የዛሬው ሳምንቱ በታሪኩ አንዱ ርዕሰ ጉዳያችን ዝነኛው የሲቪል ራይት /መብት/ ንቅናቄ ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው፡፡ ይህ ሳምንት ዓመታዊው የኪንግ ቀን የተከበረበት በመሆኑም ርዕሰ ጉዳያችን ያደረግነው፡፡ ቀኑ መከበር የጀመረው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1985 ሲሆን፣ በየዓመቱ በፈረንጆቹ ጃንዋሪ 15 እና 21 መካከል ባለው ሰኞ ይከበራል።
ዝነኛው የሲቪል ራይት /መብት/ ንቅናቄ ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ጃንዋሪ 15 ቀን 1929 እስከ ኤፕሪል 4/1968) በአሜሪካ የባፕቲስት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ነበር፡፡ ቀስ በቀስም ከባፕቲስት ቤተክርስቲያን አገልጋይነት ወደ ሕዝብ አንቂነት (activist) ገባ፤ በዚህም ይበልጥ ዝነኝነትን እያገኘ ሄደ፡፡ እጅግ በጣም ተደማጭ የአሜሪካ ሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴ ቃል አቀባይ መሪ ሆኖም ከ1955 እስከ እከተገደለበት 1968 አገልግሏል ፡፡
ማርቲን ሉተር ኪንግ የሲቪል መብቶችን ነውጥ አልባ እና ሕዝባዊ ንቅናቄን በክርስትና እምነት ተመስጦዎችና እና የማህተመ ጋንዲን ግጭት አልባ ንቅናቄዎችን በማካሄድ ይታወቃል፡፡ ኪንግ ለጥቁሮች መብትና ነፃነት ባደረገው ትግል በምርጫ ድምፅ የመስጠት መብት እንዲኖራቸው፣ በሰዎች መካከል ምንም አይነት ልዩነት እንዳይኖር፣ የሠራተኝነት መብትና ሌሎች የሲቪል መብቶቻቸው እንዲከበሩ ጥረት አድርጓል፡፡ እነዚህን መብቶች ለማስከበር ሰልፎችን በማስተባበርና ከፊት ለፊት ሆኖ በመምራት ሚናውን ተጫውቷል፡፡ በ1955 በሞንትጎሞሪ የአውቶቡስ ተቃውሞን መርቷል፡፡ የደቡብ ክርስቲያን አመራር ጉባኤ ፕሬዚዳንት እንደሆነ ያልተሳካውን በአልባኒ ጆርጂያ የተካሄደውን የአልባኒ አንቅስቃሴ መርቷል፡፡
ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርና የትግል አጋሮቹ ጥቁሮች በተፈጥሮው ሰው ስለሆነ ብቻ ሊያገኘው የሚገባውን የተፈጥሮ መብት ጨምሮ በአገሪቱ ሕገ-መንግስት (እነርሱ የሪፐብሊኩ መስራች አባቶች (Founding Fathers) ብለው በሚጠሯቸው ግለሰቦች) የተፃፉትን መርሆች የሚቃረን መዋቅራዊም ሆነ ግለሰባዊ አድልዎ ለማስቀረት ኃይል ያልተቀላቀለበት አመፅ ማድረግ ውስጥ ገቡ፡፡
ምንም እንኳን ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርና መሰሎቹ አመፅ-አልባ የትግል ስልትን ቢመርጡም እነርሱ የሚታገሉት የነጮችን የበላይነት የሚያራምደው መዋቅራዊ ስርዓትም ሆነ ግለሰቦች ይህን አመፅ-አልባ ትግል ለማስቀረት የተከተሉት መንገድ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርን ጨምሮ በዚህ አመፅ-አልባ ትግል ውስጥ የተሳተፉት ጥቁሮች ተደብድበዋል፣ ታስረዋል ተገድለዋል፡፡
እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጥቁሮቹን ከሰውነትና ከዜግነት በታች ያደረጋቸውን ስርዓት ለማስቀረት አመፁ፡፡ አንዱ የአመፁ መገለጫ የአደባባይ ሰልፍ ማድረግ ነውና በአገሪቱ ዋና ከተማ በዋሽንግተን ዲሲ አደባባይ ብዙ ሺዎች ሆነው ተሰለፉ። በዚህ የ1963 እ.ኤ.አ. የአደባባይ ሰልፍ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር “ህልም አለኝ” የተሰኘ ዝነኛ ንግግሩን አሰማ፡፡
በዚህም በወቅቱ የሲቪል መብቶች አንቅስቃሴዎች ወሳኝ የሕግ አውጪ ሕግ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉበትን ሁኔታ አሳካ። በ1964 በሲቪል መብቶች ሕግ ውስጥ ድምፅ የመስጠት ሕግ እና በ1968 ደግሞ ፍትሐዊ መጠለያ ቤት የማግኘት ሕግ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
በዚህ ንግግሩ ላይ “ … ወደ አገሪቱ ዋና ከተማ የመጣነው የተሰጠንን ቼክ ልንመነዝር ነው፡፡ የሪፐብሊኩ መስራቾች አንፀባራቂ የሆኑትን ሕገ-መንግስትና የነፃነት አዋጅ ባወጡ ጊዜ ሁሉም አሜሪካዊ ወራሽ የሚሆንበትን የቃል-ኪዳን ሰነድ (Promissory Note) ነው የሰጡን፡፡ … ይሁን እንጂ አሜሪካ ለጥቁር ህዝቦቿ ‘በቂ ስንቅ የላትም’ የሚል ማህተም የተረገጠበት ‘ደረቅ ቼክ’ ሰጥታቸዋለች፡፡ ነገር ግን በአሜሪካ ታላቅ የመጠቀም ዕድል ካዝና ውስጥ በቂ የሆነ ሀብት የለም ብለን አናምንም፡፡ ስለሆነም ዛሬ የነፃነትን ሀብትና የፍትህን ዋስትና የሚሰጠንን ይህንን ቼክ ልንመነዝር መጥተናል፡፡” ሲል አስገንዝቧል፡፡
ምንም እንኳን ይህ የደረቅ ቼክ ይመንዘርልን ጥያቄ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየርን ህይወት ጨምሮ የብዙ ሰዎችን ህይወት ያሳጣ ቢሆንም ከግማሽ በላይ የሚሆነው ግን ተመንዝሯል፡፡ ዛሬ ጥቁሮች የመመረጥና የመምረጥን ጨምሮ ከነጮች ጋር በአንድ ት/ቤት የመማር፣ ምግብ ቤት ፣ መፀዳጃ ቤት፣ የህዝብ ትራንስፖርት የመሳሰሉትን የመጠቀም መብት አላቸው፤ ይህም ኪንግ ካስነሳው ተቃውሞ የተገኘ አመርቂ ውጤት ነው፡፡
አሁንም ቢሆን ያልተመነዘሩ ቀሪ የቼኩ ስንቆች አሉ። በግለሰብና በመዋቅራዊ ሥርዓት የሚደረጉ መድሎዎች አሁንም አላቋረጡም፡፡ መሣሪያ ያልታጠቁ ጥቁሮች በታጠቁ ፖሊሶች ይገደላሉ፡፡ ጥቁሮች ከነጮቹ የበለጠ በአነስተኛ የህግ መተላለፍ ጥፋቶች የረዥም ዓመታት አሊያም የዕድሜ ልክ እስራት ይፈረድባቸዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን በስታርባክስ የቡና መሸጫ ሰው ለመጠበቅ የገቡ ሁለት ጥቁሮች ፖሊስ ተጠርቶ እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡ (ምንም እንኳን በኋላ የስታርባክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ በይፋ ይቅርታ ቢጠይቅም) ይህ አይነቱ አድልዎ BLM (Black Lives Matter) የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡
ኪንግ የደቡብ ክርስቲያን አመራር ጉባኤን በልምምድ ነውጥ አልባ በሆነው ተቃውሞ ውስጥ በብልሀት እንዲገባ አደረገው፡፡ አንዳንድ ተቃውሞዎቹ ስልታዊ በሆነ መልኩ ዘዴዎቹንና ምቹ ቦታዎችን እየተጠቀመ የተገበራቸው ናቸው። በተውኔት መልኩ መሰናክል ሆነው ሊቆሙ የመከሩ እና መለያየትን ያነገቡ ባለሥልጣኖችም አንዳንዴ ደገፈውት ተነስተዋል፡፡
ኪንግ ለብዙ ጊዜያት ታስሮም ነበር፡፡ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ዳይሬክተር ጄ እ ድጋር ሁቨር ኪንግን ፅንፈኛ አድርጎ በመመልከት ከ1963 ጀምሮ ሲከታሉት ነበር፡፡ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ወኪሎች ወንጀል ነው ብለው በሚገምቱት ሁላ እየወሰዱ ይመረምሩት ነበር፡፡ በግል ሕይወቱ ላይ ሰላይ ልከው እና በምስጢር ይቀርጹት ነበር፡፡ በ1964 ለኪንግ የሚያስፈራራ ባለቤቱ ያልታወቀ ደብዳቤ ተላከለት፡፡ ይህም በራሱ ላይ የግድያ ሙከራ እንዲፈጽም የሚያነሳሳ ነበር፡፡
በኦክቶበር 14 ቀን 1964 ኪንግ ዘረኝነትን እና አድሏዊነትን ነውጥ አልባ በሆነ ተቃውሞ በመዋጋቱ እና በመምራቱ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነ፡፡ በ1965 ከሞንትጎሞሪ ሦስት ንቅናቄዎች ሁለቱን መርቶ ነበር፡፡ በመጨረሻዎቹ ዓመታቱ ንቅናቄውን በማስፋት ህብረተሰቡ በተለይም ጥቁሮች ድህነትን፣ ካፒታሊዝምን እና የቬትናምን ጦርነት ለመዋጋት አንዲንቀሳቀሱ ተሳትፎ ነበር፡፡
በ1968 ኪንግ ብሔራዊ የዋሽንግተን ዲሲ ሥራ ለድሆች በሚል ዕቅድ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥረት ሲያደረግ በቴንስ በኤፕሪል 4 1968 በሜምፊስ ቴንስ ተገደለ፡፡ ግድያው በብዙ የአሜሪካን ከተሞች ነውጥ አስነሳ፡፡ ጀምስ አርል ራይ ኪንግ ኪንግን ገድሏል በሚል ተከሶ ተፈርዶበታል፡፡ ይህንንም ሊፈጽም የቻለው ከአንዳንድ የመንግሥት ወኪሎች ከተባሉ ጋር ተነጋግሮ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡
ኪንግ ከሞተ በኋላ ስም ከመቃብር በላይ ይሆናል እንደሚባለው መልካም ሥራው ተጠቃሽ እና አስተማሪ ሆኗል፡፡ በዚህም ከሞተ በኋላ በ1977 የፕሬዝዳንታዊ የነፃነት ሽልማት ሜዳልያ እና የምክር ቤቱ የወርቅ ሜዳልያ በ2003 እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡
ከ1971 ጀምሮ በአሜሪካ ግዛቶች የማርቲን ሉተር ቀን የሚል ብሔራዊ ቀን ተደርጎ ይከበራል፡፡ በዓሉ ሲከበር ቆይቶ በ1986 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ሕግ እንዲወጣለት አስደርገውና ፈርመው በፌዴራልና ግዛቶች ይበልጥ እንዲከበር አድርገውታል፡፡ በዚህም ከ100 በላይ በአሜሪካ የሚገኙ ከተሞችና መንገዶች ለክብሩ በሚመጥን ደረጃ ቦታዎች ሰይመዋል፡፡ በዝነኛዋ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማም ለኪንግ መታሰቢያ እንዲሰይም እንደገና ተወስኖ ተተግብሯል። የዋሽንግተን ዲሲ የማርቲን ኪንግ አጠቃላይ መታሰቢያ ብሔራዊ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰየመ፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014