የመጽሐፍና ንባብ ጉዳይ በተነሳባቸው መድረኮች ሁሉ የሚሰማ አንድ ተደጋጋሚ ወቀሳ አለ። ይሄውም በከተሞች ውስጥ የመጠጥ ቤትና ሌሎች መዝናኛ ቤቶች በብዛት ሲስፋፉ የቤተ መጽሐፍ አለመኖር ነው። የመጠጥ ቤቶች ብቻ መብዛት ደግሞ ወጣቱን ምን እያደረገው እንደሆነ ሲወቀስ ቆይቷል።
አዲስ አበባ ደግሞ የአገሪቱ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ብሎም የዓለም መዳረሻ ከተማ ናት። በርካታ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቦች ይጎበኙዋታል። ታላላቅ ሁነቶች ይካሄዱባታል። በዚህች ከተማ ውስጥ ለማንበቢያ ብቻ ሳይሆን ለአላፊ አግዳሚውም ለዓይን ማረፊያ እንኳን የሚሆን የሚታይ ነገር ያስፈልጋል።
ውጭ አገር ቆይተው የመጡ ሰዎች ምን እንደሚነግሩን፣ በምን እንደሚቀኑ እየሰማን ነው። በቅርቡ በአዲስ አበባ የተገነባው አብርሆት ቤተ መጽሐፍ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ይህን ቤተ መጽሐፍ ባጎበኘሁባቸው ሁለት ጊዜያት የተለያዩ ጉዳዮችን አስተውያለሁ።
የመጀመሪያው ያስተዋልኩት ገና እንደ ተመረቀ ነበር። ሁለተኛው ግን ከትናንት በስቲያ ነው። የሁለቱ ጊዜያት ልዩነት ገርሞኛል፤ ይህን መጣጥፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝም ይህ ልዩነት ነው። የመጀመሪያው (የተመረቀ ሰሞን ማለት ነው) ያስተዋልኩት ነገር አብዛኛው ሰው የሄደው ለማንበብ ሳይሆን ለማየት ነበር።
ውጪውም ውስጡም እጅግ ማራኪ ነው። ወደ ውስጥ ሲገባ ቆመው እያዩ የሚደመሙ፣ ፎቶ የሚነሱ ይበዛሉ። የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ የለበሱ ተማሪዎች ብቻ የማንበቢያ ጠረጴዛዎች ላይ ሆነው በቡድን በቡድን ያነባሉ። ወደ መጻሕፍት መደርደሪያው ስሄድ የሚበዙት የመማሪያ መጻሕፍት ናቸው።
የመማሪያ መጽሐፎቹ በተለያየ የትምህርት ደረጃ ያሉ እና ለተለያዩ ሙያዎች (ምጣኔ ሀብት፣ ህክምና…) የሚሆኑ ናቸው። ጥቂት የታሪክ መጽሐፎችንም አይቻለሁ። ጉብኝቴን ጨርሼ ስወጣ መግቢያው ላይ ያሉትን የመረጃ ክፍል ሰራተኞች ስለመጻሕፍቱ፣ ስለአነባበብ
ህጉ ስጠይቅ፤ ለጊዜው እንዲህ አይነት ህግ እንዳልወጣ፣ አብዛኛው ሰው ገና እየጎበኘ ስለሆነ እንዲለመድውና እንዲታይ እንጂ ገና መደበኛው ሥራ እንዳልተጀመረ ነገሩኝ። በሁለተኛው ምልከታዬ ያየሁት ግን እንደ መጀመሪያው አይደለም። የሚገቡ ሰዎች ሁሉ በጥድፊያ የሚገቡ ናቸው። ቶሎ ተፈትሸው ወደ ማንበቢያ ሥፍራው ይሄዳሉ። ፎቶ የሚነሳና ቆሞ የሚጎበኝ ብዙም የለም (እኔ በቆየሁባቸው ደቂቃዎች ማለቴ ነው)። የማንበቢያ ሥፍራዎችም በብዙ ሰዎች ተይዘዋል። የቡድን ውይይት የሚደረግባቸው ክፍሎችም ተይዘዋል።
