አልጋዋ ላይ ሆና ወደ መስኮቱ ታያለች፤ መስኮቱ ተስፋ ለራቃት ነፍሷ ብዙ ነገሯ ነው። የአዕዋፋቱን ዜማ፣ የደስተኞችን ሳቅ ያመጣላታል። የእጽዋቱን ሽታ፣ የቤተክርስቲያኑን ደወል፣ የአዛኑን ድምጽ ያሰማታል።
አቅም ቢኖራት የምትመልሳቸው ብዙ ትናንቶች አሏት። ኃይል ቢኖራት ወደ ኋላ ተመልሳ የምታስተካክለው አምና ነበራት።
ሊያ ትባላለች፤ ካንሰር አለብሽ ተብላ ሆስፒታል ከገባች ወራት ተቆጥረዋል። ሆስፒታል አካሄዷ ለቀላል ሕክምና ነበር፤ የምርመራ ውጤቷ ግን የሕክምና ጊዜው ያለፈ ካንሰር እንዳለባት ነገራት።
ዶክተሩ ቀረባት፤ እንዲህ ቆይቶ አያውቅም ነበር። ወደ መስኮቱ ተራመደች፤ መስኮቱ ጋ ስትቆም መጀመሪያ የሚሰማት ቅናት ነው። ከታች ያሉ ደስተኛ ነፍሶች ሲስቁ ስታይ፣ ሲያውካኩ ስትሰማ በመኖራቸው ትቀናለች። ሰው ነገ ከሌለው ዋጋው ምንድነው? የሕይወት ተስፋ እኮ የነገ ዋጋ ነው፣ የቆምነው በነገ ተስፋ ነው። የእሷ ተስፋ ዛሬ ብቻ ነው፤ ከመስኮቱ ባሻገር የምታያቸው ሰዎች ነገ አላቸው፤ በነገ ተስፋ የሚቦርቁ ናቸው። ቀናችባቸው።
እሷ ነገ የላትም፤ ከዛሬ ሌላ ቀን የላትም፤ ይሄን ስታስብ መኖር ትርጉሙ ይጠፋታል። ያላትን ቆጠረችው፤ በሕይወቷ ፈልጋ ያጣችው አንድም ነገር የለም። ዙሪያዋ በብዙ ነገር እድል የቀረባት ነበረች፤ ዛሬ ግን ሞቷን እየጠበቀች ሆስፒታል ውስጥ ትገኛለች።
ቤት፣ መኪናና ብዙ ውድ ነገሮች አሏት፣ ባንክ ብዙ ብር አላት፤ እነዚህ ሁሉ ግን ሕይወት አልሰጧትም። የሰው ልጅ ይገርማታል፤ የሚበጀው እያለ ለማይበጀው
የሚደክም ነው። ገንዘብን የሕይወት ጥያቄ ያደረጉ ብዙ ሰዎችን ታውቃለች። እሷም ራሷ ለገንዘብ የተፈጠረች እስኪመስላት ድረስ ገንዘብ ለማግኘት ብዙ ባክናለች፤ እነዛ ሁሉ ብርና ወርቆች ግን ዛሬ ከሆስፒታል አልጋ ላይ አላስነሷትም። ጤና ከገንዘብ በላይ እንደሆነ የገባት ሆስፒታል ገብታ ነው። ገንዘብ ምንም እንዳይደለ የተረዳችው ከአልጋ ላይ እንዳላስነሳት ስታውቅ ነው።
ጤናዋን መመለስ ብትችል ኖሮ ያላትን ሁሉ ገንዘብ ትከፍል ነበር ፤ግን ገንዘቧ ፊት ለፊቷ ከተፈጣጠችው ሞት አልታደጋትም። የቱጋ ስህተት እንደሠራች እርግጠኛ አይደለችም፤ አሁን ግን ከጤናዋ በላይ ገንዘብን መውደዷ ግን ልክ እንዳይደለ ደርሳበታለች። ድጋሚ በሕይወት ብትኖር፣ ከሞት የመዳን እድል ቢኖራት ኖሮ አሁን ከሆነችው ሌላ ትሆን ነበር.፤ በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ስትከተል ትኖር ነበር።
ገንዘብ ለማግኘት የሮጠችባቸውን ጎዳናዎች ለጤናዋ ሄዳባቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ሆስፒታል ውስጥ አትገኝም። የሰው ልጅ የሚሞተው ራሱ ነው። ፈጣሪ የሰውን ልጅ ገሎ አያውቅም። ሞትና ሕይወት በሰው ልጅ እጅ ውስጥ ናቸው።
ሞት በአዳምና ሄዋን ስህተት ወደ ዓለም እንደመጣ ሁሉ ዛሬም ድረስ እየሞትን ያለንው በእኛ ስህተት ነው። በገንዘቦቻችን ሞትን የምንገዛ ብዙዎች ነን። ሲጋራ ጤናን ይጎዳል የሚል ጽሑፍ እያነበብን የምናጨስ፣ መጠጣት ለጤና ጠንቅ እንደሆነ እያወቅን የምንጠጣ እንዲህ ነን መስኮቱ አጠገብ ቆማ ብዙ አሰበች። የተኛችበት ክፍል ሲቆረቆር ከሀሳቧ ወጣች። ዶክተሩ እንደሆነ አውቃለች። ዶክተሩ ገና እንደገባ ‹በጣም ይቅርታ የሆነ ነገር ተፈጥሯል› አላት። ‹ምን ተፈጠረ? ግዴለሽ፤ መልሳ ጠየቀችው። ‹እንዴት እንደምነግርሽ አላውቅም።
