ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ጥቅሞች የሚያስጠብቁ ውይይቶች እየተካሄዱ ናቸው

አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 79ኛው የተመድ ጉባዔ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ጥቅሞች በሚያስጠብቁ፣ ሁለትዮሽን በሚያጠናክሩና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደኀንነት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ከተለያዩ ሀገራት ጋር እያካሄደች እንደምትገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በድረ ገጹ፤ በኒውዮርክ እየተካሄደ ካለው ጉባዔ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ጥቅሞች ለሚያስጠብቁ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ውይይቶች እያካሄዱ እንደሚገኙ አስነብቧል።

አምባሳደር ታዬ ከዴንማርክ አቻቸው ላርስ ሎክ ራስምሰን ጋር ባደረጉት ውይይት ዴንማርክ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሆና በመመረጧ ደስታቸውን ገልጸዋል። በወቅታዊ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች እና ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ባላት ቁርጠኝነት ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቡት ናህያን አል ናህያን ጋር በሁለትዮሽ እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ደህንነት ዙሪያ መክረዋል።

ሶማሊያን በተመለከተ የቀጣናው ሀገራት ዋጋ የከፈሉበት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የሶማሊያ ደህንነት እንዲቀጥል ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚኖረው የኃይል ሥምሪት ጊዜ ተወስዶ በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት ገልጸዋል።

ከሕንድ አቻቸው ዶክተር ሱብራማንያ ጄይሻንካር ጋር ባደረጉት ውይይትም፤ ሁለቱ ሚኒስትሮች የጋራ ፍላጎት በሚሹ ሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል።

ከግሪኩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊኦርጎስ ጀርፐትራይተስ ጋር ባደረጉት ውይይትም፤ ግሪክ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሆና በመመረጧ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የምታደርገውን ፀረ-ሽብር ዘመቻ አጠናክራ ለመቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

አምባሳደር ታዬ ከሴራሊዮን ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ጢሞቲ ካባ ጋር በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ደኀንነት ዙሪያ መክረዋል።

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከተመድ የሰላም ኦፕሬሽን ረዳት ዋና ፀሐፊ ዣን ፒዬር ለክሮይ ጋር ባደረጉት ውይይት ረዳት ዋና ፀሐፊው ኢትዮጵያ ለተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላትን አስተዋፅኦ እና ከድርጅቱ የሰላም ኦፕሬሽን ጋር የፈጠረችውን ጠንካራ ግንኙነት አድንቀዋል።

አምባሳደር ታዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፤ በሶማሊያ ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚኖረው የኃይል ስምሪት በቂ ጊዜ ተወስዶ በጥንቃቄ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

አምባሳደር ታዬ፤ ከሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ኦሊቨር ኒዱሁንጊሬሄ እና ከኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄጄ ኦዶንጎ ጋር በተናጠል ተወያይተዋል።

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከሩዋንዳው አቻቸው አምባሳደር ኦሊቨር ኒዱሁንጊሬሄ ጋር በነበራቸው ውይይት የናይልን ወንዝ የውሃ ሀብት ፍትሐዊ እና እኩል ለመጠቀም ለትብብር ማዕቀፉ ስምምነት ትግበራ በጋራ ለመሥራትም ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ለሶማሊያ ሰላም ማስከበር ወታደር ካዋጡ ሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚደረግ ማንኛውም ችኮላ የተሞላበት ስምምነት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ እስካሁን የተገኙ ስኬቶችን አደጋ ላይ ይጥላል የሚል የጋራ ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ወደ ተግባር መቀየሩ የጋራ ሀብትን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም እና በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ከፍ ለማድረግ አወንታዊ እድገት መሆኑን አምባሳደር ታዬ ጨምረው ገልጸዋል።

ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር በነበራቸው ቆይታም፤ አሜሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና አጠቃላይ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ከቻይናው አቻቸው ዋንግ ዩ ጋር ባደረጉት ውይይትም ሚኒስትሩ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ‘’የምንጊዜም ስትራቴጂክ አጋርነት’’ (All Weather Stratagic Partnetship) መሆኑ በቀጣይ በርካታ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት መሠረት የጣለ መሆኑን ገልጸዋል።

በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይና ጉብኝት ወቅት ስምምነት የተደረሰባቸው የኢኮኖሚ ትብብር ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከቀረጥና ታሪፍ ነፃ የገበያ ዕድሎች ትኩረት ተሠጥቷቸው ተግባራዊ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።

ከ.ተ.መ.ድ. የሰላም ግንባታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሐፊ ሮዝማሪ ዲካርሎ ጋር ባደረጉት ውይይትም፤ በሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለሱዳን ቀውስ መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው የሚል አቋም እንዳላት አንስተዋል።

አምባሳደር ታዬ ሶማሊያን በተመለከተ ከሮዝማሪ ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ሽብርተኞችን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ከአልጄሪያ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያና አልጄሪያ በአፍሪካ አህጉር በሚታዩ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ይበልጥ ተቀናጅተው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሚኒስትሮቹ በቅርቡ ለሚካሄደው አምስተኛው ኢትዮ – አልጄሪያ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።

የ.ተ.መ.ድ 79ኛ ጠቅላላ ጉባዔ “ማንንም ወደ ኋላ አለማስቀረት፤ ለአሁኑ እና ለመጪው ትውልድ ሰላም፣ ዘላቂ ልማት እና ሰብአዊ ክብር በጋራ መሥራት” በሚል መሪ ሃሳብ ከመስከረም 14 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም በኒውዮርክ በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You