ይህ ጥያቄ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይነሳል።አንዳንዶች እንደውም አይደለም ድርድር ስለማድረግ በዚህ ጦርነት ወቅት የተጎዱ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ደም መና የሚያደርግ እንደሆነ በማመን የድርድርን ወሬ በራሱ መስማትም አይፈልጉም።
መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ ለሕዝብ ባያሳውቅም አጀንዳው ግን የአገሪቱን የፖለቲካ መድረክ እየያዘ ነው።በዚህ ሁኔታ ውስጥም ጥያቄዎች እንደ ቀጠሉ ነው።ችግሮች በድርድር ሊፈቱ የሚችሉ ከሆነ ለምን ይህን ጦርነት ተዋጋን ? ለምንስ ይህን ሁሉ መስዋእትነት ከፈልን? የሚሉ ጥያቄዎች እየቀረቡ ናቸው።
በመጀመሪያ ይህን ነገር ከኢትዮጵያውያን ስነ ልቦና ባህሪ አንጻር መረዳት ይገባል።ኢትዮጵያውያን ጦርነትን በተመለከተ ያለን ልምምድ ጠላትን ሙሉ ለሙሉ መደምሰስ እና በመቃብሩ ላይ ቆሞ አሸናፊነትን ማጽናት ነው ። ታሪካችን የሚያመለክተው፣ በጦርነቱም የጠበቅነው ይሄን ነበር።
የጠበቅነው ጁንታውን ሙሉ ለሙሉ መደምሰስ እና እጅ እንዲሰጥ በማድረግ አሸናፊነትን ማጽናት ነው።ይሁንና ጦሩ ወደ ትግራይ ጁንታውን እያሳደደ ከሄደ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ ሳይገባ በአማራና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲቆም መንግስት ወሰነ።ይህ ብዙዎች የተመኙትን ፍጹማዊ ድል አላስገኘላቸውም።
ድሉ ድል መሆኑን ብዙዎች ቢያምኑም የሚፈለገው አይነት ፍጹማዊ ድል አልሆነላቸውም።በዚህ ቅር የተሰኙት ጥቂት አይደሉም።ይባስ ብሎ የድርድር ወሬ ሲነሳ ብዙዎች ነገሩ ከድልነት ወደ ሽንፈት ተቀየረባቸው።ስለዚህም ለምን ይህን ሁሉ መስዋእትነት ከፈልን? ለምንስ ተዋጋን? የሚል ጥያቄ አነሱ።ጥያቄው ጦርነቱ አስተላለቅ ላይ የተመሰረተ እንጂ የጦርነቱ አላማ እና ግቦች ላይ ያተኮረ አልነበረም።
አንደኛ፤- በእርግጥ ግን መዋጋት ምርጫችን ነበር ወይ? አለመዋጋትስ እንችል ነበር ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች እንያቸው።በመጀመሪያ መዋጋት ምርጫችን አልነበረም።ወደ ውጊያው የተገባው በግድ ነው።የጥቅምት 24 ጥቃት ለጦርነቱ መጀመር እንደ ዋነኛ ነጥብ ይነሳል።
ከዚያም በፊት ግን በመቀሌ በየሳምንቱ የሚደረገው ወታደራዊ ትርኢት፤ መከላከያ ሰራዊቱ ንብረቶቹን እንዳያንቀሳቅስ የሚደረገው እገታ፤ የእዙን መሪ አንቀበልም፤ አናስተናግድም መባሉ፤ ከሁሉም በላይ በጦርነቱ ሂደት እንደታየውም አሸበናሪው ሕወሓት በየቦታው ቀብሮ ያስቀመጣቸው እና በየጊዜው የሚያወጣቸው የጦር መሳሪዎች ብዛት ጦርነቱ በሕወሓት በኩል ቀድሞ ዝግጅት የተደረገበት መሆኑ እና በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው ክህደት የፌዴራሉ መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደዚህ ጦርነት ሳይወዱ በግድ ያለ ዝግጅት እንደገቡበት አረጋቸው።ስለዚህ መዋጋት ምርጫችን አልነበረም።አለመዋጋትም አንችልም።
