ሰሞኑን በኢትዮጵያ የተከሰተው ለየት ያለ ጉንፋን በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። በርካታ ሰዎችም በዚህ ጉንፋን መያዛቸውንና ተመሳሳይ ምልክቶች እንደታዩባቸው ሲያወሩ ተደምጠዋል። የዚህ አዲስ ጉንፋን ዋነኛ ምልክቶች እንደ የንፍጥ መዝረብረብ፣ የመገጣጠሚያ ህመም፣ ትኩሳትና ራስ ምታት እንደነበሩም በጉንፋኑ (ቫይረሱ) ከተጠቁ ሰዎች ለማረጋገጥ ተችሏል።
የብዙዎች ጥያቄ ግን ይህ አዲስ ጉንፋን ምን አልባት በአለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተውና ‹‹ኦሚክሮን›› ከተሰኘው አዲስ የኮቪድ-19 ዝርያ ጋር የተመሳሰለ ወይም ራሱ እንዳይሆን ነበር። ይሁንና የጤና ሚንስቴር ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኮቪድ-19 ስርጭት ከፍ ማለቱንና ምን አልባትም ኢትዮጵያ በአራተኛ ዙር የኮቪድ-19 ማዕበል ውስጥ ሳትሆን እንዳልቀረች ተናግሯል። ‹‹ኦሚክሮን›› የተሰኘው አዲሱ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ በኢትዮጵያ ስለመከሰቱ ግን አስካሁን በምርመራ እንዳልተረጋገጠ አያይዞ ገልጿል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ፤ በተለየ ሁኔታ የተከሰተ አዲስ ጉንፋን በሚል ኅብረተሰቡ እንዳይዘናጋና ከዚህ ይልቅ አገሪቱ አራተኛ ዙር የኮቪድ-19 ማዕበል ውስጥ መሆኗንና የወረርሽኙ ስርጭት እየጨመረ መሆኑን ተገንዝቦ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ አሳስቧል።
በጤና ሚንስቴር የብሄራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዮሃንስ ላቀው እንደሚሉት በኢትዮጵያ ከሰሞኑ ተከስቶ የነበረው ጉንፋን ‹‹ኦሚክሮን›› ስለ መሆኑ በቀጣይ በምርመራ የሚረጋገጥ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ግዜ በአገሪቱ የኮቪድ-19 ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ወደ ጤና ተቋማት ሄደው ምርመራ የሚያደርጉ አብዛኞቹ ሰዎችም በኮቪድ-19 መያዛቸው እየተረጋገጠ ነው። በዚህም በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፤ በዚሁ ቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም አሻቅቧል።
በምርመራ ወቅት በኮቪድ-19 የመያዝ ምጣኔም /positivity rate/ ወደ 50 ተጠግቷል። ይህም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደ አዲስ ማገረሸቱንና ኢትዮጵያም በአራተኛው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕበል ውስጥ እንደምትገኝ ያሳያል።
ይሁንና ‹‹ኦሚክሮን›› የተሰኘው አዲሱ የኮቪድ-19 ቫይረስ በኢትዮጵያ ስለመከሰቱ እስካሁን በምርመራ አልተረጋገጠም። ቫይረሱ በትክክል በኢትዮጵያ ስለመከሰቱ ለማረጋገጥም የራሱ የሆነ የምርመራ ሂደትና አዳዲስ የምርመራ ኪቶች ያስፈልጋሉ። ሂደቱን ጠብቆ ግን በቀጣይ ቫይረሱ በኢትዮጵያ እንዳለና እንደሌለ ይፋ ይደረጋል።
እንደ አስተባባሪው ገለፃ የኮቪድ-19 በሽታ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሊመጣ የቻለው የቫይረሱን ስርጭት ማቆም ስላልተቻለ ነው። የበሽታው ስርጭት በቀጠለ ቁጥር ደግሞ የቫይረሱ ተጋላጭ ሰዎች ቁጥርም ይጨምራል። የክትባት ሽፋኑ ዝቅተኛ መሆንም የቫይረሱ ስርጭት መጠን ከፍ እያለ እንዲሄድ አድርጓል።
ከክትባቱ ጋር የተያያዙ አንዳንድ የተዛቡ ግንዛቤዎችም የክትባቱ ሽፋን በተፈለገው ልክ እንዳያድግ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። የክትባቱ ሽፋን ቢያድግና ሰዎችም ራሳቸውን ከኮቪድ-19 እየተከላከሉም ቢሆን የበሽታው ስርጭት እስካልቆመ ድረስ ‹‹ኦሚክሮን››ና ሌሎች አዳዲስ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያዎች የሚከሰቱበት እድል ሰፊ ነው።
ከዚህ አንፃር ከ60 አስከ 70 የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ክትባቱን ወስዶ በሽታ የመከላከል አቅሙን በመገንባት በሽታውንና የበሽታውን ስርጭት ማቆም ካልተቻለ አሁን ከሚታዩት የከፉ አዳዲስ የኮቪድ-19 ዝርያዎች ሊታዩ ይችላሉ። በዚህም ልክ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ክትባቱን እንዲወስድ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
