ኢትዮጵያን ከመሩ ነገስታት አንዱ አጼ ዮሃንስ አራተኛ ናቸው፡፡ አጼ ዮሀንስ ከ1864 እስከ 1881 ድረስ ነው ኢትዮጵያን በንጉሰ ነገስትነት የመሩት፡፡ አጼ ዮሃንስ የንጉሰ ነገስትነት ስልጣኑን የተቆናጠጡት በኢትዮጵያ አቆጣጠር በዚህ ሳምንት ነበር፡፡ ንጉሰ ነገስት እስከ ተባሉ ድረስም ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ ይባሉ የነበረ ሲሆን፣ ከዛሬ 149 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም አፄ ዮሃንስ አራተኛ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው ነገሱ፡፡
አፄ ዮሃንስ አራተኛ የተንቤን ባላባት ከነበሩት የራስ ሳህለ ሚካኤል የልጅ ልጅ ከሹም ተንቤን ምርጫ እና ከእናታቸው የእንደርታው ገዥ የራስ አርአያ እህት ወይዘሮ ሥላስ ድምፁ ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም በትግራይ ተንቤን ልዩ ስሙ ማይበሀ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ ተወለዱ።
ርዕሰ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ ሐምሌ 6 ቀን 1863 ዓ.ም አፄ ተክለጊዮርጊስን አድዋ አካባቢ አሳም የሚባል ሥፍራ ላይ ወግተው ድል አደረጓቸው፡፡ በዝብዝ ካሳ አፄ ተክለጊዮርጊስን ድል ካደረጉ በኋላ ለስድስት ወራት ለሥርዓተ ንግሥ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም አክሱም ላይ ሥርዓተ ንግሣቸው ተፈጽሞ አፄ ዮሃንስ አራተኛ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ።
ተክለጻድቅ መኩሪያ ‹‹አፄ ዮሃንስና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጽሐፋቸው ስለድግሱ ዝግጅት አስፍረዋል፡፡ በዚህ ጽሁፍም ፣ “…ድግሱም ሲሰናዳ ቆይቶ በጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም በአክሱም ቤተክርስቲያን ስመ መንግሥታቸው “ዮሃንስ አራተኛ” ተብሎ በጳጳሱ በአቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው በሥርዓተ መንግሥት ነገሡ፡፡
‹‹በዚሁ ስርዓተ ንግሥ ምክንያት ሦስት ቀን በዓል ተደርጓል፤ ለግብር 4ሺ ሰንጋ ታርዶ እና 50 ጉንዶ ማር የፈጀ 150 ሺህ ገንቦ ጠጅ ቀርቦ በደስታ ሲበላ ሲጠጣ እንደሰነበተ ሙሴ ጂ. በዝርዝር ጽፎ አትሞታል፡፡ የአገራችንም ጸሐፊ አለቃ ዘ ዮሃንስ የንግሡን ሁኔታ በመጥቀስ ከነገሡ በኋላ በቤተመቅደስ ወርቅ መበተናቸውን 30 ቀን ሙሉ የደስታ በዓል መደረጉን ጠቅሰውታል፡፡” ሲሉ ተክለጻድቅ መኩሪያ አብራርተዋል፡፡
ከዊኪፒዲያ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ ፤ አፄ ዮሃንስ 4ኛ ከእንግሊዝ ንግስት ጋር በመፃፃፍ ነግስናቸውን አጠናክረዋል፡፡ ይህም ተቀናቃኛቸው የነበሩት አፄ ሚኒሊክን ለማስገበር መጥቀሙን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከአፄ ሚኒሊክ ጋር የነበራቸውን የስልጣን ሽሚያ ለመከላከል ሲባል ደብረ ብርሃን ድረስ በመሄድ ድርድር በማድረግ የነበራቸውን ባላንጣነት አስወግደው ሚኒሊክ ንጉስ እንዲባሉና አፄ ዮሃንስ ርዕሰ ብሔር እንዲሆኑ ተስማምተዋል ፡፡
