ከወትሮው በአንድነቱ እና ራሱን ችሎ ለመቆም በሚያደርገው ትግል ለሌሎች አርአያ መሆን የቻለው «ኀርየነ – ነጻነት የሸማቾች ማህበር» ከሰሞኑ ከሚዛን ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ችግር በሸማቾች ማኅበር አባላት መካከል ትልቅ ውዝግብ አስነስቶ ሲያጨቃጭቅ ሰንብቷል፡፡
ይህን ተከትሎ የማኅበራችን ሊቀመንበር የንታ ፍሬው የማህበሩን አባላት ሰብስበው ሚዛኑ ለውዝግቡ መነሻ እንዴት ሊሆን እንደቻለ አባላቱን ጠየቁ፡፡ ከማኅበራችን አባል አንዱ የሆነው አቶ ፍቅሩ ቢያዝን ስለጉዳዩ ለማስረዳት የንታ ፍሬው እድል እንዲሰጡት በማሰብ እጁን ወደላይ አነሳ ፡፡
የመናገር እድልም ተሰጠው፡፡ ጉሮሮውን ሞረድ ሞረድ አድርጎ ንግግሩን ቀጠለ ፤ በማኅበራችን የሚመጡ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚያከፋፍለን ባለወፍጮ ቤቱ አቶ ታገለ ነጻነት ነበር፡፡ አቶ ታገለን አምነነው ለማህበራችን የሚመጡ ማናቸውንም አይነት ሸቀጣ ሸቀጥ እንዲያከፋፍለን ብንመርጠውም ማኅበሩ ከተቋቋመለት ዓላማ ውጭ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ይህ ደግሞ ከማኅበራችን ውጭ ሆነው ማኅበሩን የደገፉ አካላትን ጭምር ያስቆጣ ተግባር ነው ፡፡ ዘርዘር አድርጌ ለማብራራት ያህል የወፍጮ ቤቱ ባለቤት በሰፈራችን የሚገኘውን የኅብረት ስራ ማኅበር ስኳር፣ ዘይት ፣ ሳሙና እና መሰል በማኅበራችን የሚመጡ ሸቀጣ ሸቀጦችን አከፋፋይ ናቸው ፡፡ እኝህ ሰው በተለይ ስኳር በሚያከፋፍሉ ሰዓት ለአባላቱ የሚከፋፈለውን ስኳር የሚመዝኑት በወፍጮ ቤቱ ሚዛን ነው ፡፡
የወፍጮ ቤቱ ሚዛን መጀመሪያውኑ ወደ ወፍጮ ቤት እህል ሊያስፈጭ የሚመጣን ሰው ከፍ ያለ ገንዘብ እንዲከፍል በማሰብ ነገሮች ካላቸው እውነተኛ የመጠነ ቁስ ከፍ የሚያደርግ ነው ፡፡ በወፍጮ ቤቱ ሚዛን እና በትክክለኛው ሚዛን ከመቶ ኪሎ በትንሹ የአስር ኪሎ ልዩነት አለ፡፡ በመሆኑም ኀርየነ ነጻነት ሸማቾች ማኅበር አባላት ለአንድ ወር ተብሎ ከሚሰጠን አምስት ኪሎ ስኳር በሌላ ሚዛን ሲመዘን አምስት ኪሎ ሞልቶ አያውቅም። ከአራት ኪሎ የሚበልጥ አይመስልም፡፡
በወፍጮ ቤቱ ሚዛን እየተፈጸመብን ያለው በደል ይሄ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በሸማቾች ማኅበሩ ውስጥ ቤተሰቦቻቸው ያሉ፤ ነገር ግን የሸማች ማህበሩ አባላት ያልሆኑ ወጣቶች እና ባለሃብቶች የማኅበሩን ህልውና ለማስቀጠል የሚያደርጉትን ጥረት የሚያኮላሽ አካሄድ ሲፈጸም እያየን ነው ፡፡
ለምሳሌ ቤተሰቦቻቸው በማኅበሩ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ማኅበሩ ከጅምላ አከፋፋዮች የሚያመጣቸውን ሸቀጦች ከመኪና ላይ አውርደው መጋዘን ያስገባሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ያለምንም ክፍያ መጋዘኑን ይጠብቃሉ፡፡
