ኢትዮጵያ ያደረገችውን ጥሪ ተቀብሎ ወደ አገሩ የገባውን ዲያስፖራ ቤት ለእንግዳ በማለት ተቀብሎ ለማስተናገድ ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች ተደርገዋል።
ወደ አገር ቤት የሚገባው ዲያስፖራ እግሩ የኢትዮጵያን አፈር ሲረግጥ ካለው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችል በመንግሥት በኩል በርካታ ምቹ ሁኔታዎች ተደርገዋል።
ከተደረጉት ዝግጅቶች መካከልም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ከማስተላለፍ ባለፈ ዲያስፖራው የአገር ቤት ቆይታው ያማረና የሰመረ እንዲሆን በማድረግ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ መረዳት የሚያስችላቸው የተለያዩ ሁነቶችም ተዘጋጅተዋል።
ዲያስፖራው ወደ እናት አገሩ እቅፍ ሲገባ የንግዱን ማህበረሰብ ጨምሮ አጠቃላይ ማህበረሰቡ ሃሪቡ ብሎ እንዲቀበለውና እንዲያስተናግደው ተደርጓል። በተለይም በአገር ቤት በሚኖረው ቆይታ ተቀዛቅዞ የሰነባበተውን የንግድ እንቅስቃሴ ትርጉም ባለው መንገድ እንደሚያነቃቃው ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል። በቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት እንደሚፈጥርም ታምኖበት ነበር።
በመሆኑም በአሁን ወቅት ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለይም የተለያዩ ኃይማኖታዊ በዓላት በሚከበሩበት በዚህ ወቅት ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት መግባቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ የጎላ እንደሚሆን ይገመታል።
የተለያዩ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ እናት አገር ኢትዮጵያ ያደረገችውን ጥሪ ተቀብለው የመጡ ዲያስፖራዎች መገኛቸውም ሆነ ሥሪታቸው በእናት አገራቸው ብቻ የሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በተለያዩ ገበያዎች ላይ ቀርበውላቸዋል።
ቁሳቁሶቹም ሊያጌጡበት፣ ሊዋቡበት፣ ወደ ውጭው ዓለም በሚመለሱበት ጊዜም እናት አገራቸውን ሊያስታውሱበት እንዲሁም ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዲህ ናት በማለት ኢትዮጵያን ለሌሎች ሊያስተዋውቁበት የሚያስችላቸው በርካታ ባሕላዊ ቁሳቁሶች በተለያዩ የገበያ ቦታዎችና ባዛሮች ላይ ተዘጋጅተዋል፡፡
ታድያ በእነዚህ ገበያዎች እንደምን ያሉ ቁሳቁሶች ቀርበው ይሆን? ዲያስፖራው ወደ አገር ውስጥ ከመግባቱ ጋር ተያይዞስ ምን የተለየ ዝግጅት ተደርጎ ነበር? ዲያስፖራው በባህላዊ አልባሳት ጌጣጌጦችና ቁሳቁሶች ግብይት ተሳትፎው እንዴት ነው? ስንል ላነሳነው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ቀደም ሲልም ቱሪስቶች በብዛት በሚገበያዩበት በተለምዶ ጥቁር አንበሳ አልያም ፖስታ ቤት አካባቢ በሚገኘው የባህል አልባሳትና የተለያዩ ቁሳቁሶችና ጌጣጌጦች መሸጫ በሆነው የገበያ ቦታ ቅኝት አድርገናል።
ሥፍራው ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ግብዓቶች ኢትዮጵያዊ ይዘት ባላቸው በርካታ ቁሳቁሶችና ጌጣጌጦች ተሞልቷል። አይነ ግቡ የሆኑና በሰው እጅ ተሰሩ ብሎ ለማመን የሚከብዱ የተለያዩ የአገር ባህል አልባሳት፣ ከእንጨት የተሰሩ የእንስሳት ቅርጻ ቅርጾች፣ የሸክላ ውጤቶች፣ የስፌት ሥራዎችና የተለያዩ ኢትዮጵያዊ እሴት ያላቸው ስዕሎች በእያንዳንዱ ሱቅ በአይነት በአይነቱ ተሰድረው ሲታዩ እጅን ወደኪስ ያሰኛሉ።
ዞር ዞር ብሎ አካባቢውን ለመቃኘት የወጣን መንገደኛ በልዩ ውበታቸው ያሳስታሉ፡፡ለስፍራውም ልዩ ውበት ሆነዋል። በሱቅ ውስጥ በአይነት በአይነት ተሰድረው ከሚሸጡት ቁሳቁሶች በተጨማሪ በአካባቢው እየተዘዋወሩ ለመሸጥ የሚጣጣሩም ‹‹ሱቅ በደረቴዎች›› አሉ።
