በቀደመው ጊዜ በተወሰኑ ግለሰቦች ይለበስ የነበረው የባህል ልብስ ዛሬ በብዙዎች ተመርጦ ይለበስ ዘንድ ዲዛይነሮቻችን ልዩ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ናቸው።
በአልባሳቱ የራሳቸውን ፈጠራና አዳዲስ ዲዛይኖችን አክለው አስውበውና አዘምነው ፋሽን ሆነው እንዲወጡና በሁሉም ዘንድ ተመራጭ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
በመዲናችን በተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ ሱቆች ተዘዋውረን ስንመለከት ለአይን አዋጅ የሆኑ ያማሩ የአገር ባህል ልብሶች ባማረ ዲዛይን ተሠርተው እንመለከታለን፤ አልባሳቱ የለበሷቸውን ሁሉ ልዩ ውበት እያጎናጸፉ ናቸው።
በተለይ በበዓላት ሰሞን ጎዳናዎችና አደባባዮች በሀበሻ ቀሚስ ለባሽ ሴቶችና በኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች በልዩ ዲዛይን በተሠሩ ውብ ካኒቴራና የአገር ባህል አልባሳት በለበሱ ሰዎች ይደምቃሉ፡፡ ጥምቀትና የአገር ባህል ልብስ እጅጉን ይጎዳኛሉ፡፡ በተለምዶ «ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ» ይባልስ አይደል፡፡
ጥምቀት ሁሉም ያለውን አጥቦና ተኩሶ፣ መግዛት የሚችለው ደግሞ ገዝቶ በአዲስ ልብስ ተውቦና ደምቆ አደባባይ የሚገኝበት በዓል ነው፡፡ በዚህ በዓል በተለይ ወጣቶች፣ የቤተሰብ አባላት ተመሳሳይ የባህል ልብስ አሠርተው ወይም ገዝተው ልዩ ሆነው ይታያሉ፡፡ የዘንድሮው የጥምቀት በዓልን ከሌላ ጊዜ ልዩ የሚያደርገውና ድምቀት እንዲላበስ ያደረገው ሌላ ልዩ ገጠመኝም አለ፡፡
በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ ዳያስፖራዎች/ የጠቅላይ ሚኒስትራቸውን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው በርከት ብለው ወደ አገር ቤት በመምጣት ከሕዝባቸው ጋር ማሳለፋቸው ነው፡፡ እነዚህ ዳያስፖራዎች አገራዊ ናፍቆታቸውን የሚወጡበት ለብሰው አምረው የሚታዩበት የባህል ልብስ በዓይነት ባይነቱ ማግኘቱ አልከበዳቸውም፡፡ ዲዛይነሮቻችን ከወትሮ የተለየ ዝግጅት አድርገው በዳያስፖራዎቹ የሚመረጡ አዳዲስና ልዩ ዲዛይኖችን አዘጋጅተው አልባሳቱን ለገበያ አቅርበዋል፡፡
ሊዲያ ሰለሞን ጎተራ ኮንዶሚኒየም በሚገኝ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ እያዘጋጀች ለገበያ የምታቀርባቸው አዳዲስ የባህል ልብስ ዲዛይኖች በደንበኞቿ እንደሚወደዱ ትገልፃለች፡፡ በዚህም እስከ ውጭ አገር ድረስ እየላከች ገቢዋን ማሳደግ ችላለች፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች ራሷን በማስተዋወቅ በትዕዛዝ የባህል አልባሳትን የምታዘጋጀው ሊዲያ፣ ሰሞኑን ወደ አገር ቤት ለመጡ በርካታ ዳያስፖራዎች አዳዲስ ዲዛይኖች ሠርታ ለሱቆች አስረክባለች፡፡ በዚህም ከወትሮ የተሻለ ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡
የእኛ ገበያ በተለይ በባህል አልባሳት በኩል ዓውዳመት በመጣ ቁጥር የተሻለ ይሆናል፤ በማለት ከወትሮው የተሻለ ግቢ መኖሩን ታስረዳለች፡፡ ኢቫ በላይ ኑሮዋን በጣሊያን ካደረገች 8 ዓመት ሆኗታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው ከመጡ ዳያስፖራዎች አንዷ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ስትመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
በዓሉን ከቤተሰብና ከቀድሞ ጓደኞቿ ጋር በልዩ ድምቀት አክብራለች፡፡ ከዓመታት በኋላ ወደአገሯ ስትመለስ ከተመለከተችው አስደናቂ ነገር መካከል የአገራችን ባህላዊ ልብሶች ይገኙበታል፡፡ ባህላዊ አልባሳቱ በተለያየ ዲዛይን ተውበው ተመልክታለች፡፡
ባህላዊ አልባሳትን ወጣቶች ምርጫቸው አድርገው መልበስ ማዘውተራቸው ደንቋታል፡፡ እሷም ከጓደኞቿ ጋር የተዋበችው ከመጣች በኋላ በሳምንት ውስጥ አዛው በደረሰላት በራሷ ምርጫና የዲዛይን ዓይነት በተሠራላት የአገር ባህል ልብስ ነው፡፡ ኢቫ እንዳለችው፤ ገበያው ላይ በተለያየ ዲዛይን የቀረቡት የአገር ባህል አልባሳት ለተጠቃሚው ምርጫ ጥሩ እድል እንደሚፈጥሩና ወዶ ለመግዛትም የሚጋብዙ ናቸው።
በተለይም የአገር ፍቅርና አንድነትን የሚሰብኩ፣ የአገር ፍቅር ስሜትን የሚቀሰቅሱ አዳዲስ ዲዛይኖች በካኒቴራ መልክ ተዘጋጅተው በወጣቶች በስፋት መለበሳቸው በቅርቡ በነበሩት ሕዝባዊ በዓላት ተመልክታለች፡፡
በተለያዩ ድረ ገፆች የኢትዮጵያ የባህል አልባሳትና አዳዲስ ዲዛይኖች ሲወጡ እዚያም ሆና እንደምትመለከት የምትገልፀው ኢቫ፣ የኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች የሚያወጧቸው የአገር ባህል እልባሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳዩ ያሉት እድገት መልካም የሚባል መሆኑን ታስረዳለች፡፡
ዳያስፖራዎቹ የሚኖሩት ፋሽን ከበረከተበት ባህር ማዶ ነውና ያማረ ዲዛይን ለእነሱ አዲስ አይደለም፡፡ የሚለብሱት በኢንዱስትሪው እጅጉን ባደገ ማህበረሰብ መካከል እንደመሆኑም ስለዲዛይን መሠረታዊ የሆነ እውቀት አላቸው፡፡
ትዕግስት ዘለቀ ከአውስትራሊያ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ አገር ወዳዶች መካከል አንዷ ናት፡፡ በፋሽን ዘርፍ ገና ጅማሮ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳቷ በተለያየ ዲዛይን ተሠርተው በአገር ውስጥ በስፋት ለገበያ ቀርበው መመልከቷ ጥሩ ጅማሮ መሆኑን ትገልጻለች፡፡
ኢትዮጵያ ከመጣች ጀምሮ በምታያቸው የአገር ባህል አልባሳት አዳዲስ ዲዛይኖችና በአገሯ የልብስ ዲዛይን ባለሙያዎች ተደንቃለች፡፡ የራሳቸው የፈጠራ ክህሎት ታክሎባቸው አገራዊ ባህል እንዲገልፁ የተለያየ ባህላዊ ጉዳዮችን እንዲያስተዋውቁ በዲዛይኖቹ ላይ መታከላቸው መልካም ጅምር መሆኑን ታስረዳለች፡፡ እሷም በዲዛይነሮቹ ከተዘጋጁ አልባሳት ለራሷና ለቤተሰቦቿ ገዝታለች፡፡