መጋዘኑን ከሌቦች ለመጠበቅ በሚሞክሩበት ጊዜ መጋዘኑን ለመዝረፍ ከመጡ ሌቦች ጋር ብዙ ጊዜ ተፋልመዋል፡፡ በመጋዘኑ ውስጥ ያለውን ሸቀጥ ለመጠበቅ ባደረጉት ተጋድሎ ሕይወታቸውን እስከማጣት የደረሱ ወጣቶች አሉ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአይተ ጭሬ ልድፋው ዘመድ የሆነው አይተ ሲኦል ፍቅሩ የማኅበሩ አባል ሆኖ ሳለ ማኅበሩን ለማዘረፍ በሌሊት ቀማኛ እና ገዳይ ቡድን አዘጋጅቶ የማኅበሩን ንብረት ለመንጠቅ ሙከራ አድርጎ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ጠባቂዎችን ገድሏል፡፡
ይሁን እንጂ አይተ ሲኦል ፍቅሩ በከፍተኛ የማኅበሩ ጠባቂዎች እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር ውሎ ከማኅበሩ አባልነት ተሰናብቶ ነበር፡፡
ነገር ግን ሸቀጥ አከፋፋያችን ባለወፍጮው ቤት የስኳር ሚዛኑን ከማንሻፈፉም ባለፈ ይባስ ብሎ አይተ ሲኦል ፍቅሩ የማኅበሩ አባላትን ምንም ይቅርታ ሳይጠይቅ እና ምንም ቅጣት ሳይቀጣ ያለ አባላቱ እውቅና መልሶ የማኅበሩ አባል አደረገው ፡፡ ይሄ ነገር ሁላችንንም ያስቆጣ ተግባር ነው ፡፡ በነገራችን ላይ አይተ ሲኦል ፍቅሩ አንዴ ብቻ አይደለም ማኅበራችንን ለመዝረፍ የሞከረው፡፡
እንደእኔ… እንደኔ …. ለማህበራችን ህልውና የምናስብ ከሆነ ከዚህ ሰው ጋር እስከመጨረሻው ብንለያይ ይሻላል ባይ ነኝ ብሎ ወደ መቀመጫው ተመለሰ፡፡ ሌላው የማኅበሩ አባል የሆነው አቶ ስለሺህ ዋሲሁን ከተቀመጠበት ተነስቶ እኔም የአቶ ፍቅሩ ቢያዝንን ሃሳብ እጋራዋለሁ፡፡ ይሄንን ሃሳብ በምሳሌ እንዳስረዳ ይፈቀድልኝ ብሎ ንግግሩን ጀመረ፡፡ በድሮ ጊዜ በአረብ አገር የሚኖር አንድ ሰው ነበር ፡፡
ይህ ሰው «ግራውድ ፕላስ ዋን» ቤት ነበረው ፡፡ የላይኛውን ቤቱን እንደሚሸጥም በማስታወቂያ ለጠፈ፡፡ ገዥ መጣ፡፡ በጥሩ ገንዘብም የላይኛውን ወለል ቤት ሸጠው፡፡ ለዓመታትም በሰላም ተስማምተው ኖሩ፡፡ ሻጭም ከቤቱ ሽያጭ ያገኘውን ብር ለዓመታት ምንም ሳይሰራ ቁጭ ብሎ በላ ፡፡ ገንዘቡም አለቀ፡፡ ገንዘቡ ባለቀ ጊዜ ቤቱን የሸጠለትን ሰው ከዓመታት በፊት የሸጥኩልህ ቤት ቀሪ ብር ስላለኝ ብር ስጠኝ አለው ፡፡
ከዓመታት በፊት ቤት የገዛውም ሰው ለምድን ነው ብር የምሰጥህ? ይለዋል፡፡ ቤት ሻጩም ቤት ስለሸጥኩልህ ብሎ መለሰ፡፡ ገዢም አንተ ቤት ብትሸጥልኝ ለሸጥክልኝ የቤቱ የላይኛው ክፍል ተገቢውን ገንዘብ ከፍያለሁ አለው ፡፡ ሻጭም በፊት ገንዘብ ብትከፍለኝም አሁንም እንድትጨምርልኝ እፈልጋለሁ ሲል መለሰለት፡፡ ገዥም አምስት ሳንቲም እንኳን ቢሆን እንደማይጨምርለት አስረግጦ ይነግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ሻጭ ያልሸጠውን የታችኛውን ምድር ቤት አፍርሼ ልሰራ ነው በማለት የታችኛውን ቤት ዶማ እና መቆፈሪያ ይዞ ማፍረስ ጀመረ፡፡ ይህን የተመለከተው የላይኛውን ቤት የገዛው ሰው የታችኛው ቤት ሲፈርስ የላይኛው ቤት እንደሚፈርስ ስላወቀ እባክህ አታፍርሰው ሲል ለመነ ፡፡
ሻጭም ምን አገባህ ? ያፈረስኩ የራሴን ቤት ሲል መለሰ፡፡ ገዢም የታችኛው ቤት ሲፈርስ የላይኛው ቤቱ ከሚፈርስብኝ በሚል ሻጭ የጠየቀውን ብር ለመክፈል ተስማማ፡፡ ከአይተ ሲኦል ፍቅሩ ከአረቡ ሰው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ ከአይተ ሲኦል ፍቅሩ ጋር እየተነታረኩ ከመኖር ከማኅበሩ እስከመጨረሻው ማባረር ይሻላል ፡፡
ካልሆነ የላይኛውን ቤት ሸጦ በየጊዜው ብር አምጣ እያለ እንደሚነታረከው ሰው ነው፡፡ ሁሌም ችግር መፍጠሩ አይቀረም ሲል ሃሳቡን ደምድሞ ተቀመጠ፡፡ ይህን ተከትሎ ቆፍጣናው የማህበራችን ሊቀመንበር የንታ ፍሬው ስለጉዳዩ እንዲያብራራ ባለሚዛኑን ጠየቁት ፡፡
ባለሚዛኑ ማናየ አዲስም ሊቀመንበሩ ለጠየቋቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ እንዲህ አሉ «እኔ ለማኅበራችን እድገት እና ህልውና በራሴ ተነሳሽነት ብዙ ነገሮችን ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ የማኅበራችን ማንኛውም ሸቀጣ ሸቀጥ የሚራገፈው በእኔ መጋዘን ነው ፡፡ የመጋዝኑ ደህነነት የተጠበቀ ነው ፡፡ በቂ ጥበቃዎችም አሉት ፡፡ ነገር ግን አንድም ቀን ለመጋዘኑ ኪራይ ተቀብዬ አላውቅም ፡፡
እኔ የማኅበራችንን ህልውና ጠብቄ ለማቆየት ስሯሯጥ ከወገኖቼ እንደዚህ አይነት ስሞታ እና ክስ መሰማቱ አሳፍሮኛል! » አሉ፡፡ ይህን ተከትሎ የንታ ፍሬው የአሸናፊነት ሚስጥር ከሚለው መጽሐፍ ሃሳቦችን ልዋስና ስለጉዳዩ እንዳብራራ ይፈቀድልኝ አሉ፡፡ ንግግራቸውንም ቀጠሉ ፡- ለዓላማ እራስን ማስገዛት በሌለበት ሁኔታ ግንኙነቶች ሁሉ መራር ይሆናሉ፡፡ በግንኙነቶች መካከል እራስን ለዓላማ አለማስገዛት በጊዜ ሂደት የገነባናቸውን ግንኙነቶችን ያፋልሳሉ፡፡ ከናካቴውም በአባላቱ መካከል የነበረውን የጠበቀ ቁርኝት ያፈርሱታል፡፡
ይህ እንዳይሆን እና ሁሌም ለማሳካት ያለምነውን ዓላማ ለማሳካት ይቻል ዘንድ ሁሌም ቢሆን እርስ በርሳችን አንዳችን የሌሎች ጓዶችን ስሜት መጋራት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ ለማድረግ ያሰብነው ዓላማ እናሳካለን፡፡ ባለወፍጮ ቤቱም ደጉ ጠባይህ እንዳይለወጥብህ እና መልካሙ ስምህን እንዳያጠፋብህ ከክፉ ሰው ጋር አትወዳጅ፡፡ ወምስለ ጥዑይ ትጠውይ ወምሰለ ህሩይ ትከውን ወይም ከቀና ጋር የዋለ ቀና ፤ ከጠማማ ጋር የዋለ ጠማማ ይሆናል አይደል የሚባለው። ጠማማዎች ደግሞ ሰንካላ ምክንያት በመፍጠር ወይም በጠማማ ጥቅም በመደለል አለማችንን ያስቱናል፡፡
የንታ ፍሬው ንግግራቸውን ቀጥለው ለክፉ እና ተንኮለኛ ሰው ጋሻህን እና ጦርህን አታውሰው ሲባልስ አልሰማችሁ ፡፡ ምክንያቱም ባዋሳችሁት ጋሻ እና ጦር ተመልሶ አንተኑ ወግቶ ድል ሊያደርግህ ይችላልና ነው ፡፡
አሁን እኛ በሆነ ባልሆነው እያደረግነው ያለው መከፋፈል ለክፉው ጠላታቸው አይተ ጭሬ ልድፋው ድጋፍ እንደማድረግ ቁጥር ነው ፡፡ አይተ ጭሬ ልድፋው ሊያጠፋን ያቀጣጠለውን እሳት ማጥፋት ሲገባን ፕላስቲክ ለብሰን ራሳችንን እሳት ውስጥ እንደመጨመር ነው፡፡
አይተ ጭሬ ልድፋው የሚፈልገው ይህን አይደል!፡፡ በመካከላችን ችግር ቢኖር እንኳን የውጭ ሰዎች እና ጠላቶቻችን ሊሰሙ በማይችሉበት ደረጃ በመወያየት የማኅበራችንን ህልውና ልንጠብቀው ይገባል፡፡ ይህን በምሳሌ ሲያስረዱ ሁለት የተለያየ ቤት ውስጥ የሚሰሩ የሆቴል አስተናጋጆችን በምሳሌነት አነሱ፡፡ ሁለት የተለያዩ ሆቴሎች ውስጥ የሚሠሩ የሆቴል አስተናጋጆች ነበሩ፡፡ አንድ ሰው ሁለቱም ቤት በተለያዩ ቀናቶች ለመመገብ ወደ ሆቴሎቹ ይሄዳል፡፡ ለመመገብ የሚፈልገውን የምግብ አይነት ለመምረጥ አስተናጋጆችን ጠየቃቸው ፡፡ ምን ምን አለ? የአንደኛው ቤት አስተናጋጅ ጥብስ፣ ቅቅል፣ በየአይነት ፣ክትፎ ወዘተ ብሎ በቤቱ የሚገኙ ምግብ አይነቶች ዘርዝሮ ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜ ተመጋቢው «እንዴት ነው ክትፎአችሁ ጥሩ ነው ?» ሲል አስተናጋጁን ይጠይቀዋል ፡፡
አስተናጋጁም ፈጠን ብሎ «የእኛን ክትፎ አይደለም እኛ ቤት ውስጥ የምሰራው ይቅርና ከውጭ መጥተው የሚመገቡ ሰዎች ጣት እንደሚያስቆረጥም የመሰከሩት ጉዳይ ነው፡፡» ብሎ ይመልስለታል፡፡ በተመሳሳይ ምግብ ተመጋቢው ሰው ወደ ሌላ ሆቴል ይሄድና ምግብ ለማዘዝ አስተናጋጁን ይጠራዋል ፡፡ አስተናጋጁንም በሆቴሉ ምን ምን እንዳለ ይጠይቀዋል፡፡ አስተናጋጁም ፈጠን ብሎ ጥብስ ፣ቅቅል፣ በየአይነት ፣ ክትፎ ፣ወዘተ ብሎ በቤቱ የሚገኙ ምግብ አይነቶች ዘርዝሮ ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜ ተመጋቢው «እንዴት ነው ክትፎአችሁ ?ጥሩ ነው?» ሲል አስተናጋጁን ይጠይቀዋል ፡፡
አስተናጋጁም «ለእኛ ክትፎ ማን አቅምሶን ጌታው» ብሎ መለሰ፡፡ ተመልከቱ፤ አንደኛው አስተናጋጅ የቤቱን ሚስጥር ጠብቆ ለሚሰራበት ቤት ማስታወቂያ ሠራ፤ ሌላኛው ደግሞ የሆቴሉን ሚስጢር አሳልፎ ሰጠ ፡፡ እራስን ለዓላማ ማስገዛት በሕግ እንደሚከበር ውል አይደለም ፡፡
መሠረቱ በቁራጭ ወረቀት ላይ የሰፈረ ፊርማ ሳይሆን መልካም ምግባር፣ ሐቀኝነት እና የሌሎችን ስሜት የመጋራት ችሎታ ነው ፡፡ ቀደም ብሎ አቶ ስለሺህ ዋሲሁን እንደተናገረው የአይተ ጭሬ ልድፋውም ባህሪ የአረቡ ቤት ሻጭ አይነት ነው፡፡ የአረቡ ሰው ጊዜ እየጠበቀ ብር አምጡ እያለ እንደሚያስቸግር ሁሉ አይተ ጭሬ ልድፋውም ጊዜ እየጠበቀ እያስቸገርን ነው፡፡
በልቶ አልበላሁም ይላል፡፡ ሠራዊታችንን ገድሎ ገደሉኝ ብሎ ለውጩ ዓለም ኡኡኡ ይላል፡፡ የማኅበራችንን አባላት ገድሎ፣ ደፍሮ ፣ ዘርፎ እና ለስደት ከዳረገ በኋላ ተገደልኩ ፣ ተዘረፍኩ፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ሊፈጸመብኝ ነው ይላል፡፡ የአረቡ ሰው ዓይነት አስቸዖሪ ጠባይ ያለው ጠላት ነው የገጠመን ፡፡ ይሄን ጠላት ለማጥፍት ሚዛናችንን እና የሚዛን መዛኛችንን አቅም በሁለተናዊ መልኩ ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ አይተ ጭሬ ልድፋው እና የጥፋት አጋሮቹ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ በጥፋት ጥርሶቻቸው ቀረጣጥፈው ይበሉናል፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥር 12/2014