ተወልደው ያደጉት በገጠራማው የአገራችን ክፍል ነው። በተለይ ለሴቶችና ሕጻናት ፈታኝ በሆነው የገጠር ህይወት ተምረው ጥሩ ደረጃ ለመድረስ፣ ሰርቶ ስኬታማ ለመሆን መንገዶቹ አልጋ በአልጋ አልነበሩም። እርሳቸውም ቢሆን ይህንን እውነት ገና በጨቅላነት እድሜያቸው ነበር የተረዱት። ተምረው ጥሩ ደረጃ ለመድረስ ሕልማቸውን ለማሳካት በቀን አንድ ጊዜ ተመግበዋል። ፀሐይና ቁሩ ተፈራርቀውባቸዋል። በየቀኑ የአራት ሰዓት መንገድ በባዶ እግሩ ተጉዘው በመማር ትምህርታቸውን ተከታትለው 12ኛ ክፍልን አጠናቀዋል። የልጅነት ሕልማቸው ሰምሮላቸው ለውጭ አገር የትምህርት እድል የሚያበቃ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ውጤት በማምጣትም ወደ ውጭ አገር አቅንተዋል።
ለትምህርት በሄዱበት አገር ከትምህርቱ ጎን ለጎን በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተው ለስኬታማ ደረጃ የሚያደርሳቸውን መንገድ በተለየ የሥራ ትጋት ለመፍጠር ችለው ነበር። ስኬትን ቀድሞ በማለም ነገውን አሻግሮ በመመልከት፤ ከሚሠራው ሥራ ባሻገር ለዕውቀት ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ያለማንም ደጋፊ ተምረው ዛሬ ለደረሱበት ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል። በዚህም የበርካታ እውቀቶች ባለቤት መሆን ችለዋል።
በውጭ አገር በቀሰሙት እውቀት እና ባካበቱት ሀብት ሳይማር ያስተማራቸውን ማኅበረሰብ አቅም በፈቀደ ለመደገፍ እና እሳቸው ባለፉበት ፈታኝ መንገድ ሌሎች እንዳያልፉ ለማድረግ በአገር ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጸው እየሠሩ ናቸው። እኝህ የባለ ራዕይ ምሳሌ ዶክተር ገዛኸኝ ወርዶፋ ይባላሉ።
የዛሬው የ‹‹ስኬት አምዳችን›› በራሳቸው ጥረትና ትጋት ብዙ ውጣውረዶችን አልፈው፤ዳገት ቁልቁለቱን አቆራርጦ ባካበተው ዕውቀትና አቅም ለታላቅ ደረጃ የበቁትን ዶክተር ገዛኸኝ ወርዶፋን የሕይወትና የስኬት መንገዶች ለትምህርት ይሆነን ዘንድ ልንዳስስ ወደናል ።
ዶክተር ገዛኸኝ ወርዶፋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አንድ ሚሊዮን የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ለገናና ለጥምቀት በዓላት ወደ እናት አገሩ እንዲገባ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት የእናት አገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው ከገቡ የዲያስፖራ እንግዶች መሐል አንዱ ናቸው። የተገናኘነው ለዲያስፖራው ማኅበረሰብ በተሰናዳ አንድ መርሐ ግብር ላይ ነው።
ዶክተር ገዛኸኝ ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ወለንጪቲ ከተማ ነው። ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል በእናትና አባታቸው የትውልድ ቀዬ በአቃቂ ወረዳ ወሊሶና ድረገታ ኦዳ ነቤ ገበሬ ማኅበር በተባለች ቦታ ተከታትለዋል። ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ደግሞ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድ እየተጓዙ በዱከም ከተማ በቀድሞው ደጃዝማች ፍቅረማርያም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ፀሐይና ቁር እየተፈራረቀባቸው በባዶ እግራቸው በቀን የአራት ሰዓት መንገድ እየተጓዙ በደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ በሚገኝው የቀድሞው ተናኜ ወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለው ጨርሰዋል።
