የሚሞከር መሆኑንም ተናግረዋል። የመኖሪያ ቤት ጥያቄም በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደት የሚፈታበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ነገር ግን ድህነት በዘላቂነት የሚጠፋው ኢንቨስትመንቶች ሲስፋፉ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል ፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል። በሚቀጥሉት 15 እና 20 ዓመታት ዛሬ የሚነሱ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙ ስለመሆናቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስረድተዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም