እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች፣ በጣም ጥሩ። ዛሬ አባቶቻችን ልጆችን ምን ብለው እንደሚመክሩ እናያለን።
ይኸውላችሁ ልጆች አባቶቻችን፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን ለልጆች ጥሩ አመለካከት ነው ያላቸው። ልጆች ጨዋ ሆነው፣ በትምህርታቸው ጎበዝ፣ ታላቆቻቸውን አክባሪ፣ ቤተሰቦቻቸውን አፍቃሪና ለእነሱም ታዛዥ፣ አገራቸውን የሚወዱ፣ ለአገራቸው ሲሉ የሚሞቱ፤ ጥሩ ስነ-ምግባር ያላቸው ወ.ዘ.ተ ሆነው እንዲያድጉ በጣም ይፈልጋሉ። ስለዚህም ይህ ፍላጎታቸው እውን እንዲሆን ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፣ ይመክራሉ፣ ሲያጠፉ ይገስፃሉ ሌላም ሌላም ነገር ያደርጋሉ። ይህ ሁሉ እንግዲህ ልጆች ጨዋ፣ ሀላፊነት የሚሰማቸው፣ አምላካቸውን የሚፈሩ (ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲኖራቸው)፣ አገር ተረካቢ ዜጋ ሆነው እንዲያድጉ በማሰብ ነው። አይደለም እንዴ ልጆች? አዎ ትክክል ናቸው። እነሱ ይህንን ሁሉ ባያደርጉ ኖሬ ዛሬ እናንተ ጨዋ፣ ጎበዝ፣ ሰው አክባሪ፣ አገራችሁን የምትወዱ ወ.ዘ.ተ ትሆኑ ነበር? ላትሆኑ ትችሉ ይሆናል።
ልጆች አያችሁ አባቶቻችን ሲመክሩን የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ይህ ደግሞ ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አዎ፣ ይህንን የሚያደርጉት የሰጡንን መክር እንዳንረሳው፣ ሁሌም እንድናስታውሰው፣ የህይወታችን መመሪያ እንዲሆን ለማድረግ ነው። ለምሳሌ አንድ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እሱን ለማስተላለፍ ከሚጠቀሙባቸው ብልሀቶች አንዱ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ነው። እንደምታውቁት ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ደግሞ ከቅዱሳን (እምነት መጽሐፍት) ይጀምራል። ለምሳሌ የሚከተለውን እንመልከት፤
ልጄ ሆይ! ሕጎቼን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ።
ብዙ ዘመናትንና ረጅም እድሜን ሰላምንም ይጨም ሩልሃልና።
ምጽዋትና ሃይማኖት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላትም ጻፋቸው፤
ባለሟልነትን ታገኛለህና፥ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት መልካምን ዐስብ።
ልጆች አያችሁ ምን ያህል ጥልቅ ምክር እንደሆነ? በጣም ጥልቅና ሰፊ ትርጉም ያለው ምክር ነው። ይህ እንግዲህ ከአንደኛው ሃይማኖት ቅዱስ መጽሐፍ የተወሰደ ጥቅስ ሲሆን፤ በየሃይማኖቱም እንደዚህ አይነት መልእክትን የያዙ ቅዱስ መጽሐፍት ብዙ አሉ። በመሆኑም አባቶች እንደየ ሃይማኖታቸው ለልጆች ምክር ያስተላለፋሉ (ይመክራሉ) ማለት ነው።
ልጆች ግጥም (የግጥም መጽሐፍ) ታነባላችሁ? በጣም ጥሩ። ካነበባችሁማ ደራሲና ባለቅኔ ከበደ ሚካኤልን ታውቋችኋላችሁ ማለት ነው። አዎ፣ ከበደ ሚካኤል ታዋቂ ደራሲና ባለ ቅኔ ሲሆኑ በተለይ የተማሪዎችን፣ የወጣቶችን፣ ባጠቃላይም የዜጎችን ስነ-ምግባር ከመቅረፅ አኳያ ብዙ የሰሩ፣ ብዙ የለፉ፣ በበርካታ ትውልዶችና ተማሪዎች ዘንድ በሚገባ የሚታወቁ የስነ-ምግባር መምህር (አባት) ናቸው።
