የአልጀዚራ ዘገባ እንደሚያሳየው እ.አ.አ የካቲት 14 ቀን 2019 በፓኪስታን ፓሉዋማ ግዛት ውስጥ ጃኢሽ ኢ መሀመድ ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ባደረሰው ጥቃት 40 የህንድ ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በህንድና በፓኪስታን መካከል የነበረውን ቁርሾ አባብሶታል፡፡
እ.አ.አ የካቲት 26 ቀን 2019 ደግሞ የህንድ የጦር ኃይል በፓክህቱንካዋ አቅራቢያ የአየር ጥቃት ያደረሰ ሲሆን፣ የጥቃቱ ዓላማ በፓኪስታን የሚገኘውን የሽብርተኞች ማሰልጠኛ ጣቢያ ማጥፋት ነበር፡፡ ፓኪስታን በተራዋ በክልሏ የተደረገውን ጥቃት ለመመለስ በሁለቱ አገራት መካከል በሚገኘው ካሽሚር ግዛት ውስጥ በሚገኘው የህንድ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የጦርነት እንቅስቃሴ አዲስ አይደለም፡፡
ነገር ግን የአሁኑ የእርስ በርስ ጥቃት እ.አ.አ በ1971 ከተካሄደው የሁለቱ አገራት ጦርነት የሚለየው ሁለቱም አገራት ሽብርተኝነትን ለማጥፋት በሚል ሰበብ ጥቃት መሰነዛዘራቸው ነው፡፡ ቀደም ብሎ በካርጂል ጦርነት ወቅት የህንድ የጦር ጀት ፓኪስታን ላይ ጥቃት ለማድረስ ተልኮ ነበር፡፡ በወቅቱ ፓኪስታን በካሽሚር በሚገኝ የህንድ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት አድርሳለች፡፡
ድንበር ዘለል ጥቃት የሚካሄደው በአብዛኛው በካሽሚር ግዛት ውስጥ ሲሆን እ.አ.አ 2016 ላይ ፓኪስታን የተሰነዘረባትን ጥቃት ለመመለስ በህንድ አስተዳደር ስር በሚገኘው የካሽሚር ግዛት ውስጥ የሚገኘው የኡሪ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ማድረሷ ይታወሳል፡፡ ህንድ ተደጋጋሚ ጥቃት ለማድረስ ፍላጎት ቢኖራትም በአገር አቀፍ ደረጃ ይካሄድ የነበረው ምርጫ እንድትታቀብ አድርጓታል፡፡
ፓኪስታንም ችግር ከመፍጠር ይልቅ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከተለመዱ ወደፊት የሚኖራቸውን ተፅዕኖ ለማስወገድ ፍላጎት ነበራት፡፡ የጉዳዩ የመጀመሪያው ጎን ጠንካራ የጦር ኃይል የመገንባት ፍላጎት እና ጦርነትን የማስወገድ ፍላጎት አለ፡፡ ከካርጊ ጦርነት ጀምሮ በሁለቱ አገራት መካከል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት 20 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ በህንድ ሊካሄድ የነበረው ምርጫ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ተሰግቶ ነበር፡ ፡ ምክንያቱም የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሁለተኛ ጊዜ ለመወዳደር ፍላጎት ነበራቸው፡፡
የህንድ መንግሥት የደህንነት ሁኔታው ጥብቅ ትኩረት እንዲሰጠው መጠየቅ የጀመረው እ.አ.አ 2019የካቲት 14 በፑልዋማ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ነው፡፡ በደህንነት ጥበቃው ዙሪያ ፈጣን ምላሽ አለመገኘቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩና እሳቸው የሚመሩት ፓርቲ ስጋት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ሁኔታ ለተቃዋሚዎቻቸው ደስታን የፈጠረ ሲሆን አገሪቱን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ደካማ አቋም እንዳለው አሳይቷል፡፡ የፑልዋማ ጥቃት በፖለቲካዊ ተንታኞች እይታ ሲታይ ህንድን በማስተዳደር ላይ ለሚገኘው ፓርቲ ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ ምክንያቱም ከፓኪስታን ጋር የተጀመረውን ግጭት በማስቀጠል በምርጫው ድምፅ ለማግኘት ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሀን እስካሁን ህንድ ያደረሰችው ጥቃት ፖለቲካዊ መልክ ይኑረው አይኑረው የተናገሩት ነገር የለም፡ ፡ ነገር ግን የፓኪስታን ወታደሮች ፈጣን ምላሽ አለመሰጠቱ የስነልቦና ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ነበር ፓኪስታን በካሽሚር የሚገኘውን የህንድ የጦር ሰፈር ለመደብደብ ውሳኔ ላይ የደረሰችው፡፡ የአየር ጥቃቱን ፓኪስታን ከሰነዘረች በኋላ ህንድም ምላሽ በመስጠቷ በካሽሚር ሁለቱ የሚዋሰኑበት ቦታ ላይ የአየር ላይ ጦርነት አድርገዋል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው የአየር ጥቃት ደረጃው ቢለካ ለመገመት እንደሚያዳግት የወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ በሁለቱም አገሮች የሚሰጠው መግለጫ የጦር አውሮፕላኖችን መትተው መጣላቸውን ነው፡፡ ነገር ግን በሁለቱ አገራት የተሰጠው መግለጫ የተቃረነ መሆኑ የሚያሳየው ምን ያክል የጦር አውሮፕላኖች ተመትተው መውደቃቸው አለመታወቁን ነው፡ ፡
