ኢትዮጵያ በምትፈተንበት ወቅት እንደምትበራ በዘንድሮው ዓመት በብዙ መልኩ ያየንበት እንደሆነ ከምስክሮቹ አንዱ ዲያስፖራዎች ናቸው። እነርሱ በሰው አገር ሆነው ጥላቻ ሲሰበክላቸው፣ መስማት የማይፈልጉትን ሰምተው ሲጨነቁ ከርመዋል። ይሁን እንጂ የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ማንነት እዚያም ሆኖ ብርሃንን መፈንጠቁን አልተወም።
እንግልቱ ከመቼውም በላይ አጠንክሯቸውም እንዲህ ነን ወደ ማለቱም አስገብቷቸዋል። ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው በያሉበት ቦታ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው አለምን ማስደመማቸው ነው።
ኢትዮጵያን የማያውቃት ሁሉ እንዲመረምራት አስችለዋል። የማትበገርና የማትንበረከክ መሆኗን አስረድተዋል። ይህንን ያህል ሕዝብ እንዳላትና መብቷን ጠያቂ እንደሆነችም አስረግጠው ተናግረዋል። ከሁሉም በላይ፣ እራሳቸው ኢትዮጵያውያንን ጭምር ያስገረሙበት ቅጽበትም ፈጥረዋል። ምክንያቱም በውጪው ዓለም ይህንን ያህል ነዋሪና ተቆርቋሪ እንዳለን ማንኛችንም የተረዳንበት ጊዜ አልነበረም።
በሰላማዊ ሰልፉና በድጋፉ ሆ ብሎ ሲወጣ ነው ኃያል መሆናችንን እየተረዳንና እያረጋገጥን የመጣነው። ብዙዎችም ያወቋት በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ለማንም አይሸሸግም። በዚያ ላይ አገር ጥሪ ስታደርግላቸው የቻሉ በአካል ያልቻሉ ደግሞ በድጋፋቸው መጥተው አለሁልሽ ማለት እንደቻሉም ያየነው ጉዳይ ነው። አውሮፕላን ውስጥ ሳይቀር የተለያዩ መድረኮችን እየፈጠሩ ገንዘብ አሰባስበው ለአገራቸው ደርሰዋል።
ከእነዚህ መካከል አቶ ግርማ ብርሃኑ አንዱ ሲሆኑ፤ የነበሩትን ተግባሮቻቸውንና የኢትዮጵያን ኃያልነት ከሕይወት ተሞክሮዋቸው ጋር በማዋሃድ አንስተው አጫውተውናልና በዛሬ «የሕይወት ገጽታ» አምዳችን አንብቧቸው ስንል አቀረብንላችሁ።
ልጅነት ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል፣ ቱሬ ወረዳ ያየሸንኮሬ ቀበሌ፣ ባንቱ ከተማ ውስጥ ነው። ቤተሰቦቻቸው በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ ሲሆኑ፤ እርሳቸውም በብዙ መልኩ እያገዟቸው ቆይተዋል።
በተለይም በከብት ማገዱና ግብርናው ሥራ የሚታሙ አልነበሩም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን ይፈጽማሉ። ይህም ከብቶችን ማሳረፍ በሚፈለግበት ጊዜ ረፍት ሳይሰጡ ያርሳሉ።
ይህ ደግሞ አባታቸውን በጣም ያበሳጫቸው ነበር። በእርግጥ እርሳቸው ይህንን የሚያደርጉት ቶሎ ጨርሼ አርፋለሁ በሚል ነው። ነገር ግን ካልመሸ በስተቀር ሥራው አያልቅምና የሚቆም ነገር የለም። እናም እርሳቸውም ከብቶቹም ረፍት ሳይወስዱ ለመስራት ሲፈልጉ ብዙ ነገሮች ይበላሻሉ። ከእነዚህ መካከልም ሞፈር መሰበር አንዱ ነው። በዚህ ሥራቸው የተናደዱት አባትም በየጊዜው ይደበድቧቸውና ይቆጧቸው እንደነበር መቼም አይረሱትም።
ለአቶ ግርማ ቤተሰብን በማገዙ ተግባር ላይ እርሻ ማረስን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ምክንያቱም የአንድ ሰዓት ተኩል መንገድ በእግራቸው ሄደው ስለሚማሩ እርሻው ጋር ብዙ ሰዓት አያሳልፉም። በመሆኑም የማንበቢያ ጊዜ ጭምር ይተርፋቸዋል። ብዙ የጨዋታ ጊዜንም ያገኙበታል።
ስለዚህም ደስተኛ ሆነው ውሏቸውን ያሳልፋሉ። ወደውትም ባይሆን የተሻለ እረፍት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። እንግዳችን በባህሪያቸው ያልኩት መሆን አለበት የሚሉ፤ መደባደብን የሚመርጡ፤ ፈጣንና ነገሮችን በቶሎ መጨረስ የሚፈልጉ እንዲሁም ከልጆች ጋር በሆነው ባልሆነው የሚጋጩ ልጅ ናቸው።
ሥራ ሲሰጣቸው በተለይም ከብት ማገድ በጣም የሚናደዱና ፍየሎችን ጭምር የሚሰብሩ አይነት ልጅም እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ሆኖም መንፈሳዊነትን እየተላበሱ ሲመጡና በአባታቸው ምክር ሲቀየሩ ይህ መጥፎ ባህሪ ርግፍ አድርጎ ተዋቸው።
እንደውም መልካሙ እንጂ መጥፎው የማይታያቸው ልጅ ሆኑ። ለተቸገረ መድረስንም የተላመዱት ከዚህ በኋላ ነበር። በእነ አቶ ግርማ ቤት ውስጥ ስምንት ልጆች ያሉ ሲሆን፤ እርሳቸው አምስተኛ ልጅ ናቸው። ያንን ሁሉ ልጅ ሲያስተዳድሩ አባት ደከመኝን አያውቁም።
በተለይም በምክራቸው ልጆቻቸው ቀና አመለካከት እንዲኖራቸው ብዙ ሰርተውባቸዋል። ለዚህም ነው ባለታሪካችን “ለዛሬ ሕይወቴ መሰረቱ እርሱ ነው” የሚሏቸው። ትልቅ ምኞት እንዲኖራቸው አድርገዋቸዋል።
በዚህም በወቅቱ በልጅነት አዕምሯቸው ውስጥ የሚታሰበው ሁለት ነገር ሆኗል። ይህም ፓይለትና ዶክተር መሆን ነበር። ለዚህ የሚበጃቸውን ነገርም ለዓመታት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በእርግጥ አባታቸው በመደበኛው ትምህርት ሳይሆን ከራሳቸው በሚማሩት ነገር ትልቅ ምኞታቸውን እንዲያሳኩ ይፈልጋሉ።
በዚህም ከመማር ይልቅ እርሳቸውን እንዲያገለግሏቸው ብቻ ያደርጋሉ። ትምህርት ቤት እንዲገቡም አይፈልጉም። ይሁን እንጂ የትናንቱ ፈጣን ልጅ የዛሬው ጎልማሳ አቶ ግርማ ግን በሀሳባቸው መቼም ተስማምተው አያውቁም።
ጉዞዋቸው በትምህርት ሲታገዝ ብቻ ህልማቸው እውን እንደሚሆን ያውቃሉና የሚፋለሙበት ጊዜ እስኪደርስ ጠብቀዋቸዋል። በመጨረሻም ተጋፍጠው ህልማቸውን እውን አድርገዋል።
ፈተና ያልበገረው ትምህርት
አቶ ግርማ ትምህርታቸውን የጀመሩት እንደማንኛውም ልጅ ቤተሰብ እጃቸውን ጎትቶ ወስዶ አስመዝግቧቸው አይደለም። በራሳቸው ጥረትና ልፋት ልዩ ፍላጎት ነው። እንዲያውም የሰፈርን ሰው ለምነው ተመዝግበው ሲሆን፤ እርሱ ባያስመዘግባቸው ኖሮ የዛሬን ህልማቸውን እንደማያገኙት ይናገራሉ። ይህም ሆኖ ቤተሰቡ በቀላሉ አልተቀበላቸውም።
የመጀመሪያ ቀን ላይ ትምህርት ቤት ሄደው ሲመጡ አርጩሜ ነው የጠበቃቸው። በአባታቸው ጠንካራ እጅ በሀይለኛው ተደበደቡም። “ዳግም እንዳትሄድ”ም ተባሉ። እርሳቸው ግን መማር ህልማቸው ብቻ ሳይሆን ቆርጠው የተነሱበት ጉዳይ በመሆኑ ሁለት ቀን ፋታ ሰጥተው በሦስተኛው ቀን ጠዋት ተነስተው ለመሄድ ተሰናዱ።
ያን ጊዜ ግን ነገሮች ተደበላለቁ። ነገር ግን በብዙ መንገድ አሳመኑዋቸውና ለደብተር መግዢያ ስሙኒ ተሰጥተው ወደ ትምህርት ቤት ተላኩ። ደስተኛም ሆነው ትምህርቱን ቀጠሉ፤ ጉብዝናቸውም ይበልጥ ጎላ። በተለይ ሥራውን ሳያጓድሉ እየተማሩ በመሆናቸው የአባታቸው ድጋፍ ይበልጥ ጨምሮ ነበርና የደረጃ ተማሪነታቸውን ማንም አልተገዳደረውም።
እስከ ስድስተኛ ክፍልም በዚህ አይነት ሁኔታ በባንቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆዩ። እንግዳችን በተማሪነት ሕይወታቸው ፈረስ መጋለብን አጥብቀው ይወዱ ነበር። ይህ ደግሞ ለጉዳት ዳረጋቸው። በዚህም ከህክምና በኋላ ወደ ገጠር ሳይመለሱ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን በአዲስ አበባ እንዲከታተሉ ሆነዋል። ትምህርት ቤቱ ቀን እየሠሩ ማታ የሚማሩበት ሲሆን፤ ባስሊዮስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባላል።
ሁኔታዎች ሲስተካከሉላቸው ደግሞ ትምህርቱን በቀን መማር ጀመሩ። ይህ የሆነውም የእዚያን ጊዜው ኤስኦኤስ የዛሬው ከፍተኛ 23 ትምህርት ቤት ነው። እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍልም ተከታትለውበታል። ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው የሚያደርሰን ዲፕሎማቸውን የተማሩት ትሮፒካል ኮሌጅ ኦፍ ሜዲስን ላይ ሲሆን፤ በሜዲካል ላብራቶሪ የትምህርት መስክ ተምረው ተመርቀውበታል። ከዚያ በተወሰነ ዓመት ውስጥ ሥራቸውን እየከወኑ ዲግሪያቸውን ለመማር በማታው ክፍለ ጊዜ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመዘገቡ።
የትምህርቱ መስክ ባዮ ሜዲካል ሳይንስን ሲሆን፤ እስከ ሦስተኛ ዓመት መጀመሪያ ድረስ ተከታትለውበታል። ያላጠናቀቁት ደግሞ የተሻለ የትምህርት እድል በማግኘታቸውና ወደ እንግሊዝ አገር በማምራታቸው ነው። እድሉን እንዲያገኙ መንገድ የጠረገላቸው የሚሠሩበት ኢንስቲትዩት ለአጭር ስልጠና መላኩና የተሻለ ልምድ በማግኘታቸው የተነሳ እንደሆነ ያጫወቱን አቶ ግርማ፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኢስት ለንደን እንዲማሩ ሆነዋል። የትምህርት መስኩ ቀደም ሲል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩት የቆዩት እንደነበርም ነግረውናል።
ብዙም ሳይቆዩ በዚያው በእንግሊዝ አገር ቢርክቤኪ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ጀምረዋል። በእርግጥ ይህ እድል እንደ መጀመሪያ ዲግሪያቸው ሙሉ ወጪያቸው የሚሸፈንበት አልነበረም። የትምህርት ወጪው ብቻ ነው የሚሸፈነው። ስለዚህም ለሌሎች ወጪዎቻቸው መሥራት ግዴታቸው ነበር።
አድርገውታልም። እየሠሩ መማርን ቀደም ብለውም የሚያውቁት እንግዳችን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከተማሩ በኋላ ሦስተኛውን ሊቀጥሉበት አልፈለጉም። ምክንያቱም በቂ ነገር አግኝቻለሁ ብለው ያስባሉ። ቦታውን ለልጆቻቸው መልቀቅም ይፈልጋሉ። ስለዚህም ቤተሰብን እያገዙ እርሳቸው የደረሱበት ላይ ማድረስ ግዴታቸው አድርገው ዛሬ ድረስ ቀጥለዋል።
ይሁን እንጂ ይህም ሆኖ የተለያዩ ተጓዳኝ ስልጠናዎችን ከመውሰድ አልተቆጠቡም። በተለያየ ጊዜና ቦታ የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስደዋል።
ብርሃን ፈንጣቂው ጥረት
ከሥራ ጋር የተዋወቁት አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት በ14 ዓመታቸው ነው። አመጣጣቸው ለህክምና ነበር። ይሁን እንጂ የከተማው ስበት ሊለቃቸው አልቻለም። ስለዚህም ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ተውና ወንድማቸው ጋር ቆዩ። በትንሹም ቢሆን ለመዷትም። ግን ብዙ ወንድማቸው ቤት መቆየት ተሳናቸው። ምክንያቱም በቀላሉ ከእርሱ ጋር መስማማት አልቻሉም። እናም በራሳቸው ለመኖር ወሰኑና ይበጀኛል የሚሉትን ሥራ ወደ ማከናወኑ ገቡ።
መጀመሪያ ይህንን ሕይወት አያውቁትምና ፈተናው ከባድ ነበር። በብዙ ተፈትነዋልም። ነገር ግን ‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› እንዲሉ ሆነና ወይዘሮ አይናለም ታሪኩ የተባሉ መልካም ሴትን በሰው አማካኝነት በማግኘታቸው እሳቸውን ተጠጉ።
ሁሉ ነገርም በእርሳቸው አስጠጊነትና እርዳታ ቀለለላቸውም። በተለይ መጠለያና ምግብ ማግኘታቸው ለእርሳቸው ትልቅ እረፍት እንደነበር ያስታውሳሉ። እንግዳችን ምንም እንኳን ይህ እድል ቢሰጣቸውም ቁጭ ብሎ መብላት ባህሪያቸው አይደለምና ለእኝህ መልካም ሴት የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
የሚያደርጉላቸውንም እንክብካቤ ለመመለስ ጠዋት ተነስተው ያገለግሏቸዋል። ብዙ ከብት ስለነበራቸውም አዛባ የሚያወጡት እርሳቸው ነበሩ። ሌሎች የቤት ሥራዎችም ቢሆኑ ይሠራሉ። የተረፈውን ጊዜያቸውን ደግሞ ከቤት ወጥተው በቀን ሥራ ላይ ያሳልፋሉ።
በተለይም ሸክም በቀላሉ የሚያገኙበት አጋጣሚ ስለነበረ በዋናነት ይሠሩታል። ግንባታዎች አካባቢም ቢሆን እየተገኙ በባሬላ የማይሸከሙት ነገር አልነበረም። ይህ በመሆኑ ደግሞ መቸም አይቆጩም። ምክንያቱም ያቀዱት ለመድረስ መልፋት ግድ ነውና ነው።
የሚጣፍጠውም በራስ ጥረት የመጣና በወዝ የተፈጠረ ገቢ ነው ብለው ያምናሉ። አቶ ግርማ ወይዘሮ አይናለምን በችግሬ ቀን ያገኘኋቸውና ለሰው ደራሽነትን የተማርኩባቸው ናቸው። መንፈሰ ጠንካራ፤ ሥራ ወዳድና ትዕግስተኛ አድርገውኛልና ከአምላክና ከአባቴ በታች ጉዞዬን አስተካካይ እርሳቸው ናቸው ይሏቸዋል። ሁለት ዓመታት ከእርሳቸው ቤት ሲቆዩም ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ የሕይወት ትምህርት ማግኛ ደብተራቸው እንደነበሩም ያስረዳሉ። ከዚያም በኋላ ራሳቸውን ችለው ለመውጣታቸው መንስኤው እርሳቸው መሆናቸውን ይናገራሉ።
ምክንያቱም በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ በጥበቃነት እንዲሰሩ ያስመዘገቧቸውና ዋስ የሆኗቸው እርሳቸው ናቸው። እንግዳችን አርማወር ሀንሰን ጥበቃ ሆነው ለሦስት ዓመታት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ የሠሩ ሲሆን፤ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ እድገት አግኝተው የላብራቶሪ ምርምር ረዳት ሆነው እንዲያገለግሉ ሆነዋል።
ዲፕሎማቸውን እንደያዙም አስፈላጊውን ቦታ አግኝተዋል። ይህም የላብራቶሪ ቴክኒሽያንነት የስራ መደብ ሲሆን፤ ረጅም ዓመት ያሳለፉበት ነው። የጤና እንክብካቤ ሥራዎችንም ይሠሩ ነበር። በአጠቃላይ በተቋሙ ከ16 ዓመት በላይ አገልግለዋልም። ቀጣዩ ሥራቸውን እንግሊዝ አገር ያደረጉት ባለታሪካችን፤ ከትምህርቱ ባሻገር ቤተሰቦቻቸውን ስለወሰዱ ብዙ ልፋትን ይጠይቃቸዋልና ሁለተኛ ድግሪያቸውን እየተማሩ ዩሲኤልኤች የሚባል ሆስፒታል ውስጥ በላብራቶሪ ባለሙያነት ለአራት ዓመት አገልግለዋል።
ይሁን እንጂ ኮሮና ሲገባ ሥራውን አቋርጠው የራሳቸውን ሥራ ወደመሥራቱ ገብተዋል። በዚያም አሁን ድረስ እየሠሩ ያሉት የግል ሥራቸውን ነው። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ አገራቸውን መቼም ቢሆን ከአዕምሯቸው አውጥተው አያውቁም። በዚህም ገና ትምህርታቸው እንዳለቀ ነው አገሬ ወደ ማለቱ የገቡት። ይህ ደግሞ ተመላልሰው የተለያዩ ተግባራትን እንዲፈጽሙ አግዟቸዋል።
የመጀመሪያው በትውልድ ቀያቸው ቤት ሰርተው የአካባቢው ማህበረሰብን የባንክ ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው። እንደሚታወቀው አካባቢው ላይ ባንክ ተከፈተ ማለት ተያያዥ ችግሮች መፍትሄ አገኙ ማለት ነው። ይህም የመብራትና የውሃ ጉዳይ በቀላሉ ይፈታል። እናም የእርሳቸው መነሻም ይህ ነበረና ተሳክቶላቸዋል።
አሁንም ቢሆን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቦዝነው አያውቁም። የሚያግዛቸው ከአገኙ መንገዱንም ለማሰራት ዝግጁ ናቸው። በእርግጥ አሁን የመጡት አገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ነው። ይሁን እንጂ የአካባቢያቸው የመሰረተ ልማት ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኝ ይፈልጋሉ።
ስለዚህም በዚህ አጋጣሚ እንተጋገዝ ሲሉ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ። ማንም ሰው ለአካባቢው አደረገ ማለት አገሩን ጠቀመ ነው የሚል አመለካከት ያላቸው እንግዳችን፤ የመጀመሪያው የከተማዋ ገጽታ አብሪ በመሆናቸው ደስተኛ ናቸው።
አሁንም በአገር ደረጃ ይህንን መድገም ይፈልጋሉ። ለአብነት የመጡበትን አላማ እስከመጨረሻው ማሳካት ህልማቸው ነው። አገራቸው ላይ አጠቃላይ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ ላብራቶሪ መገንባት ይፈልጋሉም። ሆኖም ብዙ ቢሮክራሲዎች ነገሮችን እያሰናከሉባቸው ይገኛሉ።
‹‹ቦታ አልጠየኩም፤ የገዛሁት ራሴ ነኝ። በዚያ ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ፎቅ ሰርቼ ለሕዝብና ለአገር የሚጠቅም ተግባር ነው ልከውን ያልኩት። ይሁን እንጂ ማንም ሊሰማኝ አልወደደም።
የሚጠየቀውና የሚመለሰው ነገርም ተስፋ አስቆራጭ ነው። ስለዚህም ለእኔም ለአገሬም የሚበጅ ነገር ማድረግ ተስኖኛል፤ ፍላጎቴም ተደናቅፏል›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ አሁን ወደ አገራቸው በተደረገላቸው ጥሪም የመጡበት ዋነኛ ምክንያት በአገራቸው ላይ ኢንቨስት አድርገው አገራቸውንና ወገናቸውን ማገዝ ቢሆንም ይህ በመንግስት ደረጃ ካልተስተካከለ ግን ሊሳካላቸው እንደማይችል ይናገራሉ። ፍላጎት ብቻውን ውጤት እንደማይሆንም ያስረዳሉ።
ጉዳዩ የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የብዙ ዲያስፖራዎች እንደሆነም ጠቁመው “መንግስት ይይልን” ሲሉ ያሳስባሉ። ማንም ኢትዮጵያዊ ሲጠራና ሲመጣ ምክንያት አለው፤ ለምክንያቱ ደግሞ ምላሽ ይሰጣል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ግርማ፤ ከሚኖሩበት አገር ጀምሮ እያደረጉ ያለውን አስተዋእጾ ያነሳሉ።
ከሁለት ጊዜ በላይ የእራት ምሽት ማድረጋቸውንና ብዙ ገንዘብ እንደሰበሰቡ፣ ሲመጡም በአውሮፕላን ላይ ይህንኑ እንደደገሙት አልፈው የተፈናቀለውንና የተጎዳውን ማህበረሰብ እንዴት ማገዝ እንደሚችሉ ለማወቅ ቦታው ድረስ በህመም ምክንያት ባይሄዱም ያዩትን በመጠየቅ በቀጣይ የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አጫውተውናል።
ይሁን እንጂ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ አልሸሸጉንም። ‹‹መንግስት ትክክል ነኝ ቢልም የሕወሓት አመራርን መልቀቁ ዲያስፖራውንም ሆነ ኢትዮጵያዊያንን ያናደደ ነበር። ብዙዎችንም አስኮርፏል፤ እኔም አንዱ ነበርኩ። ይሁን እንጂ መንግስት ሳያስተውል ያደረጋቸው ነገሮች ሊኖሩ እንደማይችሉ በማሰብና በአገር ማኩረፉ መፍትሄ እንደማይሆን በማመን ትቼዋለሁ።›› የሚሉት እንግዳችን፤
ይህ ነገር ሲኖር አኩርፎ ከመሄድ ይልቅ መጋፈጥ ይገባል። በአገር ላይ ማኩረፍ ጠላትን አይዞህ ማለት ነው። ስለሆነም ስህተት ከተሠራ እየጠየቁ መጓዝ እንጂ የመጣንበትን አላማ መዘንጋት አይገባም ባይ ናቸው። ኢትዮጵያ የሚሸሽባት፣ ከውስጣችን የምናወጣት አገር አይደለችም።
