ህንዳውያንን ከእንግሊዝ ባርነት ነፃ ለማውጣት ንብረት ሳይወድም የሰው ደም ሳይፈስ በሚደረግ ተቃውሞ ዜጎችን በማስተባበር አመርቂ ሥራ ሠርተዋል። በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የዘር መድሎ በማዋጋት ይታወቃሉ፤ ማህተመ ጋንዲ።
ጋንዲ የተወለዱት በህንድ ካቲዋር ባህረ ገብ መሬት (Peninsula) ከቦምቤይ በስተሰሜን በምትገኘው ፕሮባንድራ ከተማ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ጥቅምት 2 ቀን 1889 ነበር።
በሀገራችን አቆጣጠር ጥር 21 ቀን 1940 ጋንዲ የተገደሉበት 74ኛ ዓመት በመሆኑ ነው ከታሪካቸው በትንሹ ቀንጭበን በዛሬ ሳምንቱ በታሪኩ ዓምዳችን ልነዘክራቸው የወደድነው።
ማህተመ ጋንዲ ራዲቬንድራዝ ታጎሬ የሚል ስያሜም ወጥቶላቸዋል፤ ፍቺውም ታላቁ ነፍስ ማለት ነው። በዘመናቸው ለህንድ የሠሩት አንፀባራቂ ሥራ እየጎመራ ለዓለም ዜጎች ሁሉ ምሳሌ መሆን የቻሉ ናቸው።
አገራችንም በመዲናዋ አዲስ አበባ በስማቸው ሆስፒታል ሰይማለች። የህንዳውያንና የባላንጣዎቻቸው የእንግሊዞች ደም ሳይፈስ ያስተባበሩት ተቃውሞ ለዓለም ህዝቦች ሁሉ ምሳሌ መሆን ችሏል።
የካራማቻንድ ጋንዲ አራተኛ ልጅ የነበሩት ጋንዲ ከበለፀገ ቤተሰብ እና ከህንድ ማህበራዊ ክፍሎች ከፍተኛ መደብ ከነበሩት የተገኙ ሲሆኑ፣ አባታቸው የሦስት አነስተኛ ከተማ ግዛቶች መሪ (ራጃ ) ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። ሞሀንዳስ በታዳጊነታቸው የሰከኑ፤ በትምህርታቸውም በአማካይ ደረጃ ነበሩ።
የልጅነት ምኞታቸው ሕክምና ማጥናት ቢሆንም አባታቸው ግን ሕግ እንዲያጠኑ አሳመኗቸው። በመስከረም 18 88 ለተጨማሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሄዱ፤ ሕግ ሲያጠኑ የኑሮ ስልታቸውን ግን ከእንግሊዛውያን ጋር በፍፁም ለማጣጣም አልሞከሩም።
በ1891 የህግ ባለሙያ ሆነው በመርከብ ተሳፍረው ወደ ቦምቤይ ተመለሱ። በራጃኮትና ቦምቤይ የተማሩትን ሕግ ለመተግበር ጣሩ።
ለተወሰኑ ጊዜያት ለፕሮባንዳራ መስፍን የሕግ ባለሙያ ሆነው አገለገሉ። በ1893 መባቻ ወደ ደቡብ አፍሪካ አምርተው በትራንስቫል ከተማ ለሚገኝ ለአንድ ለሙስሊም ባለሀብቶች ኩባንያ በፕሪቶሪያ የሕግ ወኪል ሆኑ።
በእዚህ ደቡብ አፍሪካም ታላቅ ገድል ፈጽመዋል። በደቡብ አፍሪካ በናታል በአንደኛ ደረጃ ባቡር ሲሳፈሩ አንድ ነጭ ሰው ጋንዲን ከነጮች ጋር መሣፈር አትችልም ብሎ ባቡሩን እንዲለቁ ጠየቃቸው።
ከባቡሩ ወርደው ሌሊቱን በጣቢያው ክስተቱን እያሰላሰሉ አደሩ። ከዚያም በዘር የታጠረ ጭፍን ጥላቻን እስከ መጨረሻው ለመዋጋትና ለመግታት እና በደቡብ አፍሪካም ለአንድ ዓመት ብቻ ለመቆየት ወሰኑ።
ያጋጠማቸው አዲስ ጉዳይ ግን በአገሪቱ እስከ 19 14 እንዲቆዩ አደረጋቸው። በአጭሩ የባቡሩ ክስተት በፕሪቶሪያ የሚገኙ ህንዳውያንን እንዲጠሩና የመጀመሪያ ስብሰባ አድርገው በነጮች የሚደረገው የዘር መድልዎን (የተወሰነ ጎጥን ከሌላው ልዩና ምርጥ ብሎ ማጎብደድና መደናገጥ) ለመዋጋት የመጀመሪያ ስብሰባ አደረጉ።
በዚህም በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ የህንድ ተወላጆች እንደ ጥቁሮች በዘር መድልዎ የሚደርስባቸውን ስቃይ የተሻለ ሕጋዊ ቦታ እንዲያገኙ ዘመቻ ከፈቱ።
ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመመለስ ወደ ህንድ ሄዱ፤ እግረ መንገዳቸውን ለአገራቸው ዜጎች ህንዳውያን የሚደረግባቸውን ደካማ አተያይ አሳወቁ። በዚያ ያደረጉት ንግግር ዜናቸውና ዝናቸው አፍሪካ ደርሶ ስለነበር ሲመለሱ አንድ የተቃዋሚ መንጋ ድንጋዮች በመወርወር ከህግ ውጪ በሆነ እንቅስቃሴ ሊገድላቸው ሞክሮ ነበር።