በኢኮኖሚ ከዝቅተኛ ቤተሰብ በመወለዳቸው እና የቤተሰብ ቁጥራቸው ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ይከታተሉ በነበረበት ወቅት ጠዋት ቁርሳቸውን ቁራሽ እንጀራ ቀምሰው በእግራቸው የአራት ሰዓት መንገድ ተጉዘው፣ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ምሳና እራት ሳይበሉ ጦማቸውን የሚያድሩበት ጊዜ ይበዛ እንደነበር ያወሳሉ። ጠዋት አፋቸውን ሳይሽሩ ወደ ትምህርት ቤት የሚያመሩበት ቀናትም በርካታ ነበር። የትምህርት ቁሳቁስ (ደብተር፣ እስኪሪቢቶ፣ ወ.ዘ.ተ) በቅጡ እንደማይሟላላቸው ይናገራሉ።
ለችግር እጅ ሳይሰጡ፣ ከዓላማቸው ወደ ኋላ ሳይሉ ተምሮ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ሕልም ነበራቸው። በዚህም በገጠማቸው የኢኮኖሚ ፈተና ከትምህርት ገበታቸው ተሰናክለው እንዳይቀሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነው በትርፍ ጊዜያቸው ቅዳሜና እሁድ ከገጠር እንቁላል እየገዙ ከተማ እየዞሩ ይሸጡ ነበር። የኩራዝ
ጋዝም በየቤቱ እያዞሩ ይሸጡ እንደነበር ይናገራሉ። ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ይህን እየሠሩ በሚያገኙት ገቢ የመማሪያ ቁሳቁሳቸውን ቤተሰብ ሳያስቸግሩ በራሳቸው ያሟሉ ነበር። በጨለማ ውስጥ የሚታየውን የብርሃን ጭላንጭል ነገ ላይ ፈንጥቆ ለማየት በነበራቸው ጽኑ እምነት፤ በዚህ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ጨረሱ።
ዶክተር ገዛኸኝ ወደ ውጭ አገር ሄደው መማር የሚያስችላቸው የማትሪክ ውጤት አግኝተው እ.ኤ.አ በ1989 ወደ ሶቭየት ኅብረት ለትምህርት ያቀናሉ። በአገሪቱ ያለው የአፈር አጠባበቅና አያያዝ እንዲሁም የመስኖ ሥራ ደካማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ በቀሰሙት እውቀት የአገራቸውን ተፈጥሮ ሃብት ለመጠበቅ በማሰብ ለትምህርት ባቀኑበት አገር በሚገኝ የመስኖና የአፈር አያያዝ ኮሌጅ ገብተው ትምህርታቸውን መከታተሉን ቀጠሉ።
ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ዳር ሳያደርሱት በመሐል እ.ኤ.አ በ1991 ሶቭየት ኅብረት ትበታተናለች።ይህ አጋጣሚ ከተለያዩ የዓለም አገራት ወደ ሶቭየት ኅብረት አቅንተው በኮሌጁ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ወደ መጡበት እንዲመለሱ ያስገድዳል። ውሳኔውም ተግባራዊ ይደረጋል።
የትልቅ ሕልም ባለቤት የነበሩት ፣ በርትቶ በመሥራትና መማር ለውጥ ማምጣት እንደሚችል የሚያምኑት ዶክተር ገዛኸኝ፤ በቀሰሙት እውቀት አገራቸውንና ወገናቸውን የማገልገል ትልቅ ፍላጎት ስለነበራቸው ሌሎቹ ወደ መጡበት ሲመለሱ እሳቸው ወደ ሞስኮ አቀኑ።መንገዳቸው ያለምክንያት አልነበረም። ከሞስኮ ሁማኒተሪያል ስቴት ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያና የማስትሬት ዲግሪያቸውን በሰብዓዊ መብትና በሕግ ትምህርት ያዙ። በኋላም በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀበሉ።
ወደ ሞስኮ አቅንተው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ሕይወት አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ዶክተር ገዛኸኝ ያስታውሳሉ። ዶክትሬታቸውን እስኪጭኑ ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተቀጥረው ራሺያ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ዱቄት እየተሸከሙ፣ ከተለያዩ የዓለም አገራት ለሚመጡ ስደተኞች የማስተርጎምና ምግብ በማቅረብ በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን እየደጎሙ ነው ትምህርታቸውን የተማሩት።