ዛሬ ከችግሯ ልናላቅቃት፤ ቀዳዳዋን ልንደፍንላት የሚገባን ወቅት ላይ ያለች ሆና ሳለ ልንገፋት አይገባም። ምክንያቱም የልባችን ማህተም ናት። እናም ዲያስፖራው አሁን ማድረግ ያለበት መጠየቅ ያለበትን አካል እየጠየቀ መፋለምና ግዴታውን መወጣት ነው። ለዚህ ደግሞ አቅሙም ኃይሉም፣ ልምዱም አለው። ስለሆነም በእኛ አገር እኛ እንጂ ማንም ሊወስንም፤ ሊያድንም አይችልምና “ምን አገባኝ”ን ከውስጣችን አውጥተን ከችግሯ ልንታደጋት ነው የሚገባው።
ካልሆነ ግን የምንከፍለው ብዙ ዋጋ ወደፊት ይበዛልና ማዘናችን አይቀርም ይላሉ። መንግስት ዲያስፖራውን አገርህን ታደግ ብሎ ሲጠራ የሚጠበቅበት ትልቅ ነገር እንዳለ የሚያነሱት ባለታሪካችን፤ ኢትዮጵያዊ ነን የሚሉ ባለስልጣናትን በአሰራር ማስተካከል ይገባዋል። ዲያስፖራን የሚመለከቱበትን እይታ እንዲያስተካክሉ መሥራት አለበት።
ለመዝረፍ ሳይሆን ለመሥራት እንዲጥሩ ማድረግ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። ቢሮክራሲዎችን እያበዙ ተስፋ እንዳያስቆርጡትም ማስተካከል ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ግን ማንም አገሩ ላይ መሥራትን አይሻም፤ ሙዋለ ንዋዩንም አያፈስም። ምክንያቱም በአብዛኛው የሚበላው በጉቦኞች ነው። እናም ታችኛው ክፍል ድረስ ወርዶ መሥራትና ትክክለኛው የአገር ሀብት ትክክለኛ ቦታ ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
ጥሪ ከመደረጉም በፊት በተለያየ ጊዜ አገር ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ይመጡ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ ሁኔታው በሙሰኞች የተበላሸ በመሆኑ ያሰቡትን እውን ማድረግ አልቻሉም።
ከአምስት ዓመት በላይ የፈጀ ፕሮጀክታቸውንም አላሳኩም። ዛሬ ድረስ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ እንዳለ ነው። እናም መንግስት መጥራት ብቻ ሳይሆን አሰራሮችን ማስተካከል ካልቻለ ዲያስፖራው አገሩን ሊያግዝበት የሚችለው ምንም አይነት ሁኔታ አይኖረውም። ሊያስብበት ይገባልም ሲሉ ይናገራሉ። እንግዳችን የዲያስፖራውን ጠቀሜታ በሌሎች አገሮች ላይ በስፋት ማየት እንችላለን። የሠሩትን ገንዘብ ሳይቀር አገራቸው ልከው ሕዝባቸውን ከብዙ ችግር ያወጡ በርካቶች ናቸው።
በእኛ አገርም ቢሆን ይህ እንዲፈጠር እያንዳንዱ የድርሻውን መወጣት አለበት። በተለይም ኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ነገ እንደሚያልፉ አስበው ለአሉበት ቦታ የሚመጥን ሥራ መሥራት አለባቸው። ስማቸውን መትከልም ይገባቸዋል።
ይህ ደግሞ በተለይ በዚህ ወቅት እጅግ አስፈላጊና አንገብጋቢ ነው። በአንድነት የመጣውን ዲያስፖራ ሳያስከፉ ተንከባክቦ ማቆየትና ለአገሩ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የአገራቸውን ውለታ በዚህ እንደሚከፍሉት ማመን አለባቸው ሲሉም ሀሳባቸውን ይገልጻሉ። በውጪ ዜጎች እሳቤ ኢትዮጵያ በልቶ የሚያድር ዜጋ ያለባት አይመስልም።
በተለይ የውጪ ሚዲያዎች ሲያራግቡት የነበረው መረጃ እጅጉን የሚያሰቅቅና ዲያስፖራውን ጭምር ያሸማቀቀ ነበር። የማያውቋትን ኢትዮጵያን እያዩ እንደነበርም ይሰማቸዋል። የውጪ አገራት ጫናም ሲበራከት እየሆነ ያለውን ለማመን ተቸግረው ቆይተዋል። ነው/አይደለም የሚለውን ለማረጋገጥ ደግሞ እድሉ ብዙም አልነበረም።
በዚህም ብዙ ስቃይ አሳልፈዋል። ነገር ግን ሕወሓት በሠራው ተግባር ጥሩ እድልም መጥቷል። የመጀመሪያው ሆ ብሎ በአንድነት መነሳቱና ለሥራ መቆሙ ነው። ለዲያስፖራው መነቃቃትንና ኢትዮጵያን ለማያውቋት ማሳወቅንም ያደለ ነው።