ሁለተኛው ጉዳይ ፤- በኋላ ድርድር መኖሩ ስለማይቀር አንዋጋም ማለትስ እንችል ነበር ወይ? አንችልም።በኋላ ስለምንታረቅ አሁን እንደፈለጉ ይደብድቡን የሚል አመክንዮ አይሰራም።ጦርነቱንም ተሸናፊ ያረገናል ፤ በድርድር ሂደትም ተንበርካኪ ያደርገናል።ስለዚህ የመጀመሪያው ስራ ጥቃቱን ማስቆም ነው፤ ከዚያም ማጥቃት።በመንግስት በኩል የተሄደበት መንገድም ይሄው ነው።
ነገር ግን ያኔ ድርድር መኖሩ ስለማይቀር አንዘምትም አንዋጋም ብንል ዛሬ ላይ አይደለም የድርድር ወሬ ሁላችንም በሕይወት መኖራችን ያጠራጥር ነበር።ይህ መላምት ሳይሆን ሀቅ ነው።አሸባሪው ሕወሓት ሸዋ ከደረሰ በኋላ የቡድኑ መሪዎች “ጦርነቱ አልቋል፤ ከማን ጋ ነው የምንደራደራው?” በማለት ድርድር የሚባል ነገር እንደማይኖር አስረግጠው መናገራቸው ይታወሳል።
ሶስተኛው ጉዳይ ፤- ድርድር የግድ ነው ወይ? አዎ፤ ይህ የሁሉም ጦርነቶች ባህሪ ነው።ለዚህ ብዙ ምሳሌዎችን ማሳየት ይቻላል።አሸናፊው አካል ድሉን በህጋዊ መሰረት መቋጨት አለበት።ተሸናፊውም ካሁን በኋላ መሰል ተግባር ላለመፈጸም ስምምነቱን በፊርማ ማኖር አለበት።በዓለም ታሪክ ትልቁ የሚባለው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንኳ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ ካለቀ በኋላ በስምምነት ፊርማ ነው የተጠናቀቀው።
ጀርመን እጇን ለመስጠት ቃሏን በፊርማ አሳርፋ ነው ጦርነቱ የተጠናቀቀው።የአውሮፓ አህጉር እስከ ዛሬ ድረስ ፍጹማዊ ሰላም ያገኘው በዚህ መልኩ ነው።አልያም አሸናፊዎቹ እንግሊዝ ፤ ፈረንሳይ ፤ እና አሜሪካ ጀርመንን ሙሉ ለሙሉ ካልደመሰስን ጦርነቱን አናቆምም ቢሉ ኖሮ ምናልባትም የአውሮፓ እጣ ፈንታ ከዚህ የተለየ ይሆን ነበር።
አራተኛው ጉዳይ ፤- መደራደር ግድ ከሆነ ለምን ቀደም ብለን አንደራደርም ነበር? መጀመሪያ መደራደር ያልተቻለው አሸባሪው ሕወሓት ልቡ አብጦ ሁሉንም ሰላማዊ መንገዶች በመዝጋቱ ነው።በሌላ መልኩ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ድርድሩርን ለማድረግ ትክክለኛውን ወቅት መጠበቅ ያስፈልጋል።
ትክክለኛው ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ ሁለቱም እጆቿ ያልታሰሩበት ወቅት ነው።ለምሳሌ አሸባሪው ሕወሓት አዲስ አበባ ዳርቻ ላይ ደርሶ ቢሆን ድርድሩ የሚካሄደው የፌደራል መንግስቱ አንድ እጁ ታስሮ ነበር።አሁን ድርድር ቢካሄድ መንግስት ትግራይን ከብቦ በጁንታው ላይ ብልጫ ይዞ ነው።ስለዚህ አሁን አንድ እጁ የተጠረነፈው ጁንታው ነው።መንግስት ሁለቱም እጆቹ ነጻ ናቸው።
