የአፍሪካ ውክልና – በጸጥታው ምክር ቤት

ዜና ትንታኔ

በሰው ሠራሽ ቀውሶች፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በዕዳ ጫና እየተፈተነች የምትገኘው አፍሪካ እንደ ጸጥታው ምክር ቤትና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች በመሳሰሉ ተቋማት ውስጥ ተገቢ ውክልና አለመኖሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ከሆነባት ሰነባብቷል፡፡

በዚህም የተነሳ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንዲሰጣት ግፊት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ነገሩ አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም ነውና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ለአፍሪካ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ ዘመናት አልፈዋል፡፡

አፍሪካ ለጥያቄዎቿ የሚሆን ምንም እንኳን ለረጅም ጊዜ ያለምላሽ ብትቆይም የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በነሃሴ ወር 2016 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ለአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲሰጣት ጥሪ ካቀረቡበት ጊዜ አንስቶ ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት አግኝቷል፡፡

ዋና ጸሐፊው የምክር ቤቱ አሰራርና በአባላት ስብጥሩ በፍጥነት ከሚለዋወጠው የዓለም ሥርዓት ጋር እኩል የሚራመድ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ለአላት የአፍሪካ አህጉር በምክር ቤቱ ቋሚ ድምጽ አለመኖር ተቀባይነት የሌለው መሆኑም የብዙኃኑ አስተያየት ነው።

ኢትዮጵያም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ሰኞ ዕለት መስከረም 13 ቀን 2017 በኒውዮርክ በተካሄደው 79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተ.መ.ድ የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ የአፍሪካን እውነተኛ ውክልና ባረጋገጠ መልኩ እንዲከናወን ጠይቃለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ጥያቄያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ምክር ቤቱን ለማሻሻል የሚደረገው እንቅስቃሴ የአፍሪካን የውክልና አድማስ ከሁሉም መመዘኛዎች አንጻር ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባው ጠይቀዋል።

አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ብታገኝ በተለይ ጦርነትና አለመረጋጋቶችን በቀጣናው ከመቀነስ በተጨማሪ ውሳኔ ሰጪነትን ከማሳደግና አህጉራዊ ጥቅሞችን ከማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር እና የሕግ አማካሪ ተስፋዬ አባተ (ዶ/ር) ለኢፕድ በሰጡት ቃል አህጉሪቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና የሚሰጣት ከሆነ በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ፍላጎት ተግባራዊ እንድታደርግ ያግዛታል ይላሉ።

አፍሪካ እንደ አህጉር ጥቅሞቿን ለማስከበር፣ አጀንዳዎቿን ለማስጠበቅ እና ተሰሚነቷን ለማሳደግ የሚኖረው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ባይ ናቸው።

አፍሪካ እንደ አፍሪካ እስከ አሁን በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ባለማግኘቷ ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጓታል የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ፤ በተለይ አፍሪካ በሌለችበት የሚሰጠው ውሳኔ የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ሙሉ ጠባይዋን ያላገናዘብ ውሳኔ እንደሚሆን ይጠቁማሉ።

ዶክተር ተስፋዬ እንደሚገልጹት፤ ታዳጊ ሀገራት የራሳቸው የማደግ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ የማደግ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ነገር ግን እስካሁን ባለመሆኑ ግን እድገቱ እንዲቀጭጭ ማድረጉንም ያብራራሉ።

አፍሪካ በድርጅቱ ቋሚ መቀመጫ የምታገኝ ከሆነ ድምጽን በድምጽ የመሻር ዕድልን ለመጠቀም የሚረዳት መሆኑንም ያስረዳሉ።

አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ፤ ከዚህ ቀጥሎም በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ አፍሪካ እንደ አህጉር የመልማት አቅም የማሳየትና የመሪነት ሚና ማሳደግ ይጠበቅባታል።

ከዲፕሎማሲው ጎን ለጎንም ባለሙያዎች በየመስኩ ሙያቸውን በተገቢው መንገድ ማከናወን እንዲሁም በቴክኖሎጂ ረገድ ዓለም እያደረገች ያለችውን የቴክኖሎጂ ለውጥ መከተልና መተግበርም ለዚህ የሚረዳ እንደሆነ ያክላሉ።

በአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ፣ የመካካለኛው ምሥራቅና የቀጣናዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ጆርጅ ካታሪኖ እንደሚሉት፤ አፍሪካ ከ70 ዓመታት በላይ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሳታገኝና ፍላጎቷን ሳታሳካ ቀርታለች።

የአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ችግሮች በተመለከተ በጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ባልተገኘችበትና ድምጿን ባልሰጠችበት ሁኔታ ተፈጻሚ እየሆነ መቆየቱንም ይጠቁማሉ።

በተለይ አሁን ላይ የዓለም ሕዝቦች የአሰፋፈርና አስተዳደራዊ መዋቅር ጋር ተያይዞ አካታችና ሁሉን አቀፍ ውሳኔ ለመስጠት የተ.መ.ድ.ጸ.ም.ት ሪፎርም የሚያስፈልገው ስለመሆኑንም ያብራራሉ። ይህም አስፈላጊነቱ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ታዳጊ ሀገራትም ጭምር ነውም ይላሉ።

በተ.መ.ድ የዩናይትድ ኔሽን አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በበኩላቸው ዓለም ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የጸጥታው ምክር ቤት ተገቢውን ሪፎርም ማድረግ ያስፈልገዋል ባይ ናቸው።

አሁን ላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስብስብ ችግር ተጋርጦበታል የሚሉት አምባሳደር ቶማስ-ግሪንፊልድ፤ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ጦርነት እንዲሁም ኮቪድ-19 በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ያስታውሳሉ።

አሁን በዓለም ላይ እያጋጠሙ ያሉት የተለያዩ ችግሮች አካታች የጸጥታ ምክር ቤት አለመኖሩ ማሳያ ነውም ይላሉ።

አሜሪካ ለአፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ላይ ሁለት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅሰው፤ ምክር ቤቱ ውይይት ብቻ ማድረግ ሳይሆን ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትም ይመክራሉ

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You