የከበደ ሚካኤል ስም ሲነሳ አብሮ ሳይነሳ የማይታለፍ አንድ የመጽሐፍ ርዕስ ቢኖር “ታሪክና ምሳሌ” ሲሆን፤ በ “ታሪክና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ” ምን ምን ብለው (ይህንን ከዚህ በፊት “የከበደ ሚካኤል ዐሥርቱ ትዕዛዛት” በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሁፍ ውስጥ ሳልጠቅሰው አልቀርም፤ ዛሬ ደግሞ ለእናንተ) ተማሪዎችን እንደ መከሩ ተመልከቱ።
ከበደ ምክራቸውን ሲጀምሩም “እኛ ኢትዮጵያውያን ባሁኑ ጊዜ በግድ ልንከተለውና ልንፈፅመው የሚገባን ዐሳብ ከዚህ ቀጥሎ ያለው ነው።” በማለት መሆኑን አስቀድሜ ልነግራችሁ ፈልጋለሁ።
አንደኛ፤ – ኢትዮጵያዊ የሆንህ ሰው ሁሉ ንጉስህ፣ ሰንደቅ አላማህ፣ አገርህና ነፃነትህ የሚጠቁበትን ነገር ለማስወገድ ወይም ደግሞ እነሱ የሚጠቀሙበትን ስራ ለመፈፀም ብለህ በሞትህ ጊዜ በሰማይና በምድር ስምህ በወርቅ ቀለም የሚፃፍበትን የሰማዕትነት ሥራ መስራትህን ልብህ ተረድቶ ደስ ይበለው።
ሁለተኛ፤ – አገርን መውደድ ማለት አገርህ የምትጠቀምበትንና የምትከበርበትን ሥራ መሥራት ማለት ነው።
ሶስተኛ፤ – አገርህንና ወገንህን የሚያስንቅ ወይም የሚጎዳ ሥራ ከመሥራት መሞት ይሻልሀል።
አራተኛ፤ – እኛ ኢትዮጵያውያን የምንሰራው ስራ መልካም ቢሆን አገራችን ኢትዮጵያ እንደምትከበር የምንሰራው ሥራ መጥፎ ቢሆን ግን እንደምትዋረድ አትርሳ።
አምስተኛ፤ – ኢትዮጵያ አገርህ ከሌሎቹ ከማንኛቸውም አገሮች ሁሉ ይልቅ የምትበልጥብህ መሆንዋ ቀንም ሆነ ሌሊት በዐሳብህ ውስጥ ሳይረሳና ሳይዘነጋ ተጽፎ ይኑር።
ስድስተኛ፤ – ማንኛውም የውጭ አገር ሰው ለተወለደባት አገሩ የሚያስብላት መልካም ዐሳብ ወይም የሠራላት መልካም ሥራ ሲነገር በሰማህ ወይም ተጽፎ ባየህ ጊዜ አንተም ደግሞ እንደዚሁ ይህንኑ ያህል ላገርህ ለኢትዮጵያ ልታስብላትና ልትሰራላት የሚገባህ መሆኑን እወቀው።
ሰባተኛ፤ – አንድ ኢትዮጵያዊ ሲበደልና ሲጠቃ ባየህ ጊዜ የተበደለችውና የተጠቃችው እናትህ ኢትዮጵያ መሆንዋን ተረዳው።
ስምንተኛ፤ – ኢትዮጵያ አገርህ በእውነት ትልቅ ሳትሆንና ወንድሞችህም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሳይደላቸው አንተ ብቻህን የምታገኘው ደስታ፣ ገንዘብና ተድላ በህልም እንደ ተገኘ ወርቅ መና፤ ባዶ ሆኖ የሚቀር መሆኑን ልብህ አይዘንጋው።
ዘጠነኛኛ፤ – ብዙ ገንዘብና ብዙ ርስት ከማግኘት ይልቅ ለአገሩ ትልቅ ሥራ የሠራላት ሰው ስሙ ለዘለዓለም በታሪክ ሲጠራ ይኖራል።
ዐስረኛ፤ – ሌሎቹ የዓለም ነገሥታት ከደረሱበት የስልጣኔ ደረጃ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ በቶሎ እንድትደርስ እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ማሰብና መጣጣር ይገባናል። ድካማችንና ትጋታችንም በተለየ ለዚሁ ዐሳብ ብቻ እንዲሆን ያስፈልጋል።
ታዲያስ ልጆች፤ ከበደ ሚካኤልን አላደነቃችኋቸውም፤ አልወደዳችኋቸውም? እንደ ወደዳችኋቸው እርግጠኛ ነኝ አይደል ልጆች፤ በጣም ጥሩ።
በሉ እንግዲህ የአባቶቻችንን ምክር በሚገባ ስራ ላይ እንደምታውሉ እርግጠኛ በመሆን ደህና ሁኑ ልላችሁ ነው። ደህና ሁኑ ልጆች፣ ደህና ሁኑ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014