ምክንያቱም የጦር አውሮፕላን አብራሪዎቹ መያዝ አለመያዛቸው፣ምን ያክል ጉዳት እንደደረሰ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች አልተጠቀሱም ነበር፡፡ ሆኖም ፓኪስታን አንድ የህንድ አብራሪ መያዟን ባለፈው ሳምንት ገልጻለች፡፡ የተያዙ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች በምን ዓይነት መንገድ እንደተያዙ እንዲሁም ወደ አገራቸው መመለሳቸው በተጨማሪም በህንድ በኩል አሁንም ከባድ የአየር ጥቃት እየተሰነዘረ እንደሚገኝ መረጃዎች አሉ፡፡ የህንድ የአየር ጥቃት ማድረስ ተከትሎ ፓኪስታን በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦሯን በማዘጋጀቷ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት ጨምሯል፡፡
በህንድና በፓኪስታን መካከል እየጨመረ የመጣው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት በድንበራቸው አካባቢ ከባድ ውጥረት ፈጥሯል፡፡ ይህ እየተባባሰ የመጣው ውጥረት እስከመቼ እንደሚቀጥል አልታወቀም፡፡ ህንድ በድጋሚ ለአየር ጥቃት የምትዘጋጅ ከሆነ ሁለቱ አገራት ከባድ የሆነ ጦርነት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ነገር ግን ፓኪስታን ከምታደርገው ጥቃት ልትታቀብ ትችላለች የሚል ግምት አለ፡፡ ፓኪስታን የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመመለስ የምትወስደውን እርምጃ የመቀነስ አማራጭ አላት፡፡
ነገር ግን በአገሯ ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ነፃ መንገድ በመስጠት ህንድ ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ልታደርግ ትችላለች፡፡ ይህ ሁኔታ ቀደም ብሎም ተከስቶ ነበር፡፡ እ.አ.አ 2016 በህንድ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት የደረሰ ሲሆን ጥቃቱ በካሽሚር የህንድ የጦር ሰፈር በፓኪስታን ታጣቂ ቡድኖች የተደረገ ነበር፡፡ ይህ አማራጭ እንግዲህ ለፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሁን ለጦር ኃይሉ ከባድ አይሆንም፡፡ ወደ ጦርነት የመግባት አዝማሚያ የህንድም ይሁን የፓኪስታን መሪዎች ፍላጎት ያለ ይመስላል፡፡ እየተባባሰ የመጣውን ግጭት የማስቆም ኃይል ቢኖራቸው ህዝቦቻቸው ፊት የውሸት ፈገግታ እያሳዩ ችግሩን ማባባሳቸውን ቀጥለዋል፡፡
የህንድ ወታደሮችን ጨምሮ በትንሹ 5 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት ወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ መካሄዱም ታውቋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 የተካሄደውን የተኩስ ማቆም ስምምነትን ተከትሎ ጃሙና ካሽሚር በተባለ ስፍራ ላይ እንዲወሰኑ የተደረገውን ወታደራዊ የድንበር መስመር የተቀበሉ ቢሆንም በቀደሙት ዓመታት ህንድ ፓኪስታንን ስትወነጅል ቆይታለች። ሆኖም ከ15 ዓመታት ወዲህ የአሁኑ ከፍተኛና የሁለቱን ሀገራት ወታደሮች ለተኩስ ልውውጥ የጋበዘ እንደሆነም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው። በደረሰው ጥቃት የ52 ዓመት ሴትን ጨምሮ የሁለት ሲቪሎች እንዲሁም አንድ ህንዳዊ የድንበር ጠባቂ ወታደር መገደል የቀሰቀሰው ውጥረት የሁለቱን ሀገራት ወታደሮች ለተኩስ ልውውጥ የጋበዘ ሆኗል። ንፁሀን ዜጎችና የድንበር ጠባቂው የተገደሉት ከፓኪስታን ወገን በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ እንደሆነም ታውቋል።
ከደረሰው ጥቃት ቀደም ብሎ አንዲት የ17 ዓመት ወጣት እንደተገደለች የገለጹት የህንድ የአካባቢው ባለስልጣናት 24 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አምስት ያህል ሰዎች መገደላቸውንና ከ20 በላይ መቁሰላቸውን አስታውቀዋል። ፓኪስታን ስምምነቱን በመጣስ ወታደሮቿ በህንድ ይዞታ ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ አድርጋለች በማለት ህንድ በተደጋጋሚ ክስ ስታቀርብ መቆየቷም ታውቋል። ከፓኪስታን ወገንም የከባድ መሳሪያ ተኩስ በህንድ ግዛት ውስጥ እንደተፈጸመም አንድ ባለስልጣንን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል።
ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ እየጠነከረ የመጣውና አሁን የተባባሰው ሁኔታ በቀደሙትም ተከታታይ ዓመታት መጠነኛ ግጭቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። ፓኪስታን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1947 ከሕንድ ተገንጥላ የራሷን ነጻነት ካገኘች ወዲህ በካሽሚር ግዛት ሳቢያ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ሁለት ጊዜ ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዷል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1989 ለካሽሚር ነጻነት የሚታገሉ አማጽያን ከህንድ ጋር ባደረጉት ውጊያ ከ70 ሺ በላይ ሰዎች አልቀዋል። በአካባቢው በአሁኑ ወቅት ግማሽ ሚሊዮን የህንድ ወታደሮች መስፈራቸውም ይታወቃል። በካሽሚር ሳቢያ የሚወዛገቡት ህንድና ፓኪስታን ሁለቱም የኒዩክሌር መሳሪያ የታጠቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011
በመርድ ክፍሉ