አትክልትን አዘውትሮ መመገብ ለጤናችን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ይሰጠናል። የምግብ አፈጫጨትን ቀላል ለማድረግ እና የደም ግፊትን ለመቆጣጠር መርዳታቸው ከሚሰጡን የጤና ጥቅሞች በዋናነት ይጠቀሳሉ። አትክልቶች በውስጣቸው በያዙት ከፍተኛ የአንቲኦክሳይዳንት መጠን እንደ ካንሰር፣ ስትሮክ እና የካርዲዮቫስኩለር ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዱናል። የያዙት የአንቲኦክሳይዳንት ንጥረ ነገር እና የአነስተኛ ካሎሪ መጠን የልብ ህመምን እና የስኳር በሽታን ይከላከሉልናል።
አትክልቶች በውስጣቸው በያዙት ቫይታሚን A፣ ቫይታሚን K፣ ፎሌት እና ቫይታሚን B6 በሽታን የመከላከል አቅም አላቸው። አትክልት አዘውትረን በመመገባችን በሚይዙት አነስተኛ የካሎሪ መጠን ውፍረታችንን መቀነስ እንችላለን። የተስተካከለ እና ጤናማ የሰውነት አቋም እንዲኖረንም ያስችሉናል።
ከበርካታ ለጤና ተስማሚ ከሆኑ የአትክልት አይነቶች መካከል ለዛሬ አራቱን ማለትም ቃሪያ፣ ሎሚ፣ ቀይ ሽንኩርትንና ድንችን እንመልከት።
ቃርያ፦ የቫይታሚን ኤ ንጥረ ነገርን በውስጡ ይዟል። በመሆኑም ለዓይን ጥራት እና ጤናማነት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። በቫይታሚን ሲ እጅግ የበለጸገ በመሆኑ ቆዳችንን ጤናማና የሚያበራ እንዲሆን ያስችላል።
በተጨማሪም የምግብ መፈጨት ሂደትን ያፋጥናል። ለአጥንት ጤናማነት እና ጥንካሬ እጅግ ጠቃሚ ሲሆን ለሰውነታችን ጠቃሚ ያልሆኑ ንጥረ ነገሮችን በማስወገድ እና የፋይበር ምንጭ በመሆን የሆድ ድርቀትን፣ ጉንፋን፣ ሳልና የሣንባ ካንሰርን ይከላከልልናል። በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳብራል። ቃርያን በመመገባችን የቆዳ መሸብሸብ አይገጥመንምና ቶሎ አናረጅም።
ሎሚ፦ ጸረ-ባክቴሪያ ባህሪ ያለው ሲሆን በቫይታሚን ሲ የበለጸገም ነው። የሎሚ ጭማቂን በውሃ ቀላቅሎ መጠጣት ሰውነታችን የአሲድ አልካላይን ሚዛኑን ለመጠበቅ ያግዘዋል። በተጨማሪም የጉበትን ሥራ በማነቃቃት ዩሪክ አሲድና ሌሎችንም ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ከሰውነታችን ውስጥ ለማስወገድና የሀሞት ፈሳሽንም የፈሳሽነት ባህሪውን እንዳያጣ የማድረግ ጥቅሞችን ይሰጠናል።
የሎሚ ጭማቂ በቫይታሚን ፒ የበለጸገ እንደመሆኑ በህዋሳት መጎዳትና በዕድሜ መጨመር ሳቢያ የሚከሰቱትን ፍሪ ራዲካሎችን ለማስወገድ ይረዳናል። የሎሚ ጭማቂ ፀረ-ካንሰር ባህርያት ሲኖሩት ከዕድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የመገጣጠሚያ አካላት በሽታን በመከላከል ረገድም ዓይነተኛ መፍትሄ ይሆነናል። በሎሚ ውስጥ ያለው ፔክቲን ፋይበር የመጥፎውን ኮሌስትሮል መጠን ከመቀነሱም በላይ የመጥገብ ስሜትን ስለሚፈጥር በብዛት ከመመገብ ያግዳል።
ቀይ ሽንኩርት፦ በውስጡ ክሩሚየም የተባለ ንጥረ ነገር ሲኖረው ንጥረ ነገሩ የደም ግፊትንና ስኳርን ይቆጣጠርልናል። ገላን የማሳከክና የማቃጠል ዓይነት ባህሪ ያላቸውን አለርጂዎች በመቆጣጠሩ ረገድ አስተዋጽዖው የጎላ ነው። በተለይ ንብ ሲነድፈን ትንሽ የቀይ ሽንኩርት መቀባት ከስቃይ ይታደገናል። በውስጡ የሚገኘው ክዩርስቲን የተሰኘው ንጥረ ነገር ደግሞ ካንሰርን የመከላከል ሚና ይጫወታል። ሰውነትን ከበሽታ የመከላከል አቅምን ያሳድጋል። ቀይ ሽንኩርት ጥሬውን መመገብ ኮሌስትሮልን ከመቆጣጠሩ ባሻገር የጤናማ ልብ ባለቤት ያደርጋል። ቀይ ሽንኩርትን በየዕለቱ መመገብ ከጨጓራ አልሰርም ይጠብቀናል።
ድንች፦ ውፍረትን የሚያመጣ ቢሆንም ለጨጓራ ህመም ፈውስ ነው። ለደም ግፊት፣ ለካንሰር፣ ለኩላሊት፣ ለራስ ምታትና ለሌሎችም በሽታዎች መድኃኒትነት አለው። በተጨማሪም የድንች ጭማቂ በተፈጥሮ በሽታ የመከላከል አቅምን ለማሻሻል፣ በየጊዜው የሚከሰትን የራስ ምታት ህመምና የወር አበባን ተከትሎ የሚከሰቱ ህመሞችን ለማስታገስ ይረዳል።
ምንጭ፡- ጠቅላላ እውቀት ማዕድ
ሠላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2014