ይህ እድል በበኩሉ ብዙዎች ኢትዮጵያን ለመኖር ጭምር የሚመኟት አገር እንድትሆንም አድርጓል። ምክንያቱም በየአገሩ በተደረገው ተቃውሞና ሰልፍ እንዲሁም የድጋፍ ዝግጅት ሁሉም ኢትዮጵያን እየተደመመ አውቋታል።
ኢትዮጵያዊ ሆነው ክብሯንና ማንነቷን ጭምር ያልተረዱትንም አስተምሯል። “ኑ” ሲባሉም በተለያየ መልኩ መምጣት የቻሉት ይህ እድል በመፈጠሩ ነው። ዲያስፖራው በሁነቱ ማንነቱን አስከብሯል፤ የማን ልጅ እንደሆነም አረጋግጧል። የጥንካሬውና የጀግንነቱ መንስኤ ማን እንደሆነችም አሳይቷል።
በሌላ በኩል በአንድነት ስለ ኢትዮጵያ ዘምሯል። ለድጋፍም ቢሆን ተነስቶ በሚኖርበት ብቻ ሳይሆን በዋለበት ጭምር እንዳይለይ ሆኗል ይላሉ አቶ ግርማ። ይህንን ክስተት በወጉ የመጠቀሙ ሁኔታ ክፍተቶች ያሉበት እንደሆነ የጠቆሙት እንግዳችን፤ ዲያስፖራው በመጣበት ወቅት የሚረብሹ ነገሮችን መስማት መቻላቸው ብዙ እድሎችን መጠቀም እንዳይቻል አድርጓል ይላሉ። በምክንያትነት የሚያነሱት ደግሞ የሕወሓት አመራሮች መለቀቅን ተከትሎ የዲያስፖራዎች ማኩረፍና ወደ መጡበት መመለስ ነው። ከአኩራፊዎቹና ካልተመለሱት አንዱ እርሳቸው እንደነበሩም ያወሳሉ።
ላለመመለሳቸው ምክንያቱ ደግሞ በአገር ማኩረፍ ትክክል አለመሆኑን ማመናቸው ነው። ተግባሩ እንደተባለው አገርን ይጠቅም ይሆናል። ጊዜው ግን ሰዓቱን የጠበቀ እንዳልሆነም እምነት አላቸው።
ሕዝቡም ሆነ ዲያስፖራው በአንድነት መነቃቃትና ለአገሩ መታገል በጀመረበት በዚህ ወቅት ይህ መሆኑ ብዙ ነገሮቻችንን አክሽፏል። ስለዚህም እንደ አገር ሁነቶች ጊዜያቸውን ቢጠብቁ መልካም ነው ሲሉ ይመክራሉ።
የሕይወት ፍልስፍና
ጣት የተፈጠረው ለመሥሪያ እንጂ ለመብያ ብቻ አይደለም። በዚህም አስሩንም ጣት ማሠራትና ሥራ ፈጣሪ ማድረግ ይገባል ብለው ያምናሉ። ይህንን እምነታቸውን ለመተግበርም የሰዓት ገደብ ሳይኖራቸው መሥራት ያስደስታቸዋል። ፍልስፍናቸውም ሥራ የሕይወት መንገድ መቀየሻ ናትና የሰዓት ገደብ ሊበጅላት አይገባም ነው።
በእርግጥ እዚህ ላይ አንድ የማይረሳ ነገር እንዳለ ያነሳሉ። ይህም መብዛት የለበትም እንጂ ማረፍ አስፈላጊ ነው የሚለው ነው። ምክንያቱም ጤነኛ ሆኖ ለመሥራት ማረፍ የግድ ነው።
ሌላው የሕይወት ፍልስፍናቸው “ለአገር የሚሰሰት ምንም ነገር ሊኖር አይገባም” የሚለው ነው። ለአገራችን ሰሰትን ማለት ለቤተሰባችን መሥራትና መኖር አቆምን የሚል እይታ አላቸው።
ከቤተሰብ አፍ ላይ ምግብን መንጠቅም ነው ይሉታል። ስለዚህም ይህንን እምነታቸውን በሕይወት ባሉበት ወቅት እየተገበሩት መኖር ይፈልጋሉ። ሕይወት እንደ ዲክሽነሪ የምንሸመድደውና በፍጥነት የምናልፈው አይደለም። ቆሞ ማየት፣ አገናዝቦ መራመድንና ከየአቅጣጫው የሚመጣውን ፈተና መርምሮ መጋፈጥን ይጠይቃል።
ለዚህ ደግሞ ወደ ራስ መመለስንና መመልከት ያስፈልጋል የሚለውም ሌላው የህይወት ፍልስፍናቸው ነው። ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት ፈጣን ውሳኔዎች የት ላይ እያደረሱን እንደሆነ በማንሳት ነው። ስለዚህም ሕይወትን ስንኖራት በጥበብና በብልሃት መሆን አለበት ይላሉ።
መልእክት
ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለው ሁለት አይነት (ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ) ጦርነት ነው። አካላዊ ጦርነቱ ከሞላ ጎደል ተጠናቋል። አሁን በአፋር አካባቢ ያለው ደግሞ ይመከታል። ሕወሓት ብዙ እንደማይጓዝም በአወጣጡ ታይቷል። ስለዚህም ዋናው ተግባራችን ዲፕሎማሲያዊው ላይ መስራት ይሆናል።