ዶክተር ገዛኸኝ በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ከአፍጋኒስታን፣ ከየመን፣ ከሶሪያ እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ስደተኞችን ስቃይና እንግልት የማየት አጋጣሚው ነበራቸው። በዚህም ስደተኞችን ከደረሰባቸው የስነልቦና ስብራት ለመጠገንና ለመርዳት በስደተኞች ላይ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ በሳይኮሎጂ ዶክትሬታቸውን እንደያዙ ይናገራሉ። ዶክትሬታቸውን እንደያዙም ስደተኞችን ለመርዳት የነበራቸውን ሕልም ዕውን ለማድረግ “ኦፕራ/ Opra” (በራሺያኛ ኃይል ወይም ደጋፊ ማለት ነው) የተሰኘ በስደተኞች ላይ የሚሠራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ዩኤን) አጋር የሆነ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2000 ላይ ያቋቁማሉ።
ይህን በስደተኞች ላይ የሚሠራ ድርጅት መሥርተው የዩኤን አጋር ሆነው በዓለም ላይ የተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩ ስደተኞችን በመርዳት ሥራ ላይ ይቆያሉ። በዚህም ተግባር ታዋቂ ለመሆን መብቃታቸውን ይናገራሉ። ድርጅታቸው በሞስኮ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ቀደም ሲል ያልነበሩ (የምግብ ማብሰያ ኪችን፣ የምግብ ባንክ ወ.ዘ.ተ) የተለያዩ ዘመናዊና አዳዲስ አገልግሎቶችን በማስጀመራቸው ስመጥር ለመሆን መብቃታቸውን ይናገራሉ። በዚህም መነሻ ገቢያቸው እያደገና ኑሯቸው እየተደላደለ ሄዷል።
የእንጀራና የሕይወት ጉዳይ ሆኖባቸው አካላቸው ከእናት አገራቸው ቢርቅም፤ መንፈሳቸው ሁሌም ከኢትዮጵያ የማይለየው ዶክተር ገዛኸኝ፤ በሥራቸውና በትምህርታቸው ስኬት ማግስት ሳይማር ያስተማራቸውን ወገናቸውን ለመጎብኘት በ2005 ዓ.ም ከባለቤታቸው ጋር ወደ እናት አገራቸው መጡ ። ለኦዳ ነቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት 10 ኮምፒውተሮችን በማበርከትም ድጋፋቸውን “ሀ” ብለው ይጀምራሉ።
የወገናቸውን ድጋፍ አጠናክረው የቀጠሉት እኚህ ስኬታማ ሰው፤ በኦዳ ነቤ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር “ኦዳ ነቤ” የተሰኝ ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ገንብተው አስረክበዋል። ቤተ መጽሐፍቱ ለአምስት ሺህ ሰዎችን ግልጋሎት ይሰጣል። በተመሳሳይ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ለሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችና ተማሪዎቻቸው አስተዋጽኦ ያበረክታል። የአካባቢውን ኅብረተሰብ የማንበብ ባህል ለማሳደግና መጽሐፍት ፍለጋ ከሁለት ሰዓት በላይ ለሚጓዙ ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ቅዳሜና እሁድ ጭምር ያገለግላል።