ከገበያ ስፍራው ውጪ ውር ውር የሚሉቱ በአብዛኛው የስፌት ሥራዎችን የያዙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የተለያየ መጠን ያላቸው ሙዳይና መሶቦች ይገኙበታል። እጅግ ተመሳሳይና ተቀራራቢ ከሆኑት የባህል አልባሳትና የጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆች መካከል ወደ አንደኛው ጠጋ በማለት አሁን ያለው የገበያ እንቅስቃሴ እንደምን ያለ ነው በማለት ያነጋገርናት ወጣት ሰርካለም ብርሃኔ፤ ሁለት ዓመታትን ሊያስቆጥር ጥቂት የቀረው ኮቪድ 19 የዓለም ስጋት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ መሆኑን አስታውሳለች። ይሁንና በአሁን ወቅት አገሪቷ ካለችበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ ጥሪ የተደረገለት ዲያስፖራ ወደ አገር ቤት በመግባታቸው ገበያው እንዲነቃቃ አድርጎታል።
ጥሪው የኢትዮጵያ ወዳጆችንም ያካተተ በመሆኑ ኤርትራውያንም በከተማዋ በብዛት በመኖራቸው ካለፉት ጊዜያት አሁን ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ኮቪድ 19 በዓለም በተለይም በአገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ገበያው በእጅጉ የተቀዛቀዘ በመሆኑ ምንም አይነት ሥራ አልነበረም። ዲያስፖራውም ወደ አገር ቤት ሲገባ የተለየ ዝግጅት ማድረግ አልቻልንም።
ለዚህም ምክንያቱ ሁለት ዓመት ያህል ሥራ መሥራት ባለመቻሉ ያሉትን ዕቃዎች ይዘው ለመቅረብና እነሱኑ ለማጣራት መገደዳቸውን ያነሳችው ወጣት ሰርካለም፤ በዋጋም ቢሆን የተለየ ጭማሪ አለመደረጉንና በነበረው ዋጋ ለሽያጭ መቅረቡን ታስረዳለች። ይሄም ተቀዛቅዞ የነበረውን ገበያ ለመመለስና እንግዶችን ባልተጋነነ ዋጋ ለመቀበል መሆኑን አንስታለች፡፡
በአሁኑ ወቅት አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባላቸው አልባሳትና ቁሳቁሶች ላይ ትኩረት እየተደረገ በመሆኑ የኢትዮጵያ ባንዲራን የሚወክሉ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን የያዙ የተለያዩ አልባሳትን በተወሰነ መጠን አስገብተው ዲያስፖራውን እየጠበቁ መሆኑን በማንሳት ነገር ግን ገበያው የጠበቀችውን ያህል እንዳልሆነላት ትናገራለች።
ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ጥሪ ከተደረገላቸው ዲያስፖራዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ገበያው የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም በኮቪድ 19 የተጀመረው የገበያ መቀዛቀዝ በጦርነቱም ይበልጥ ተዳክሞ የሰነባበተ ቢሆንም አሁን ግን መጠነኛ መሻሻል እየታየበት ነው ብላለች፡፡ ካለፉት ጊዜያት በተሻለ በአሁን ወቅት በአገር ቤት ያሉ ሰዎችም እንደ ዲያስፖራው ሁሉ ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁሶችን መጠቀም ልምድ እየሆነ ነው።
ይህን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። ከዲያስፖራው በተጨማሪ የአገር ውስጥ ሸማቾችን ማበረታታት ያስፈልጋል። ይህም ሲባል ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ሁሉም ሰው ወደ ባህሉ እንዲመለስ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
አሁን የአንገት ልብስ ከ200 እስከ 400 ብር፣ ቅርጻቅርጾች፣ የስፌት እና የሸክላ ሥራዎችም እንደየመጠናቸውና ሥራቸው በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥ መሆኑንም ገልጻለች፡፡
ዲያስፖራው ጥሪውን ተቀብሎ ወደ አገሩ በመምጣቱ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት አቶ በጃዱ ናደሞ በአካባቢው ከሚገኙ የባህል አልባሳትና ቁሳቁሶች መሸጫ ሱቆች መካከል የአንደኛው ባለቤት ናቸው።