ነገሩ በቀላሉ የሚሠራ ባለመሆኑ ከሚዲያው ጀምሮ ትልቅ ተግባር መከወንን ይጠይቃል። መንግስትም ቢሆን እርምጃውን ሕዝብንና ሀገርን በአስቀደመ መልኩ ማድረግ አለበት። በየጊዜው የሚፈጠረውን ነገር ከተሰጠው አደራ አንጻር እያየ መራመድ አለበት። እድገት የሚመጣው ልዩነትን አክብሮ መኖርና መሥራት ሲቻል ብቻ ነው።
መተውን ካልለመድን መሥራትና መለወጥን በምንም መልኩ ልናስበው አንችልም። እናም ስተቶች ተፈጥረዋል፤ ለእኔ አልተመቸኝም የሚሉ ነገሮች መተው አለባቸው። ብዙኃኑን ያስቀደመና አገርን የሚታደግ ነገር ሲሆን የእኛን ጥቅም አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል።
ይህን ጊዜ አገራችንን ከፍ አድርገን እኛም አብረን ማደግ እንጀምራለን። ስለሆነም መርሃችን መሆን ያለበት ሕዝብና አገር ይቅደም ነውም ብለዋል። መንግስት ለመሆን የሚፈልግ ቡድን ተቋማትን አያፈርስም፣ መሰረተ ልማቶችን አያወድምም። ነገ የሚመራውን ሕዝብም አይገልም። ሕወሓት ግን ይህንን አድርጓል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አገር መምራት ሳይሆን አገር ማውደም አላማው መሆኑ ነው።
ስለዚህም እርሱን በምንም መልኩ መደራደርና በአገር ላይ ኃላፊነት እንዲኖረው ማድረግ አገር ማፍረሱን ቀጥልበት ከማለት አይተናነስምና ትግሉን አጠናክሮ ከምድረ-ገጽ ማጥፋት ያስፈልጋል። የሰጠን እድል እንድንጠነክር በር የከፈተልን መሆኑን አውቀን ያወደመውን ጠግኖና መልሶ ገንብቶ ዳግም አገር ወደ ነበረችበት ሁኔታ እንድትመለስ ማድረግም ይገባል የሚለው ሌላው መልእክታቸው ነው።
ዲያስፖራው ገንዘብ ሲያገኝ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለው የሥራ ባህል ሠርቶ አይደለም። ከዚያ በላይ ፈግቶ፣ ያልለመደውን ሥራ ፈጥሮ ነው። ከ20 ሰዓት በላይም ሊሠራ ይችላል። ላቡን ጠብ አድርጎ ያመጣውን ገንዘብም ለአገሬ ሲል የሚበዘብዘው ብዙ ነው። ስለዚህ ይህ ነገር ሊቀር ይገባል።
በተለይም ከሥራ ጋር ተያይዞ ያልለፉበትን ለመብላት የሚጣጣረው ግለሰብ ራሱን መመርመር አለበት። የመሥራት ባህሉን ከእነርሱ እኩል አድርጎ አገሩንም ራሱንም ለመለወጥ መጣጣር እንጂ ያልለፋበትን ለመዝረፍ መዘጋጀት አይገባውም።
ለዚህ ደግሞ መንግስትም ቢሆን ከወረቀት ያለፈ ሥራ መስራት ይገባዋል፤ ተጠያቂነትን ማስፈን ያስፈልጋል ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ። አቶ ግርማ ለዲያስፖራውም የሚሉት ነገር አላቸው።
ይህም ከአገራችን ስንወጣ በተለያየ ምክንያት ቢሆንም መቼም እንደማንረሳት እናውቃለን። አወጣጣችን ስሟን ጭምር ይዘን ነውና። ስለዚህም ለእርሷ መክፈል ያለብን መስዋዕትነት ብዙ ነው።
ለዚህ ደግሞ መነሻችንን ኢትዮጵያዊነት ማድረግ ይኖርብናል። ለአንድ ብሔር የምንታገለው ነገር የትም አያደርሰንም። ስንወጣ ኢትዮጵያዊ ብለን እንደሆነ ሁሉ ስንመላለስና ስናገለግላትም ኢትዮጵያዊ ሆነን መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ አሁን እያደረግነው ያለነው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው። መጠናከርም አለበት።
አንድነታችንን የሚሸረሽር ምንም አይነት ነገር ቢሆን ልናስገባ አይገባንም። ምክንያቱም ከእኛ ውጪ አንድነት ኃይል እንደሆነ ኖሮት ያየ አገር የለም። ስለሆነም መኖራችንና መሥራታችን፤ እንዲሁም መደጋገፋችን ከማንነታችን ጋር ይተሳሰር የሚለው የማጠቃለያ መልእክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥር 22/2014