‹ነገ ልትሞት የዛሬ ንጋት ብርቅ ለሆነባት ሴት እንዴትም ብትነግራት ግድ አይሰጣትም፤ እንደፈለከው ንገረኝ..› አልዞረችም..ፊቷ ከታች መንደር ከምታያቸው ሰዎች ላይ ነው።
‹የምሰሚው ነገር እንደሚያስቆጣሽ አውቃለሁ፤ ይቅርታ እንደምታደርጊልኝ ቃል ግቢልኝ› አይኖቹን ጀርባዋ ላይ ተክሎ ተማጸናት። ‹ከሞት ጋር ቀጠሮ የያዘች ሴት አይደለም፤ ላልበደሏት ለበደሏት የሚሆን ብዙ ይቅርታ አላት። አታስብ እንዴትም ብታስቀይመኝ ይቅርታ አደርግልሀለሁ። ‹አይመስለኝም›› አላት። ‹እያስጨነከኝ ነው ዶክተር፤ ልቤ ቂምን የምታደምጥበት ጊዜ ላይ አይደለሁም። ከፈጣሪ ጋር ስገናኝ ኩነኔ ከሌለባት ነፍሴ ጋር ነው እንዲሆን ለራሴ ቃል ገብቻለሁ፤ ለየትኛውም ምድራዊ በደል የሚሆን ይቅርታ አለኝ፤ ይልቅ ንገረኝ ምንድነው? ‹የሆነ ስህተት ተፈጥሯል። ‹የምን ስህተት? ዶክተሩ ረጅም ዝምታ ዝም አለ።
‹ሁሉም ነገር እንደነገርኩህ ነው፤ ልትሞት ቀን የቀራት ነፍስ ምንም ብርቅ ነገር የላትም። ምንም ነገር ብትነግረኝ ብርቄ አይደለም እያልኩህ ነው። በአሁኑ ሰዓት የነፍሴ ብርቅ ነገር መኖር ብቻ ነው.፤ የኔ ነፍስ በአሁኑ ሰዓት የሚያስደስታት ነገር ቢኖር ከሞት የምትድንበትን ዜና መስማት ብቻ ነው ፤ ያ ደግሞ አይሆንም። ‹ሆኗል…› ዶክተሩ ተናገረ። ወደ ኋላዋ ዞረች። ‹ምን እያልክ ነው? ‹አንቺ ጤነኛ ሴት ነሽ ፤ ውጤቱም በተመሳሳይ ስም በስህተት የተፈጠረ ነው› ፊቷ ላይ አቀረቀረ የሆነ ነገር የሰማች ይመስላታል፤ አጠገቧ የሚያወራ የሙያ ልብስ የለበሰ ዶክተር ቆሟል።
‹ሆኗል…› ዶክተሩ ተናገረ። ወደ ኋላዋ ዞረች። ‹ምን እያልክ ነው? ‹አንቺ ጤነኛ ሴት ነሽ ፤ ውጤቱም በተመሳሳይ ስም በስህተት የተፈጠረ ነው› ፊቷ ላይ አቀረቀረ የሆነ ነገር የሰማች ይመስላታል፤ አጠገቧ የሚያወራ የሙያ ልብስ የለበሰ ዶክተር ቆሟል።
እጆቹ ላይ ነጭ ወረቀት የያዘ። ባቀረቀረበት ሆኖ ‹በሌላ ሰው ውጤት ነው እስካሁን ሆስፒታል የቆየሽው። ልትከሺኝ ትችያለሽ፣ ከሥራዬ ልታስባርሪኝም ሙሉ መብት አለሽ፣ የሆነውን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ› አላት።
ለዚህ ዶክተር የሚሆን ይቅርታ ይኖራት ይሆን? በነፍሷ ውስጥ ኮሽታ ተሰማት፤ ከልቧ ጽላት ስር የሙሴን ሕግ አገኘችው። ከሰማየ ሰማያት መጠቀች። ከእንግዲህ ባለው ምንም ክፉ ነገር የማድረግ አቅም የላትም።
ለዚህ ሰው ይቅርታ በማድረግ ሕይወትን ትጀምራለች። ታማ ሳለች፣ መስኮቱ አጠገብ ቆማ ሳለች፣ ዳግም በሕይወት ብኖር ብላ ተመኝታ ሳለች ያሰበችው ሀሳብ አለ..በዛ ሀሳብ ውስጥ ለበደሏት ሁሉ ይቅርታ እያደረገች ትኖራለች።
ብዙ ሰዎች ከመኖር ወደ አለመኖር ይወስዱናል፣ ብዙ ሰዎች ካለመኖር ወደ መኖር ያመጡናል በዚህ ዶክተር ብዙ ነገር ሆናለች። የምትገባበት ቤት እንኳን የላትም። እዛው ሆስፒታል እያለች ቤት ንብረቷን ሁሉ ለድሀ ሰጥታለች።
አካውንቷ ውስጥ ያለውን ሚሊዮን ገንዘብ ለእርዳታ ለግሳለች። ከፈጣሪ ጋር በደግነት ለመገናኘት ስትል ድሀ ሆናለች።
አሁን ምንም የላት፤ ወዴት እንደምትሄድ እንኳን አታውቀውም። ለመልካም ነፍስ የሚሆን ሥራ እንደማታጣ ግን እርግጠኛ ነበረች። ዓለም ላይ የድሀ ድሀ ሆና ከሆስፒታል ወጣች፤ ሁሉን ለነጠቃት ዶክተር ይቅርታ በማድረግ ሕይወትን ከምንም ጀመረች።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 13/2014