የደንብ ልብስ የለበሱ ተማሪዎችም ይታያሉ። ከግቢው ጀምሮ ቤተ መጸሀፉ ፀጥ ያለ ነው። መጀመሪያ አካባቢ የነበረው የሰዎች ንግግርና ጫጫታ የለም። በአጠቃላይ አብርሆት ቤተ መጽሐፍ የመጽሐፍ አወሳሰድና አጠቃላይ የአጠቃቀም ህግና ደንቡ ገና ቢሆንም ቦታው ግን እየተነበበበት ነው። አሁን ለማንበብ እንጂ ለማየት የሚሄድ የለም፤ የዕለቱ ሥራ ፈት ምናልባትም እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም ነበር። ሳላስነቃ ሹልክ ብየ ወጣሁ።
በእርግጥ የሁሉም ትኩረት ንባቡ ላይ ስለነበር ሥራ ፈቶ እኔን የሚያይ አልነበረም፤ በዚያ ላይ ከወዲያ ወዲህ የሚሉ ብዙ ሰዎችም ነበሩ። የተመረቀ ሰሞን በማህበራዊ ገጾችም ሆነ በየካፌው ብዙ ተብሏል። ሰው በወረት ለማየት ነው እንጂ የሚሄድ አይኖርም፤ በቅርቡ ባዶውን ይውላል ሲባል ሰምቻለሁ። አንባቢ ነው እንጂ የጠፋ ማንበቢያ ቦታ ነው ወይ ተብሎም ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ስንት ችግር ባለባት አገር እንዴት እንዲህ አይነት የቅንጦት ሥራ ይሰራል ተብሏል። በወቅቱ ሁሉንም ወቀሳዎች ልብ ብለን ካየናቸው አሳማኝ አይደሉም። በመጀመሪያ ቤተ መጽሐፍ የቅንጦት አይደለም፤ መሰረታዊ ፍላጎት ሆኗል። ከመሰራቱ በፊት የነበረው ወቀሳ የቤተ መጽሐፍ አለመኖር ነበር።
መንግሥት አንባቢ ትውልድ እየፈጠረ አይደለም በሚል። ያም ሆነ ይህ ቤተ መጽሐፍ በፍፁም የቅንጦት አይደለም፤ ችግሮች የሚፈቱት አንድም በንባብ ነውና። አንባቢ ጠፋ እንጂ ቦታው አልቸገረም የሚለውም ምናልባትም ሳያውቁ የተደረገ ወቀሳ ነው። እስኪ አዲስ አበባ ውስጥ ሰው ነፃ ሆኖ የሚያነብበት ቦታ ነበር ወይ? ስንቶች ናቸው በቂ መጽሐፍ ያላቸው? ተማሪዎች ማጣቀሻ መጽሐፍ እንደፈለጉ ያገኙ ነበር ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ካነሳን ምንም ሰፊ ማብራሪያ ሳያስፈልገው ቤተ መጽሐፉ የግድ ነበር። ገና ብዙ ቤተመጻህፍት ያስፈልጉናል። ክፍለ ከተሞች፣ የክልል ዋና ከተሞችና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ይህን አርአያነት ያለው ተግባር ፈጥነው ሊኮርጁ ይገባል።
ቤተ መጻህፍት ለመገንባት ሲታሰብም ሰፋ አርጎ ማሰብ ያስፈልጋል። ትውልድ የሚቀረጽበት፣ የችግር መላ የሚቀዳበት ስፍራ ነው፤ የምናስቀምጠው ቅርስ መሆኑም ሊታሰብ ይገባል። አንባቢ አለ ወይ? የሚለውም ይሄው እየታየ ነው። በነገራችን ላይ የዚህ ቤተ መጽሐፍ መሰራት አስፈላጊነት የሚደነቀውና የሚመሰገነው በየዕለቱ በሚታየው የአንባቢ ብዛት መሆን የለበትም፤ እንዲያውም የመሰራቱ ዋና ዓላማ እኮ አንባቢ ትውልድ መፍጠር እንጂ የንባብ ልምድ ላዳበረው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ አይደለም። የንባብ ልምዳቸውን ያዳበሩ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚ አዳብረዋል።