በምትኖርበት አገር እጅግ የገዘፉ የፋሽን ኢንዱስትሪዎች በርክተው እንደሚገኙ የምትገልፀው ትዕግስት፣ በአገራችንም የልብስ ዲዛይን ባለሙያዎች በተለያየ የአገር ውስጥ ምርት ጨርቆች ማራኪና ተመራጭ የሆነ ልብስ ማዘጋጀት መቻላቸውን በአድናቆት ተመልክታዋለች፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ዳያስፖራዎቹ አንድ የተለየ ምልከታ አላቸው፡፡ እነዚህ ባህላዊ አልባሳት በመሸጫ ሱቆቹ የሚሸጡበት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነና ይህም ልብሶቹ ከዚህ በተሻለ እንዳይለበሱ አገራዊ ምርቶችም በገበያው ላይ ተመራጭ እንዳይሆኑ እንቅፋት እንደሚፈጥር ከአውስትራሊያ የመጣችው ትዕግስት የራሷን ገጠመኝ በመጥቀስ ታስረዳለች፡፡ የኢቫ በላይ አስተያየትም ቢሆን የተለየ አይደለም።
አልባሳቱ በተሻለ ጥራትና የዲዛይን ለውጥ በስፋት ቢገኙም ዋጋ ላይ ግን ከፍ ማለቱን ታዝባለች፡፡ ለዚህ ዋጋ መናር የመስሪያ ቁሳቁስ የአቅርቦት ዋጋ መናር መሆኑን በምክንያትነት የምትገልፀው ዲዛይነር ሊዲያ፣ ልብሶቹ በአብዛኛው የሚሠሩት በእጅ በመሆኑ የሚወስዱት ጊዜም ስለሚጨምር መሆኑን ታስረዳለች፡፡
በአገር ውስጥ በተለያየ መንገድ የሚመረቱ አልባሳት በስፋት ገበያው ላይ መገኘታቸውን የተመለከተችው ትዕግስት፣ ይህም አገራዊ ኢኮኖሚን በመደገፍ ትልቅ አበርክቶ አለው ባይ ናት፡፡ የመንግሥታቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው የመጡ ዳያስፖራዎች በየመንገዱ በኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች የተሠሩ አልባሳትን ተጎናፅፈው በአገራቸው ባንዲራ ያሸበረቁ ልብሶችን ደርበው በየጎዳናው ሽር ሲሉ ታይተዋል፡፡
እኛም በከተማችን ውስጥ ባህላዊ አልባሳት ተጎናፅፈው የዲዛይነሮቻችን አዳዲስ የፈጠራ ሥራ አይተውና ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የሸመቱ እንግዶችን (ዳያስፖራዎችን) አውርተናል፡፡
በኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮች የተሠሩ ባህላዊ አልባሳት ወደገበያው በስፋት መቅረባቸው አገራዊ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ፤ ይህ ብቻ አይደለም ማህበረሰቡ ባህላዊ ይዘቱን የጠበቀ የአለባበስ ሥርዓት እንዲከተል፣ ባህሉን እንዲያከብር ያስችላል፣ ይህ ሁሉ አልባሳት ፋሽን ዲዛይን ዘርፉ እንዲዘምን ይረዳል የሚሉት የዳያስፖራዎቹ አስተያየቶች ናቸው ፡፡
በምልከታቸው በባህል አልባሳት በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ ማየታቸውን የሚገልፁት ዳያስፖራዎች የልብስ ዲዛይን ባለሙያዎቹን ማበረታታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ዲዛይነሮቻችን እጃችሁ ይባረክ፤ ባህልና ማንነታችንን የሚገልፁ ከእኛነታችን ያልራቁ አልባሳት እውቀትና ክህሎታችሁን በመጠቀም ሠርታችሁ ገበያው ላይ ሞልታችኋልና ያብዛላችሁ ተብለዋል፡፡ አበቃን፤ ቸር ያሰማን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014