አቶ በጃዱ ዲያስፖራው ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ሲገልጹ፤ ከዚህ ቀደም የባህል አልባሳትም ሆነ የተለያዩ ባህላዊ ቁሳቁሶች የሚገኙት በዚሁ ፖስታ ቤት አልያም ጥቁር አንበሳ አካባቢ፣ ሽሮሜዳና መርካቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው ነገር ግን በአሁን ወቅት በየመንገዱ የባህል ዕቃዎች እየተሸጡ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ።ይህም ንግድ ፈቃድ አውጥተው ግብር እየከፈሉ የሚሰሩትን እያዳከመ ነው ይላሉ።
ወትሮም በበዓላት ወቅት የተሻለ እንቅስቃሴ አለው ተብሎ የሚታመነው የባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁሶች ገበያ በተለይም በአሁን ወቅት ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት ከመግባቱ ጋር ተደማምሮ እንዴት ነው በማለት ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ በጃዱ ሲመልሱ፤ ገበያው በተጠበቀው ልክ አለመሆኑን እንዲሁም ዲያስፖራው መገበያየት እንዲችል በተለያዩ ፓርኮች፣ አደባባዮችና ባዛሮች ላይ ገበያ መፈጠሩ የአካባቢውን ገበያ አቀዛቅዞታል። በተለይም በበዓላት ወቅት በአካባቢው ድንኳኖች ዘርግተው የሚሸጡ አሉ ።
እነሱም ከፍተኛ ተጽዕኖ አድርገዋል። ስለዚህ መንግሥት መሰል ችግሮችን በመረዳት ፈቃድ አውጥተው ህጋዊ በሆነ መንገድ ለሚሰሩት ትኩረት ቢሰጥና መልካም ነው በማለት ሀሳባቸውን ሲቋጩ ‹ዲያስፖራው ወደ እኛ የገበያ ማዕከል በተጠበቀው መጠን ባይመጣም በአገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ በመቻሉ ደስተኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዲያስፖራው ጉዞ ወደ አገር ቤት እንዲያቀና ግብዣ የተደረገበት ይህ ወቅት እጅግ አዋጭና ተመራጭ መሆኑን በመግለጽ አጠቃላይ የተደረገውን ጥረትና ያለውን እንቅስቃሴ የገለጹልን በባህልና ስፖርት ሚኒስትር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው ናቸው፡፡
እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ ፤ወቅቱ አገሪቱ የተለያዩ ሁነቶችን ያስተናገደችበት ከመሆኑም ባለፈ አርሶ አደሩ ከሥራ መልስ በማለት የተለያዩ ድግሶችን የሚያደርግበትና እንደ ሠርግ፣ መተጫጨትና የመሳሰሉ ሁነቶች የሚተገበሩበት ወቅት ነው። ከዚህም ባለፈ ጥር ተቀራራቢና ተከታታይ የሆኑ በርካታ ባህላዊና ኃይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩበት ነው።
ስለሆነም ግብዣው የተደረገበት ይህ ወቅት ለእንግዳውም ሆነ ለእንግዳ ተቀባዩ ምቹ ነው፡፡ በተለይም መንግሥት ሰላምን ለማስከበር በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የገባባትን ጦርነት የመጀመሪያው ምዕራፍ በማጠናቀቁና የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ አጠቃላይ በአገሪቱ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ማየት እንዲችሉ አድርጓል።
ለወትሮው በዚህ ወቅት ይደረግ የነበረው ዝግጅት ተቀራራቢና ተደራራቢ የሆኑ ኃይማኖታዊ የሆኑ የገና እና የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ነበር። በእነዚህ በዓላትም በርካታ ባህላዊ ሁነቶች ይስተናገዳሉ። ለአብነትም ትግል፣ የገና ጨዋታ፣ ጉግስ፣ ሸርጥና ሌሎችም ባህላዊ ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ታድያ በዚሁ ሞቅ ደመቅ በሚልበት ወቅቱ እንግዶች ወደ አገሪቱ መምጣታቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ከመስጠት ባለፈ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አለማየሁ፤ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለረጅም ጊዜ የተለያቸውን ቤተሰቦቹ ይመጣሉ ብሎ በማሰብ ሁሉም በተቻለው መጠን ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል።