ሁለት ጊዜ ግብፆችን ድል በማድረጋቸው ስማቸው ገናና ሆኖ ነበር፡፡ የንግስና ዘመናቸውን በጦርነቶች ያሳለፉት አጼ ዮሃንስ ህይወታቸውን ያጡትም ከደርቡሾች ጋር በተደረገ ጦርነት ላይ እየተዋጉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አፄ ዮሃንስ በወረራ መተማንና አልፎም እስከ ሳር ውሃ ተቆጣጥሮ የነበረውን የሱዳን ሰራዊት /ደርቡሾች/ ለመዋጋት ወደ መተማ ዘመቱ፡፡ ወደ መተማ ሰራዊታቸውን አስከትለው የሄዱት፣ ሰሃጢ ላይ ከጣሊያኖች ጋር የነበራቸውን ፍጥጫ ትተው ነው፡፡
ሰሃጢ ላይ፣ ጣሊያኖችን ከምፅዋ ምድር ለማስወጣት ዘምተው ሳለ ደርቡሾች ወሰን አልፎ መያዙን ሰሙ፡፡ ወረራውን እንደሰሙ በንጉስ ተክለ ሃይማኖት የሚመራው የጐጃም ጦር የሱዳንን ወታደሮች እርምጃ እንዲቆጣጠር አዘዙ፡፡የጐጃም ጦር፣ ሳር ውሃ በተባለው አካባቢ ከሱዳኖችጋር ፅኑ ውጊያ ቢያደርግም አልቀናውም፡፡
ንጉስ ተክለ ሃይማኖት፤ ጥቂት ራሳቸውን ሆነው ሲያመልጡ፣ አያሌ ሰራዊት ለሞትና ለምርኮ ተዳረገ። በኢትዮጵያኖቹ መማረክና መታረድ እጅግ ያዘኑት አፄ ዮሃንስ የሰሃጢውን ዘመቻቸውን ትተው ወደ መተማ አቀኑ፡፡ አብረዋቸውም ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና መቶ ሺህ የሚደርስ ሰራዊታቸው ተከትለዋቸዋል፡፡
በዛኪ ቱማል የሚመራው የሱዳን ወራሪ ጦር በመተማ ላይ ጠንካራ ምሽግ ሰርቶ ውጭውንም በሹል እንጨትና በድንጋይ አጥሮ 60 ሺህ ይደርሳል የተባለውን ሠራዊቱን አዘጋጅቶ ተሰለፈ፡፡ መጋቢት 1 ቀን ጠዋት ጦርነቱ ተጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት በጀግንነት እየተዋጋ የመጀመሪያውን ምሽግ ጥሶ ገባበት፡፡
በሳር ውሃው ጦርነት የሞቱትን ዜጐቻቸውን ሲያዩ ቁጭት የገባቸው አፄ ዮሃስን ራሳቸው እንደ አንድ ወታደር ሆነው በጦር ግንባር ገብተው ተዋጉ፡፡ በጦርነቱም የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል ለማድረግ በተቃረበበትና የሱዳን ሠራዊት ከምሽጉ ወጥቶ ለመሸሽ በተዘጋጀበት ወቅት አፄ ዮሃንስ እጃቸው ላይ ቆሰሉ፡፡ ቢሆንም ከጦርነቱ መካከል አልወጡም፡፡
እንደገና በግራ እጃቸው አልፋ ወደ ደረታቸው የዘለቀች ጥይት መታቻቸው፡፡ አጃቢዎቻቸው ወደ ድንኳናቸው ወሰዷቸው፡፡ የአፄ ዮሃንስ መቁሰል ሲሰማ በኢትዮጵያኖች ዘንድ ድንጋጤ ተፈጠረ፡፡ የያዙትን ምሽግ እየለቀቁ መውጣት ጀመሩ በዚህ የተበረታታው ዛኪ ቱማል ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋገረ፡፡ የንጉሰ ነገስቱ መቁሰል መዘበራረቅ የፈጠረበት የኢትዮጵያ ሠራዊትም ወደ ኋላው አፈገፈገ፡፡ አፄ ዮሐንስ በመቁሰላቸው ምክንያት በማግስቱ መጋቢት 2፣ 1881 ዓ.ም አረፉ፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥር 16/2014