ዶክተር ገዛኸኝ ልጅ ሳሉ በአካባቢያቸው ሕክምና አልነበረም። እናታቸው ከሶስት ሰዓት በላይ በሚያስኬድ የእግር መንገድ በቃሬዛ ተጋጉዘው ይወልዱ እንደነበር አይዘነጉም። ይህን እውነታ አሳምረው ስለሚያውቁ ዛሬም በሕክምና እጦት እናቶች ሕይወታቸውን እንዳያጡ በማሰብ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በትውልድ ቀያቸው ጤና ኬላ እየገነቡ ነው። አሁን ጤና ኬላው ወደ መጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅም በስምንት ገበሬ ማኅበራት ለሚገኙ ነዋሪዎች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው።ጤና ጣቢያው የተሟላ ቤተሙከራ ተገንብቶለታል። የማዋለድ፣ የድንገተኛ ሕክምና እርዳታ እና የተለያዩ ሕክምናዎች ይሰጥበታል። ጤና ኬላው ሲጠናቀቅ ለመውለድ ሁለትና ሶስት ሰዓት የእግር መንገድን በቃሬዛ ይጓጓዙ ለነበሩ እናቶች ታላቅ ተስፋ ሆኗል።ነዋሪው ከቀዬ መንደሩ ሳይርቅና ሳይንገላታ ሕክምና እንዲያገኝና የነበረ ታሪክ እንዲቀየር ያግዛል።
ስኬታማው ሰው በቀላሉ ሠርተው ትርፍ የሚያገኙበት ቢዝነስ ላይ ለመሠማራት ልባቸው አልፈቀደም። በአገሪቱ ካለው ዝቅተኛ የጤና አገልግሎት አኳያ የበኩላቸውን ለማበርከትና የወገናቸውን ችግር ለመጋራት በሆስፒታል ኢንቨስትመንት ላይ ፊታቸውን አዙረዋል።አሁን በዱከም እና በቢሾፍቱ ከተሞች መካከል በምትገኝ ‹‹ጠሌቻ›› በምትባል የገጠር መንደር በ28 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሆስፒታል ለመገንባት ቦታ ተረክበው ወደ ሥራ ገብተዋል። ለሆስፒታሉ ግንባታ እስከ 300 ሚሊዮን ብር ካፒታል መድበዋል ። ሆስፒታሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅም የጤና ኮሌጅ፣ ባንክ፣ ሱፐር ማርኬት፣ መድኃኒት ቤት፣ የእናቶችና ሕጻናት ልዩ ሕክምና የሚሰጥበት ክፍል ይኖረዋል። መንግሥት ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚሆን ቦታ ማመቻቸቱን ተከትሎ ለግንባታውና ለሕክምና ሥራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እየገቡ ነው። ግንባታውም በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።
“ሆስፒታሉ ትርፍን ብቻ ማዕከል ሳያደርግ ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የሚቋቋም ነው” የሚሉት ዶክተር ገዛኸኝ፤ ሆስፒታሉ ወደ ሥራ ሲገባ ለአቅመ ደካሞች፣አካል ጉዳተኞች እና ጉዳት የደረሰባቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በነጻ ሕክምና ለመስጠት እቅድ ያለው ነው ። ዶክተር ገዛኸኝ ለሰፊው የኅብረተሰብ ክፍል አገልግሎት በሚሰጥ ፕሮጀክት ላይ በመሠማራታቸው ዕድለኝነታቸውን ይገልጻሉ። ለዚህ አጋጣሚ እግዚአብሔር እንዳደላቸው ሲያስቡም ደስተኝነታቸውን አይሸሽጉም።
እኚህ ሰው በግል ጥረትና ትጋታቸው ከሚፈልጉት የሕይወት ማማ ላይ ለመድረስ ችለዋል። ገና በለጋ እድሜያቸው አርቀው ያለሙትን ሕልም ዕውን አድርገዋል። እደርስበታለሁ ካሉት የስኬት መዳረሻ ለመቆም መንገዶች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም። ይሁን እንጂ የኑሮን ተራራ ለመውጣት፣የሕይወት ውጣውረድን ለማሸነፍ አእምሯቸው ብሩህ ነበር ።እጆቻቸው ከመስጠት አልፈው ለሥራ መበርታታቸው የዛሬውን መልካም ፍሬ እንዲያፍሱ መነሻ ሆነዋል።
እነሆ ! ዛሬ የተጋ ማንነት ሥራ ሆኖ መስክሯል።የትናንት ጥረትና ልፋትም ለበርካቶች ቱርፋት ሆኖ በረከቱ መፍሰስ ጀምሯል። ልፋትና ድካም ውጤት ሲይዝ፣ በስኬት ሲገለጥ ያስደስታል።ይህ እውነት ለአገርና ወገን ጠቀሜታ ሲውል ደግሞ ድል አድራጊነቱን እጥፍ ያደርገዋል።ዶክተር ገዛኸኝ ከራሳቸው ወገን አልፈው በሌላው ዓለም ለሚገኙ ስደተኞች ጭምር ረዳትና አለኝታ መሆን ችለዋል። የዛሬው የስኬት እንግዳችን ተምሮ መለወጥን፣ ሠርቶ ማሳካትን አሳይተውናል ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2014