በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1970 የታተሙት ጋዜጦች ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ በ1969 ዓ.ም ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ለተቀሰቀሰው ጦርነት መፍትሄ ለማምጣት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የወቅቱ የናይጄሪያ ጀነራልና ርእሰ ብሄር በነበሩት ኦባሳንጆ የማግባቢያ ሃሳብ ቢያቀርቡም፣ ሶማሊያ አለመቀበሏን የሚያመለክት እንዲሁም ሌሎች በማኅበራዊ ሕይወት ያጋጠሙ ክስተቶች የተዘገበባቸው ዜናዎችን ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አግባቢ ኮሚቴ ያቀረበውን ሃሳብ ባሬ አልተቀበለውም
በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተሰየመው አግባቢ ኮሚቴ በቅርቡ ካርቱም ውስጥ ተደርጎ በነበረው የመሪዎች ጉባዔ ላይ ያቀረባቸውን ሃሳቦች አድኃሪው የሶማሊያ መንግሥት መሪ አልተቀበልም ማለቱ ተገለጠ፡፡
ይህንን የገለጡት በካርቱም በተካሄደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚኒስትሮችና የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተካፋይ ሆነው የተመለሱት አቶ ብርሃኑ ዲንቃ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለውን ችግር በሚመለከት ረገድ የአግባቢው ኮሚቴ ሊቀመንበር የናይጄሪያ ርዕሰ ብሔር ጄኔራል ኦባ ሳንጆ ለጉባዔው ሪፖርት ማቅረባቸውን አቶ ብርሃኑ ገልጠው ፤በዚሁ ሪፖርት ላይ ቀርበው የነበሩትን ሃሳቦች ፕሬዚዳንት ሲያድ ባሬ ፈጽሞ ያልተቀበሏቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ኮሚቴው ካቀረባቸው ሃሳቦች መካከል የአፍሪካ አገሮች ነፃነታቸውን በተጎናጸፉበት ወቅት በያዙበት ድንበር እንዲፀኑ የሚልና በአገሮች መካከል የሚፈጠርን አለመግባባት ለማስወገድ የሚመለከታቸው ወገኖች በኃይል መጠቀም እንደሌለባቸው የሚያሳስብ ይገኝበታል ፡፡
ከዚህም ሌላ የጊኒ ፕሬዚዳንት ሴኩ ቱሬ ባለሦስት ነጥብ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረባቸውን አቶ ብርሃኑ ገልጸው ፤አንደኛው ነጥብ አትዮጵያና ሶማሊያ የጠብ አጫሪነት ተግባር እንዲያቆሙ የሚል ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ሁለቱም ወገኖች ወታደሮቻቸውን ከየድንበራቸው አምስት ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ እንዲመልሱ የሚጠይቅ ነው፤ ሦስተኛው የአግባቢ ኮሚቴው ሊቀመንበር ጥረታቸውን እንዲገፉበትና የሁለቱም ወገኖች ወታደሮች ወደ ኋላ ማሸግሸጋቸውን እንዲቆጣጠሩ የሚያሳስብ ነው ብለዋል፡፡
ይኸው የውሳኔ ሃሳብ ለጉባዔው እንደቀረበ የናይጄሪያ ልዑካን ማሻሻያ ሃሳብ ሲያቀርቡ የሶማሊያ ልዑካን ሲቃወመው የኢትዮጵያ ልዑካን ግን የውሳኔውን ሃሳብ ከነማሻሻያ ሃሳቡ በአጠቃላይ ይዘቱ መቀበሉን አቶ ብርሃኑ ጨምረው ገልጠዋል፡፡
(ሐምሌ 19 ቀን 1970 ዓም)
ገንዘብ ይዘው ሊወጡ የነበሩ ፪ ሴቶች ተያዙ
ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ለመሄድ የተዘጋጁ ሁለት ኢትዮጵያውያን ፪ሺ፫፻ ብር በልዩ ልዩ ዘዴ ደብቀው ለማስወጣት ሲሞክሩ ትናንት ጠዋት በቦሌ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ በጉምሩክና ፊናንስ ፖሊስ ፈታሾች አማካይነት እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡
ወይዘሮ አልያ የሱፍ የተባለችው ፰፻ ብር ደብቃ የተያዘችው በእጅ ቦርሣዋ ገበር ውስጥ በዘዴ ተሰፍቶ በተጠቀለለ ጨርቅና በጠጉሯ ጭምር ደብቃ ነው ፡፡ ዘይነባ አብዱልቃድር የተባለችው ደግሞ ፩ሺ፭፻
ብር የተገኘባት በቀኝና በግራ ክንዶቿ ላይ በፋሻ ፕላስቲክ አጣብቃና እንዲሁም በጠጉሯ ውስጥ ደብቃ ሲሆን ፤ሁለቱም ሴቶች ገንዘቡን ለማስወጣት የሞከሩበት ሁኔታ በመጣራት ላይ ነው፡፡ (መጋቢት 27 ቀን 1970 ዓ.ም)
ዓባይ ወንዝ የበላቸውን ወታደሩ አዳናቸው
ደብረማርቆስ፡-(ኢ/ዜ/አ-) በጐጃም ክፍለ ሀገር በደብረማርቆስ አውራጃ በደጀን ወረዳ ሰንጣይት አቦ በተባው ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሴት ሰሞኑን በዓባይ ወንዝ ከተወሰዱ በኋላ ከነሕይወታቸው ተገኙ፡፡ የ፵፭ ዓመት አዛውንት ወይዘሮ ወርቄ ቸሬ በአለፈው ሳምንት የደብረ ማርቆስንና የብቸናን አውራጃዎች የሚያዋስነውን የመጋን ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ ይኸው ከፍተኛ ወንዝ እያንሳፈፈ ከዓባይ ወንዝ በመጨመር በጣም ሩቅ ጉዞ ከወሰዳቸው በኋላ ፤ድልድዩን ለመጠበቅ ከተሰማሩት ጓዶች መካከል ወታደር ቸሩ አቤ ሳይሳሳ ከሞላ ውሃ ውስጥ በመግባት በዋና ያዳናቸው መሆኑን የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ አስታውቀዋል፡፡
ለሴትየዋ የሕክምና ርዳታ ተደርጎላቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው የሄዱ ሲሆን ወታደር ቸሩ አቤም የራሱን ሕይወት በመስዋዕትነት አሳልፎ ከዓባይ ወንዝ ገብቶ የሴትየዋን ሕይወት በማትረፉ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ አመስግነውታል፡፡ (ነሐሴ 7 ቀን 19 70ዓ.ም )
በሬውን ገደል የጨመረው ገበሬ በእሥራት ተቀጣ
አሰላ፡-(ኢ/ዜ/አ-) በአርሲ ክፍለ ሀገር በሊሙ በልበሌ ወረዳ በጨመሪ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው በቀለ አረዳ ራሱን እንዲረዳት ከቀበሌው ገበሬ ማኅበር የተሰጠውን የእርሻ በሬ እግሩን አስሮ ገደል በመጨመሩ ተከሶ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት የቀበሌው ፍርድ ሸንጎ በ፫ ወር እሥራት እንዲቀጣ የበየነበት መሆኑን የወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በቀለ አረዳ የተጠቀሰው ቅጣት የተበየነበት የቀበሌው አርሶ አደሮች ራሱን እስኪችል ድረስ እንዲጠቀምበት የሰጡትን የእርሻ በሬ በገመድ አሥሮ ገደል መክተቱ በቀረበበት ማስረጃ ስለተረጋገጠ ነው፡፡ (ነሐሴ 11 ቀን 19 70 ዓ.ም )
እምነት ያጎደለችው የቀበሌ ተመራጭ 3 ወር ተፈረደባት
ድሬዳዋ ፡-(ኢ-ዜ.አ-) በእምነት ማጉደል ወንጀል የተከሰሰች የቀበሌ የሴቶች ማኅበር ሊቀመንበር በቀረበባት ማስረጃ መሠረት በሦስት ወር እሥራት እንድትቀጣ የቀበሌው ፍርድ ሸንጐ ወስኖባታል፡፡
በድሬዳዋ ከተማ አዲስ ዓለም ቀበሌ የሴቶች ማኅበር ሊቀመንበር የነበረችውና ልዩነሽ ክፍሌ የተባለችው ይቺው ተከሳሽ በቅርቡ በካራማራ ተዘጋጅቶ ለነበረው በዓል በቀበሌው ስም እንድታስረክብ ከተሰጣት ፬፻ ብር ውስጥ ፪፻ ብር በማስቀረት ለግል ጥቅሟ አውላ መገኘቷ በማስረጃ ተረጋግጦባታል፡፡
ከዚህም ሌላ ለዚሁ በዓል ወደ ካራማራ አብረው ለሚሄዱት ሁለት ሴቶች ወጪ ከማኅበሩ የተሰጣትን ፩፻ ብር ለራሷ ጥቅም ማዋሏ በተጨማሪ ተረጋግጦባታል፡፡ በዚህም ድርጊቷ በቀበሌው ቁጥጥር ሥር ከዋለችበት ከሚያዝያ ፳፭ ቀን ፸ ጀምሮ በሦስት ወር እሥራት እንድትቀጣ የቀበሌው ፍርድ ሸንጎ ባለፈው ሳምንት ወስኖባታል፡፡
እንዲሁም ለግል ጥቅሟ ያዋለችውን ገንዘብ እንድትከፍል የተወሰነባት መሆኑን የቀበሌው ምክትል ሊቀ መንበር ገልጠዋል፡፡ (ሰኔ 8 ቀን 1970 ዓ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 17/2014