አስተባባሪው እንደሚሉት እንደማኅበረሰብ በሽታውን የመከላከል አቅም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ክትባት የወሰደው ሰው ቁጥርም ገና ከ10 ሚሊዮን አልተሻገረም። ይህ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከሚኖርበት አገር ጋር ሲወዳደር በጣም ጥቂት ነው። ከዚህ አንፃር በሽታው አሁንም የስርጭት መጠኑ እያደገ ሄዶ አዳዲስ ዝርያዎችን ሊፈጥር ይችላል።
ይኼው አዲስ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ ደግሞ የራሱ የሆነ የተለየ ባህርይ ይዞ ይመጣል። ምንአልባትም በጣም ገዳይና ተላላፊ የሚሆንበት ዕድልም ሊፈጠር ይችላል። ከመጀመሪያው የኮቪድ-19 ክስተት ጀምሮ እስካሁን ያለው ሂደት ሲታይ የተለያዩ የኮቪድ-19 ቫይረስ አይነቶች ታይተዋል።
በሽታው ሊሰራጭ የሚችለው የመከላከል አቅም ሳይኖር ሲቀር በመሆኑና የመከላከል አቅምን ሊገነባ የሚችለው ደግሞ አንዱ ክትባት በመሆኑ የበሽታውን ተጋላጭነት በመቀነስ ስርጭቱን ለመግታት እያንዳንዱ ሰው ክትባት መውሰድ ይጠበቅበታል።
ይሁንና በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ሽፋን ከፍ ሊል አልቻለም። አንዳንዶች ክትባቱን ከሃይማኖት ጋር ሌሎች ደግሞ ከፖለቲካ ጋር ያያይዙታል። የክትባቱን የጎንዮሽ ጉዳት በመፍራትም ላለመከተብ የወሰኑ አሉ። ከሌሎች ጉዳዮች ጋርም ክትባቱን በማገናኘት ኅብረተሰቡ ስለክትባቱ ያለውን ግንዛቤ ለማዛባት በርካታ የተዛቡ መረጃዎች ወጥተዋል።
እነዚሁ መረጃዎች በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ኅብረተሰቡ ክትባቱን እንዳይወስድ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ሌሎች የአለም አቀፍ የክትባት እጥረቶችም ለክትባቱ ሽፋን አለመደግ የድርሻቸውን ተወጥተዋል። ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀርም የክትባት ሽፋኑ በእጅጉ አነስተኛ መሆኑ ተረጋግጧል። አስካሁን ባለው ሂደትም መከተብ የተቻለው 10 ከመቶ ያህሉን ሕዝብ ብቻ ነው።
ከክትባቱ ጋር በተገናኘ የተዛቡ መረጃዎችን ለማስተካከልና ኅብረተሰቡ ስለክትባቱ ትክክለኛ ግንዛቤ ኖሮት ክትባቱን እንዲወስድ ለማድረግ በጤና ሚንስቴር በኩል ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። የባህርይ ለውጥ በአንድ ግዜ የሚመጣ ባለመሆኑ ኅብረተሰቡን አሳምኖ ክትባቱን እንዲወስድ ለማድረግ ትንሽ ግዜ ይፈልጋል።
ይሁንና ከበፊቱ የተሻለ ለውጥ አለ። ባለፈው በዘመቻ መልክ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ መደረጉም አንዱ የለውጡ ማሳያ ነው። አሁንም ከዚህ የበለጠ ሰው በዘመቻ ለመከተብ እቅድ ተይዟል።
በዚህ አመት ክትባቱን በስፋት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት እቅድ የተያዘ ሲሆን በቅርቡ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ የክትባት ዘመቻ ስለሚደረግ ከወዲሁ ዝግጅት እየተካሄደይገኛል።
አስተባባሪው እንደሚገልፁት የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶች የመከላከል አቅማቸው ጥሩ እንደሆነ በሌሎች አገራት ታይቷል። ሰዎች በኮቪድ-19 ቢያዙ እንኳን በበሽታው የመሰቃየት እድላቸውን ይቀነሳል። ይህም በተዘዋዋሪ በበሽታው ምክንያት የሚከሰተውን ሞት ይቀንሳል።
ከዚህ ውጪ ግን ክትባቱን ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የሚያገናኘው ምንም ምክንያት የለም። እንደጤና ባለሞያም ጉዳዩ ሚዛን የሚያነሳ አይደለም። ይህንንም ኅብረተሰቡ ሊገነዘብ ይገባል። የክትባቱን የጎንዮሽ ጉዳት ፈርተው ላለመከተብ የወሰኑ ሰዎችም ክትባቱ የከፋ የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው ተረድተው ክትባቱን መውሰድ ይኖርባቸዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ኅብረተሰቡ ቀደም ሲል ሲተገብራቸው የቆዩና አሁን ደግሞ የዘነጋቸውን እንደ ማስክ ማድርግ፣ እጅን በንፁህ ውሃና ሳሙና መታጠብና ርቀትን መጠበቅ የመሳሰሉ የኮቪድ መከላከያ መንገዶችን እለት በእለት መተግበር ይጠበቅበታል።
መደበኛውን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን ሙሉ በሙሉ የወሰዱና ስድስት ወር የሞላቸው ሰዎች ደግሞ በሽታ የመከላከል አቅማቸውን ይበልጥ ለማጎልበት ተጨማሪ ክትባት /booster dose/ በየጤና ጣቢያዎች በመቅረብ መከተብ ይችላሉ። ይህም ‹‹ኦሚክሮን››ን ጨምሮ አዳዲስ የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ያግዛል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2014