የሰላም አማራጩም ባይሳካ በወታደራዊ መንገድ ነገሩን መቋጨት የሚችልበት እድል አለው።ስለዚህ ድርድሩ እስካሁን እንዲቆይ የሆነው ጦርነቱን ለማስቀጠል ከመፈለግ ይልቅ ወታደራዊ አላማዎች እስኪሳኩ እና ለፖለቲካዊ አላማዎች የሚያመች ሁኔታ እስኪገኝ ድረስ ነው።ይህም የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የጦርነት ባህሪ ለሚረዱ እንግዳ ጉዳይ አይደለም ።
አምስተኛው ጉዳይ ፤- ባንደራደርስ? አለመደራደር ጦርነቱን ለመቀጠል መወሰን ነው።ጦርነቱን መቀጠል የሚያስችለን ኢኮኖሚያዊ ፤ ፖለቲካዊ ፤ ዲፕሎማሲያዊ አቅም አለን ወይ? ቢኖረንስ በዚህ መልኩ ምን ያህል ውጤታማ መሆን እንችላለን? ጦርነቱን ብንቀጥል አሁን ያገኘናቸውን ድሎች እያሰፋን እንሄዳለን ወይስ እያጣን እንሄዳለን? በዚያ በኩል ያለው ሕዝባችን እና ግዛታችን ዘላቂ ህልውናስ ምን ይሆናል? በዚያ በኩል ያለው ወገንስ በጦርነት ብቻ ብናሸንፈው በዲፕሎማሲው ካልደገምነው ነገ ደግሞ ችግር መፍጠሩ አይቀርም ወይ? አሁን አሸባሪው ሕወሓትን ከጀርባው ላይ እንዲያወርድ የምንገፋፋው የትግራይ ሕዝብስ በጫና ብዛት ሕወሓትን ብቻ ሳይሆን መንግስትን መልሶ መታገል አይጀምርም ወይ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ታሳቢ መደረግ አለባቸው።
በጥቅሉ ስናየው ጦርነቱ እና የተገኘው ድል በድርድር ሂደት የሚከስሙ ከንቱ መስዋእቶች ሳይሆኑ በድርድሩ ወደ ሌላ ከፍተኛ ድል የሚሻገሩ ህያው መስዋእትነቶች ናቸው። በዚህ ዘመቻ ለአገሪቱ ህልውና አደጋ የሆነው ሀይል ጡንቻ እንዲሟሽሽ ተደርጓል።
በዚህም የተነሳ ራሱን ከፍጹማዊ መደምሰስ ለማዳን በእርግጫ ብሎት ወደ ሄደው የውይይት ጠረጴዛ ለምኖ እና ሽማግሌ ልኮ ለመመለስ እየጣረ ነው።መንግስትም በሩን በስሱ ገርበብ አድርጓል፤ ቡድኑ ግን በጠረጴዛው ዙሪያ ወንበር ለማግኘት አሁንም የሚቀሩት የቤት ስራዎች አሉ።
እነዚያ ቅደመ ሁኔታዎች በመንግስት እንደቀረቡ እምነት አለ።እነዚህ ቅደመ ሁኔታዎች ሕወሓት ዳግም የኢትዮጵያ ሰላም እና አንድነት አደጋ መሆን የማይችልባቸው ቅደመ ሁኔታዎች በሽማግሌዎች ፊት ቀርቦ መፈረም እና የፈረመበትን ጉዳይ መተግበር አለበት።
ሰራዊታችን የአሸባሪውን ሕወሓትን የጀርባ አጥንት ሰብሯል።የፖለቲካ አመራሩ ደግሞ በፖለቲካ መድረክ ጀርባው የተሰበረውን ሕወሓት በፖለቲካዊ መድረክ እጅና እግሩም እንዲታሰር ማድረግ ይኖርበታል።ከዚያ ውጭ ድርድሩም ሆነ ውይይቱ ሕወሓትን በምንም አይነት መልኩ ቀና እንዲል የሚያደርግ መሆን የለበትም።
በተመሳሳይ ሕዝብም ድርድርን እንደ ሽንፈት ማየት እና የሰራዊቱን መስዋእትነት እንደ ኪሳራ መመልከት ማቆም አለበት።ይህ ሰራዊት ባይኖር ድርድርም ሆነ ሌላ ነገር አይኖርም፤ ኢትዮጵያም አትኖርም።በተመሳሳይ በጦርነት ብቻ ሁሉን ነገር እንፈጽማለን ከሚል የተሳሳተ ተስፋም መውጣት ያስፈልጋል።ይህ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነት ባህሪ ነው። አሸናፊነትንም ማጽናት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነውና።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ጥር 23/2014