ነጋዴውም እንግዳው ፍላጎቱን በሚፈለገው መጠንና ጥራት ማግኘት እንዲችል ያደርጋል። ለዚህም ንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ በንግዱ ዘርፍ ሊኖር የሚገባውን ዝግጁነት በማጠናከር ንግዱ ጤናማ በሆነ መንገድ እንዲከወን አድርጓል።
ሌሎች ተቋማትም እንዲሁ መሰል ዝግጅቶችን አድርገዋል። ሆቴሎችና አጠቃላይ የመስተንግዶ ተቋማትም እንዲሁ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሌሎችም ችግሮች ተቀዛቅዞ የነበረውን እንቅስቃሴ ለማነቃቃት አስፈላጊ የሆነው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እንዲሠራ ተደርጓል።
ለአብነትም ሆቴሎች እድሳት ከማድረግ ጀምሮ ባለሙያዎችን በማሰልጠን እንግዶችን ሞቅ ባለ አቀባበል ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል። ጎዳናዎችንም በማጽዳት ንጹህ እና በቆይታቸው ደስተኛ እንዲሆኑ ነው ጥረት የተደረገው።
ዲያስፖራው በአገር ቤት ቆይታው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አገሩን ማገዝ የሚችልባቸው በርካታ መንገዶች የተዘጋጁ ሲሆን የባህል አልባሳትና ቁሳቁሶችን መጠቀም እንዲችልም የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
ለዚህም ከገና ጀምሮ በየጎዳናው ላይ የሚንቀሳቀሰው ሰው ባህላዊ አልባሳቱን በተለያየ አግባብ በመልበስ አሸብርቆና ደምቆ የታየበት ሁኔታ መኖሩ አንዱ ማሳያ ነው።
ከሰዎቹም በተጨማሪ በየአካባቢው የሚታዩ የኤሌክትሪክና የስልክ ፖሎች በሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም አሸብርቆ ታይቷል። ይህ ሁኔታም ዲያስፖራው ወደ አገር ቤት መግባቱን ተከትሎ እንዲሁም በዓላቱን ምክንያት በማድረግ ከፍ ያለ የግብይት ሥርዓት የነበረ መሆኑን ያመላክታል፡፡
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም የዘንድሮ በዓላት በሁሉም አካባቢዎች ከወትሮው በተለየና በደመቀ መልኩ የተከበረ መሆኑን በተለያዩ የፎቶ፣ የፊልም መረጃዎች የሚያመላክቱ መሆናቸውን ያነሱት አቶ አለማየሁ፤ በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በከፊል አልያም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ባሕላዊ በሆኑ አልባሳትና ቁሳቁሶች አምሮና ደምቆ የታየ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ይህም በተለይም በባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች እንዲሁም ባህላዊ ቁሳቁሶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ግብይት ሥርዓት የነበረ ስለመሆኑ ምስክር ነው ብለዋል።
‹‹ዲያስፖራውን ጨምሮ ማንኛውም የከተማው ሰው ሲንቀሳቀስ በእንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ሰዋዊ ባህሪው በሚጠይቀው ልክ ፍላጎቶቹን ያሟላል›› ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ሰዎች ሲንቀሳቀሱ የትራንስፖርት፣ የምግብና የመጠጥ ፍላጎቶቻቸውን ያሟላሉ። በተለይም ልጆች ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የልጆች ፍላጎት ከፍ ያለ በመሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ፈቃደኛ ሲሆኑ ይታያል።
ስለዚህ እስካሁን ባሉት የበዓላት ቀናት በተለይም በዓላቱ በሚከበሩባቸው አካባቢዎች የግብይት ሥርዓቱ በከፍተኛ መጠን ተከናውኗል። በቀጣይም እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ባሉት ጊዜያቶች ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴው በከፍተኛ መጠን ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ ይጠበቃል። ይህም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚኖረው ድርሻ የጎላ ነው ብለዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥር 18/2014