በ19 07 ጋንዲ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሕንዳውያን ሁሉ እንዲመዘገቡና የጣት አሻራ እንዲወስዱ የወጣውን ህግ አሻፈረኝ እንዲሉ ቀሰቀሱ። በዚህ አንቅስቃሴያቸው ለሁለት ወራት ታስረው ነበረ፤ ኋላም በራሳቸው ፈቃድ ይመዝገቡ በሚል በመስማማታቸው ተለቀቁ።
በእሥር ሆነው ሰላማዊ አለመታዘዝ (“Civil Disobedience,”) የሚለውን የአሜሪካውን ሄንሪ ዳቪድ ዦሩን ወግ አነበቡ። በህንድ በ19 19 በፖለቲካ ወንጀሎች የሚከሰሱ
ሰዎችን ያለ ዳኛ እንዲጠየቁ ጨቋኝ ሕግ ወጣ። ይህም ጋንዲን በመላው አገሪቱ ትልቅ የሥራ ማቆም አድማ እንዲጠሩ አደረጋቸው። 400 ህንዶች ከሞቱበት ከአርሚስትራ እልቂት ቀጥሎም ከእንግሊዝ ፍርድ ቤቶች መደብሮችና ትምህርት ቤቶችም ጋር ህንዳውያን እንዳይሠሩ በማስተባበር ተበቀሉ። የእንግሊዝ መንግሥትም የተከሰተውን አድማ አይቶ ማሻሻያ ለመውሰድ ተስማማ።
ከ19 34 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ስለ ጨርቅ አሠራር ስለ መሠረተ ትምህርት እና ሂንዱን ብሔራዊ ቋንቋ ስለማድረግ ግንዛቤ ይሰጡ ነበር። በነዚህ ዓመታት የህንድ ብሄራዊ ንቅናቄ መሪ እና ህንድ ነጻነቷን ስትቀዳጅም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት ከጀዋህራል ኔህሩ ጋር (1889-1964) በኮንግረስ ኮሚቴ ውስጥ በቅርበት ሠርተዋል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲከሰት እንግሊዝ ህንዶችን ለጦርነቱ አሰለፈቻቸው፤ ይህም ሳትመካከርና ከብሔራዊ መሪዎች የፖለቲካ ስምምነት ሳታደርግና አጥጋቢ ምክንያት ሳታቀርብ ነበር የተፈጸመው። ጋንዲ ጦርነቱን ላለመርዳት ሃሳብ አቀረቡ። በዚህም የኮንግረስ ፓርቲ መሪዎቹ እሳቸውና ኔህሩ ታሠሩ፤ በህንድ ሁከት ተጫረ።
ብሪቲሽ ጋንዲን ለመውቀስ ስትሞክር በእስር ለሦስት ሳምንታት በመጾም ቆዩ፤ በእስር ቤት በወባ ስለተነደፉና ስለታመሙ ተለቀቁ። ከእስር ሲወጡ የህንድ ሙስሊሞች ለብቻቸው ለመሆን እየተንቀሳቀሱ ነበር፤ ፓኪስታንን ከህንድ ለመነጠል የሚደረገው ንቅናቄ አሳዘናቸው፤ በዚህም የህንድ ሙስሊሞች ቀጥተኛ የተግባር ቀን (ኦገስት 16 ቀን 1946) ብለው አውጀው በቀኑና በተከታታይ ዕለታት በ5ሺ ሰዎች ላይ ግድያ ተፈጸመ፤ በካልካታ ብቻ 15ሺ ሰዎች ቆሰሉ፤ የጅምላ ግድያው ለብዙ ቀናት ቆይቶ ሁከቱም በመላ ሀገሪቱ ተሠራጨ።
ይህ ሁኔታ ጋንዲን በከፍተኛ ሁኔታ አሳዝኗቸው ወደ ቤንጋል ሄዱ ።‹‹ ቤንጋልን ለቅቄ የምወጣው፤ የተቀጣጠለው የግርግር ፍም ሲጠፋ ነው›› ብለው ነበር። ነገር ግን ብዙ ሰዎች ተገደሉ ።
የ77 ዓመቱ ጋንዲ በሥፍራው ተሀድሶ ካልተደረገ እስከ ሞት እንደሚጾሙ ገለፁ። ሂንዱዎችና ሙስሊሞች አንድ ላይ የመኖርን ትሩፋት መማር አለባቸው፤ ለመከፋፈል የሚሞክሩ ከሆነ ራሴን አጠፋለሁ አሉ።
የተወሰነ ጊዜ ርጋታ ፀጥታ ቢሰፍንም፣ ሁከቱ አገረሸ። በማርች 1947 የእንግሊዝ ወኪል የነበረው መስፍን ህንድ ደረሰ፤ ዓመቱ እንግሊዝ ከህንድ ለቃ እንድትወጣ በታዘዘው መሠረት ነበር። ኮንግረስ ፓርቲው በወቅቱ በህንድና ፓኪስታን መካከል ያለው መነጣጠል ተቀበለ።
ጋንዲ አገሪቱ በእምነት ሳትነጣጠል ነፃ ወጥታ እንድትቀጥል ያደረጉት ጥረት ተስፋ አስቆረጣቸው፤ ለሰላምና ወንድማማችነት የለፉት ያደረጉት ልፋት መና ስለሆነ በነሐሴ 15 ቀን 1947 ዓ.ም የነፃነታቸው ቀን ሲያከብሩ አልተሳፉም።
በጃንዋሪ 13 ቀን 1948 ዓ.ም ጀምረው ለህንድ አንድነት ይጸልዩ ነበር፤ በወሩ መጨረሻ በፑና ጸሎት እየተከታተሉ ሳለ አንድ የሂንዱ ጽንፈኛ ጋዜጣ አርታዒ በሽጉጥ ተኩሶ ገደላቸው።
ሀይለ ማሪያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 22/2014