ዳሩ ግን ከመጽሐፍ ጀምሮ እስከ ማንበቢያ ቦታ ተቸግረው የንባብ ልምዳቸው ላልዳበረ የህብረተሰብ ክፍሎች ግን ይህ ምቹ አጋጣሚ ነው፤ ቢያንስ ለማየት ሲሉ በዚያው ወደ ንባብ ይሳባሉ። አብርሆት ቤተ መጽሐፍ ለማንበብ ብቻ ሳይሆን ለመጻፍም የሚያነሳሳ ማራኪ ግቢ ነው። ቤተ መጻህፍቱ ብቻ ሳይሆን አካባቢው የተዋበት መንገድ የሆነ ውስጣዊ መነቃቃትና የመንፈስ ደስታ ይፈጥራል።
ፀሐፊዎች ደግሞ በየዕለቱ ከሚያዩት ነገር ለየት ያለ ሲያዩ ነው ሀሳብ የሚመጣላቸው። ይህን ለፀሐፊዎች እንተወውና ለአንባቢዎች ግን ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ነው። ከበይነ መረብ ግብዓቶች ጀምሮ እስከ የወረቀት መጻሕፍት ድረስ የመረጡትን ያነባሉ። ይህ ቤተ መጽሐፍ ለከተማዋም ትልቅ ውበትና ገጽታ ያላበሰ ነው። የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነች ከተማ እንዲህ አይነት የሚታዩ ቤተ መጻሕፍት ሊኖሯት ይገባል። የአገር ገጽታ አንድም የሚገነባው በእንዲህ አይነት መንገድ ነው፤ የመጣ የሄደው ሁሉ ስለቅርሶቻችንና ምቹ የአየር ንብረታችን ብቻ እየመዘገበ ሊሄድ አይገባም! ለመማር ለማወቅ ያለንን ዝግጁነትም መረዳት ይኖርበታል።
አዎ! ብዙ ችግሮች አሉ፤ ብዙ ድህነት ያለበት አካባቢ አለ። ዳሩ ግን እነዚያ ድህነት ያለባቸው አካባቢዎች ብቻ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲታዩ ማድረግ በድህነት ላይ ድህነት መደራረብ ነው። በጎ ገጽታዎቻቸውን የምናወድስላቸው አገራት ምንም ችግር የለባቸውም ማለት አይደለም። ዓለም አቀፍ ዝና ምን ያህል ተፅዕኖ እንዳለው በዚህ ዓመት በሚገባ አይተናል።
በጎ ገጽታን ማስተዋወቅ ቱሪስት እና ኢንቨስተር ይስባል። ይህ ደግሞ ራሱን የቻለ ገቢ ነው። ስለዚህ ከድህነት የመውጫ አንዱ መንገድ በጎ ነገሮችን ማስተዋወቅና ተጠቃሚ ልንሆንባቸው ይገባል፤ ይህ ሲሆን የተገነቡና የሚገነቡ የመናፈሻ ፓርኮችንና እንደ አብርሆት ያሉ ማራኪ ቦታዎቻችን ዳቦ ናቸው ማለት ነው።
አሁን ከሁላችንም የሚጠበቀው ወደ ቤተመጻህፍቱ ሄዶ ማንበብ ነው። የምናነሳቸው ወቀሳዎች ሁሉ የሚቀረፉት አንባቢ ትውልድ ሲፈጠር ነው፤ ችግሮቻችን የሚቀረፉት አንባቢ ማህበረሰብ ሲፈጠር ነው። ከድንጋይ ውርውራ ወደ ሀሳባዊ መግባባት የምናድገው በንባብ ነው። የሰለጠኑ አገራት አምላኪ መሆናችንን የምናቆመውም በንባብ የዳበረና የሰለጠነ ማህበረሰብ ሲፈጠር ነውና እናንብብ!::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 21/2014